
አዲስ አበባ:- በተማሪዎች መካከል ጤናማ ውድድርን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በሳይንስና ፈጠራ ሥራ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር እየተካሄደ የሚገኘው የሳይንስና ፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ የጎላ ሚና እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
‹‹የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጉዟችንን በሣይንስ ፈጠራ ሥራ እውን እናደርጋለን›› በሚል ለሶስት ቀናት የሚቆየው ሰባተኛው ከተማ አቀፍ የሳይንስና የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይ በወዳጅነት ፓርክ ትናንት ተከፍቷል፡፡
በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት፤ አውደ ርዕዩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና በሳይንስ ፈጠራ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ይረዳል፡፡
መምህራን እና ተማሪዎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች አሳይተውበታል፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሥራዎችን በማበረታታትና እውን በማድረግ ከተሞች ላይ ያለውን ውስብስብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዲሁም ሌብነትና በተለያየ መንገድ የሚባክነውን የህዝብ ሀብት ለልማት ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
አውደ ርዕዩ ጥራት ያለው ፈጣን አገልግሎት ለህዝብ ለማቅረብ የሚያስችለው የተለያየ አማራጭ ሲታይ መሆኑን በመጠቆምም፤ የመምህራንና ተማሪዎቹ በአውደ ርዕዩ የመፍትሔ አካል ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፈጠራ ሥራዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እንዲተኩ የከተማ አስተዳደሩ ሌሎችንም ተቋማት በማስተባበር በበጀት እና በሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ ከለውጡ ወዲህ በትምህርት ዘርፍ በትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነት፣ ጥራትና ተገቢነት ላይ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እርከኖች እስከ ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት በተከናወኑ የትምህርት ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
በሰባተኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት አውደ ርዕይ የታዩት የፈጠራ ሥራዎች የመምህራን የተማሪዎችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጥረት ማሳያዎች መሆናቸ ውን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲካሄድ እንደሚረዳም ጠቁመዋል።
በአውደርዕዩ ላይ የተሻለ የፈጠራ ሥራ ለሚያቀርቡ ተማሪዎችና መምህራን እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
አውደ ርዕዩ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር የሚያሳዩበት መሆኑንና ተማሪዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ደጋግሞ በመሞከር የፈጠራ ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው፤ በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ሥራዎች ጥቅም ላይ ውለው በከተማዋ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርትና አገልግሎቶች በአጠቃላይም ኢኮኖሚያችን ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ናቸው ብለዋል።
የፈጠራ ሥራዎቹ የኢንፎርሜሽን እና የመረጃ መረብ ደህንነት ዘርፍ አገልግሎት በሀገር ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚቻል መሆኑንም አመልክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014