
አዲስ አበባ፡- “እኛ ልዩ ነን “የሚል ስሜት ያዘለን የብሔር፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ጽንፈኝነትን መጸየፍና መታገል እንደሚያስፈልግ ምሁራን አሳሰቡ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወርሃዊነት የሚያዘጋጀው የአዲስ ወግ ውይይት ማጠንጠኛውን ‘የጽንፈኝነት መገለጫዎችና ውጤቶቹ’ በተሰኘ ርዕስ ላይ አድርጎ ትናንትና ተካሂዷል።
በወቅቱ የአፍሪካ ልህቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና የስነ አዕምሮ ሐኪም ዶክተር ምህረት ደበበ እንደገለጹት፤ የጽንፈኝነት ዋና ፍላጎት የበላይ መሆን ነው። ጽንፈኝነት “እኛ ልዩ ነን“ የሚል ስሜት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው። በተለይም ሌላውን በማጥላላትና እኛ ስለተጎዳን እኩልነት ያስፈልጋል በሚል ጥያቄ ውስጥ ስለእኩልነት ሳይሆን የበላይ ሆኖ መገኘት ላይ ያተኮረ ችግር ነው።
ጽንፈኝነት ከበታችነትና የጎደለብኝ አለ ከሚል ስሜት ስለሚነሳ እኩልነትን እንዲጠፋ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ምህረት፤ የጎደለኝን ለማስተካከል ለእኔ መጨመር አለበት ሳይሆን ከሌላው ላይ ተቀንሶ ለእኔ ብቻ መደረግ አለበት የሚል ስሜትን ያዘለ በመሆኑ አጥፊና ጥንቃቄ የተሞላበት የመከላከል ጥረት እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል።
በመሆኑም የጽንፈኝነት ችግር ግን ልህቀት ስለሌለው፤ ወደ አማካይ ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ዶክተር ምህረት ገለጻ ፤ ለጽንፈኝነት ተጋላጭ የሆኑ ዕድሜዎች በዋናነት የልጅነትና የወጣትነት ዕድሜዎች ናቸው። በተለይ ልጅነት ላይ ለጽንፈኝነት ምክንያት የሆኑና ሊፋቁ የማይችሉ ስሜቶች በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ሊቀረጹ ይችላሉ።
በወጣትነትም እንዲሁ ለጽንፈኞች የመጋለጥ አዝማሚያው ከፍተኛ በመሆኑ ውስጣችን የሚገነባበት መንገድ ወሳኝነት እንዳለው አመልክተው፤ ጽንፈኝነት እንዳይፈጠር በቤተሰብም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ስለውስጣዊ ዕሳቤ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወልይ በበኩላቸው፤ ጽንፈኝነት ውስጠ ስሪቱ ፖለቲካዊ ነው። የእራሱ የሆነ የሚያራምደው እሳቤና ዓላማ ያለውና በባህሪያዊ አወቃቀሩ ውድመት የሚያስከትል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ፖለቲካን መሰረት ያደረገ ጽንፈኝነት አላማውን አልቀበልም ያሉት ላይ እንደአስፈላጊነቱ ኃይል በመጠቀም ጫና ማድረግ ላይ ያተኩራል፤ በአንጻሩ የብሔር ነክ ጽንፈኝነት ደግሞ ድህነትን፣ የታሪክ መሻማትና አለመስማማትን፣ ትርክቶች መሰረት አድርጎ የሚመራና ወደ ተግባር ሲለወጥም ውድመት የሚያስከትል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥም ያለው ጽንፈኝነት የአንዱን ጠርዝ በመንካት አገርን ወደጥፋት ለመክተት ያለመ ነው፤ ይህ አካሄድ ደግሞ አደጋ አለው። በመሆኑም ከጽንፈኝነት የራቀና ወርቃማ ማዕከል ለመፍጠር በምሁራን፣ በፖለቲካ መሪዎች፣ በብሔርና ሃይማኖት እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ መግባባትን የሚፈጥሩ ጥልቅ ውይይቶችን ማካሄድ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሰለሞን ተሾመ ደግሞ ከፖለቲካና ከብሔር ጽንፈኝነት ባለፈ የሃይማኖት ጽንፈኝነት የእራሱ አካሄድና ጉዳት እንዳለውም አስረድተዋል።
ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እንደ መገፋት፣ መገለል የመሳሰሉ ውስጣዊ መንስዔዎች እንዳሉት የገለጹት ዶክተር ሰለሞን፤ ውጫዊ መንስዔዎቹ ደግሞ የገንዘብ፣ የሞራል፣ የፖለቲካ ድጋፍ ማግኘት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ የሃይማኖት ጽንፈኝነት ዓውዳዊ መንስዔዎችም አሉት፤ በተለይም ጠንካራ ያልሆነ የመንግሥት ስርዓት፣ የሕግ የበላይነት አለመከበርና ሙስና መንስኤ ይሆናሉ። እነዚህ ምክንያቶች ሲዳመሩ የወንጀል መበራከትና የጽንፈኝነት ችግርን ያመጣል።
በመሆኑም የሃይማኖት ጽንፈኝነትን ለመከላከል በመጀመሪያ ብዝሃነትን መረዳትና የጽንፈኝነት ችግር ከየሃይማኖቱ ጋር ተዛምዶ እንደ ሌለው መገንዘብ ይገባል። በተጨማሪ እያንዳንዱ የእራሱንም ሆነ የሌላውን ዕምነት በአግባቡ እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር፤ በመንግሥትና በሃይማኖት መካከል ያለውን ልዩነት ዕኩል ርቀት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጽንፈኝነትን ለመከላከል እኔ የበላይ ነኝ የሚል ስሜት እንዲጠፋና በእኩልነታችን ውስጥ አብረን መጓዝ እንችላለን የሚል የአብሮነት ስሜትን ማዳበር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014