
አዲስ አበባ፡- ባለፉት አስር ወራት ከውጭ ይገባ የነበረ ከአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት ምርት በአገር ውስጥ እንዲተካ መደረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የአስር ወራት የእቅድ አፈጻጸም አድምጧል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ባቀረቡት ሪፖርት ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንዳለ ገልጸዋል። ባለፉት አስር ወራት ውስጥ ከውጭ ይገባ የነበረ አንድ ቢሊዮን 891 ሚሊዮን 600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚገመት ምርት በአገር ውስጥ እንዲተካ መደረጉን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ፤ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት እቅድ ሊሳካ የሚችለው አምራች ኢንዱስትሪዎች የአገሪቷን አንጻራዊ አቅሞችና የመወዳደሪያ ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅመው በአነስተኛ ወጪ፣ በተፈላጊ ጥራትና በተወዳዳሪ ዋጋ ምርት ማቅረብ ሲችሉ እንደሆነ አመላክተዋል።
ከዚህ አንጻር ባሳለፍናቸው አስር ወራት ውስጥ በድምሩ ሁለት ቢሊዮን 218 ሚሊዮን 500ሺህ የአሜሪካ ዶላር ግምት ያላቸው ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ታቅዶ አንድ ቢሊዮን 891 ሚሊዮን 600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም የእቅዱን 85 በመቶ በአገር ውስጥ ምርት እንዲተካ መደረጉን ገልጸዋል።
በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ንዑስ ዘርፍ 144 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ በማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ 186 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ በኬሚካልና በኮንስትራክሽን ንዑስ ዘርፍ 471 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መተካት የተቻለ ሲሆን፤ በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ አንድ ነጥብ 089 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች በማምረት ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ማበርከት እንደተቻለ ሚኒስትሩ አብራርተዋል::
የነባር ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ለማሻሻል እየተሰራ እንዳለ ያመላከቱት ሚኒስትሩ፤ በአስር ወራት አፈጻጸም 49 ነጥብ 2 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በ2014 ዓ.ም አስር ወራት ውስጥ 498 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 418 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደተቻለም ገልጸዋል። ይህም የእቅዱን 84 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም በሪፖርቱ ጠቅሰዋል።
ከአስር ዓመቱ ብሄራዊ የልማት እቅድ ውስጥ ለአምራች ዘርፉ የተቀመጡት ግቦች በጥረት ሊሳኩ የሚችሉ ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ለዚህም የውጭ ምንዛሪና የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የጸጥታ ችግር፣ የፋይናንስ አቅርቦትና የመሠረተ ልማት አለመሟላት እንደ ምክንያት አንስተዋል። ማነቆዎችን በመለየት ለመፍትሄው ከባለ ድርሻ ተቋማት ጋር እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለውን ንቅናቄ እቅድ ጽንሰ ሀሳብን ለሁሉም አስፈጻሚ አካላት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በቀጣይነት በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014