በ1933 ዓ.ም ተቋቁሞ በየእለቱ ለአንባቢያን የሚደርሰው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለፉት ሰማንያ አንድ ዓመታት በስፖርቱ ዙሪያ የተለያዩ የአገር ውስጥ ውድድሮችንና ታላላቅ ዓለምአቀፍ የስፖርት መድረኮችን በመከታተል ታሪካዊ ዘገባዎችን አስነብቧል። ከታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ አንስቶ እስከ ዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ድረስ በርካታ አይረሴ ዘገባዎችን ለአንባቢዎቹ እንካችሁ ከማለት ባሻገር ታሪክን ሰንዶ ለአሁኑ ትውልድ ማሸጋገር ችሏል። አዲስ ዘመን ባለፈው ማክሰኞ ሰማንያ አንደኛ ዓመቱን አክብሯል።
ይህ አንጋፋ የሕትመት ሚዲያ ካለፉት ስምንት አስርት ዓመታት በላይ በተለይም ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ መድረኮች ኦሊምፒክንና የአፍሪካ ዋንጫን በመሳሰሉት ውድድሮች በደመቀችባቸው ዘመናት ለንባብ ያበቃቸው ታላላቅ ዘገባዎች የስፖርቱ ማህደር አንድ አካል ናቸው።ከነዚህ ታሪካዊ ዘገባዎች መካከልም በተወዳጁ የአፍሪካ ዋንጫ በተለይም ኢትዮጵያ በውድድሩ ዋንጫ ያነሳችበትና ብቸኛው ትውልድ የሚኮራበት ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት የነበረውን ታሪካዊ ዘገባ በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን እየቀነጨብን መለስ ብለን እንመለከታለን።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ የመሰረት ድንጋይ ያኖረች አገር እንደመሆኗ መጠን የመድረኩን ጣፋጭ ድል ለአንድ ጊዜም ቢሆን መጎንጨት ችላለች። ኢትዮጵያ በወርቃማ የእግር ኳስ ዘመኗ የአፍሪካ ዋንጫን ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት ማንሳት ስትችል አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኢትዮጵያ አዘጋጅ አገር እንደመሆኗ መጠን ከመስተንግዶው ጀምሮ እስከ ዋንጫው ፍፃሜ ዘገባዎችን ለአንባብያን ሲያደርስ የነበረ ግንባር ቀደም የህትመት ውጤት ነበር። ጥር 6ቀን 1954 የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ የመክፈቻ ጨዋታውን ከቱኒዚያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ እውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ጥር 9ቀን 1954 ለአንባቢያን በበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት አምድ ላይ ያቀረበው ዘገባ የሚከተለውን ይመስል ነበር።
«የሦስተኛው ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ የፉትቦል ውድድር ጥር 6ቀን 1954 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድዮም ላይ በኢትዮጵያና ቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን መካከል ተጀምሮ የኢትዮጵያ ቡድን 4ለ2 ማሸነፉን ከጨዋታው ስፍራ በመገኘትና በራዲዮን በመስማት ሴት ወንዱ፤ ልጆችና ሽማግሌዎች ተባብለው ሳይከፋፈሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልብ የተደሰተ በመሆኑ ሰሞኑን በመስሪያ፤ በመኖሪያ፤ በሆቴልና በቡና ቤቶች፤ በገበያና ንግድ ሱቆች፤ በሴይቼንቶና በአውቶብስ ውስጥ እንዲሁም በልዩ ልዩ አደባባዮች የሚወራው ወሬ አንዳችም ጣልቃ ሳይገባበት የኢትዮጵያን ቡድን አድናቆት የተመልካችን ሁኔታና ይኽንኑ የመሳሰሉ ወሬዎች ብቻ ናቸው»።ሰለሞን የጨዋታውን መክፈቻ በእዚህ መልኩ ካተተ ከቀናት በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተመሳሳይ ውጤት ግብፅን በፍፃሜ ጨዋታ በመርታት እስካሁን የምንጠቅሰውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስኬት ማስቀረት ችሏል።
በወቅቱም አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 15 ቀን 1954 ዓ.ም ባወጣው እትሙ የፊት ገፅ ላይ « ቀልጣፋው የኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን የግብፅን ቡድን 4ለ2 አሸነፈ» በሚል ርእስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለቡድኑ አምበል ሉቺያኖ ቫሳሎ የአፍሪካ ዋንጫውን ሲያበረክቱ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ ይዞ ወጥቷል። የዘገባው መግቢያም የሚከተለውን ይመስላል« ለ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚደረገው የእግር ኳስ ውድድር ጥር 13 ቀን 1954 ዓም ባለፈው እሁድ ቁጥሩ ከ5oሺህ የማያንስ ህዝብ በተሰበሰበበት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድዮም ተደርጎ ፤ የኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን የግብፅን ብሔራዊ ቡድን 4ለ2 አሸንፎ የአፍሪካን ዋንጫ ወስዷል። በሁለቱ አፍሪካዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ውድድር ለማየት በስታድዮሙ ውጭና ግቢ አሰፍስፎ ይጠብቅ የነበረው ተመልካች ታሪካዊ አቀባበል የሚመሳሰል ነበር። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግሥት ወራሽ ልዑል መርዕድ አዝማችን፤ አስፋ ወሰንን፤ ልዑል ራስ እምሩንና ሌሎችንም የክብር ተከታዮቻቸውን አስከትለው በፖሊስ ሰራዊት ሞተር ብስክሌተኞች ታጅበው ከስታድዮም ደረሱ»።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ንቅናቄን በፈጠረው የ2o13 የደቡብ አፍሪካ ዋንጫም አዲስ ዘመን ከዘመኑ ጋር ተጉዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ በርካታ ጨዋታዎችን ተከታትሎ ዘገባዎችን ለአንባቢ አቅርቧል። በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ቤኒንን ከእዚያም ሱዳንን በመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ በደርሶ መልስ ውጤት ዋልያዎቹ ድል አድርገው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለሱ ጥቅምት 3ቀን 2oo5 ዓም ይዞት በወጣው እትሙ በፊት ገፁና በስፖርት ባለቀለም ገፁ የአሰልጣኞች፤ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ስሜትን የሚገልፁና በቃለ መጠይቅ የዳበሩ በርካታ ዘገባዎችን ማቅረብ ችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም