ኢትዮጵያና ግብጽ የአፍሪካ እግር ኳስ ጠንሳሾች ናቸው።ይህን ታሪክ ይጋሩት እንጂ ዛሬ ላይ የሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነቱ ሰፊ ነው። የደረጃ ልዩነቱ የቱንም ያህል ቢሰፋ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የተቀናቃኝነት ስሜታቸው ለአፍታም ደብዝዞ አያውቅም። ሁለቱ አገራት የአለም ብሎም የአፍሪካ ጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ ከመሆናቸው ባሻገር በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሙት ጦርነትና የአባይ ወንዝ ትስስር በእግር ኳሱ መንደር ሲገናኙ ፍልሚያቸውን ይበልጥ ያጦዘዋል። በተለይም ሁለቱ አገራት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ውሀ ሙሌት ጋር በተያያዘ ከቅርብ አመታት ወዲህ የገቡበት ውዝግብ ባላንጣነታቸውን አደባባይ እንዳወጣው በርካቶች ይስማሙበታል።
ዋልያዎቹ ከፈርኦኖቹ፣ ሁለቱ አገራት ውጥረት ውስጥ ባሉበት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም ተጀምሮ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሊከናወን በተቃረበበት በዚህ ወቅት ዛሬ በታላቅ የእግር ኳስ መድረክ ይገናኛሉ። በ2023 ኮትዲቯር ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያ ጨዋታ በምድብ አራት የተደለደሉት ዋልያዎቹና ፈርኦኖቹ ዛሬ ምሽት አንድ ሰአት በገለልተኛ አገር ማላዊ ላይ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም ባለቤት ባለመሆኗ ካፍ ጨዋታዎችን በገለልተኛ አገር እንድታከናውን ፈርዶባታል። ይህም ዋልያዎቹ ዛሬ ከፈርኦኖቹ ጋር የሚያደርጉትን ከእግር ኳስም የዘለለ ትርጉም ያለውን ፍልሚያ በሜዳቸውና በውብ ደጋፊያቸው ፊት እንዳያከናውኑ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ፈርኦኖቹም ይህን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ዋልያዎቹ ሙሉ ወጪያቸውን ተችለው ፍልሚያውን ግብጽ ላይ እንዲያደርጉ ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የክብር ጉዳይ ነውና ዋልያዎቹ በገለልተኛ አገር ጨዋታውን እንዲያከናውኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ብሎ መወሰኑን ከሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።
ዋልያዎቹ ይህን ጨዋታ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት አለማድረጋቸው በእጅጉ ተጎጂ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ቢታመንም በቁጭት ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና ሌሎች ተጫዋቾች በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል። ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል። ባለፈው እሁድ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከማላዊ ጋር አድርገው ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት የተሸነፉት ዋልያዎቹ በጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ ቢከፍሉም ደጋፊያቸውን ባሳዩት ድንቅ ጨዋታ መካስ ችለዋል። ዋልያዎቹ በእሁዱ ጨዋታ የነበራቸው አስደናቂ አቋም ማላዊያንን ጭምር የማረከና ዛሬ ከፈርኦኖቹ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ድጋፋቸውን እንዲሰጧቸው ያደረገ ነው። በማላዊ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት ከእሁዱ ጨዋታ በኋላ ለዋልያዎቹ ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ በተወካዮች አማካኝነት ባደረጉት ንግግር፣ ብሔራዊ ቡድናቸውን በማላዊ በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለፅ በጨዋታው ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል። አክለውም በስራ እና በኑሮ እንቅስቃሴ የማላዊ ዜጎች ሲያገኟቸው ዋልያዎቹ ስላሳዩት አስደናቂ እንቅስቃሴና አቋም እንደሚያወሩላቸው፣ በቀጣይም ከግብፅ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ድጋፋቸውን ለዋልያዎቹ እንደሚሰጡ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ታሪኮች ኢትዮጵያውያን ዋልያዎቹ በፈርኦኖቹ በሰፊ የግብ ልዩነት እንዳይሸነፉ ሲጨነቁ ማየት የተለመደ ነው። በእርግጥ የሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ደረጃና የተጫዋቾች ስብስብ ጥራት አሁንም ለውድድር የሚቀርብ አይደለም። ነገር ግን ዋልያዎቹ በእሁዱ ጨዋታ ያሳዩት እንቅስቃሴ ዛሬ ከተደገመ የአገራቱ የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነት ታሪክ የሚሆንበት እድል ጠባብ አይደለም። ዋልያዎቹ በማላዊ ሽንፈት ቢገጥማቸውም የነበራቸው የጨዋታ የበላይነት በየትኛውም የአፍሪካ ቡድን ዝቅ ተደርገው እንዳይገመቱ የሚያደርግና በተጫዋቾቹም ስነልቦና ላይ ትልቅ የራስ መተማመን የሚፈጥር ነው። ተከላካዩ ያሬድ ባዬና አማካኙ ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ምክኒያት በዛሬው ጨዋታ መሰለፋቸው አጠራጣሪ ከመሆኑ ባሻገር የዋልያዎቹ ስብስብ ፈርኦኖቹን የሚገጥመው ለክብር ጭምር በመሆኑ በትልቅ ተነሳሽነት ተዘጋጅቷል።
ፈርኦኖቹ በተመሳሳይ ባለፈው እሁድ በሜዳቸው ጊኒን ገጥመው አንድ ለምንም በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ቢችሉም ለዋልያዎቹ ስጋት የሚሆን እንቅስቃሴ አሳይተዋል ማለት አይቻልም። ይህ ማለት ግን በዛሬው ጨዋታ ተመሳሳይ አቋም ይኖራቸዋል ማለት አይደለም። ምክኒያቱም የዛሬው ጨዋታ ለዋልያዎቹ የክብር ጉዳይ የመሆኑን ያህል ለፈርኦኖቹም ተመሳሳይ ነውና። ባለፉት ጥቂት ቀናት የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ፈርኦኖቹ ወሳኙን አጥቂያቸውን መሐመድ ሳላህን በጉዳት ምክኒያት በዛሬው ፍልሚያ አያሰልፉም። ይህ ለዋልያዎቹ አንድ መልካም አጋጣሚ ሊሆን ቢችልም የሳላህ አለመኖር ለዋልያዎቹ ፍልሚያውን ቀላል እንደሚያደርገው መታሰብ አይኖርበትም። ዋልያዎቹም በዚህ ይዘናጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ፈርኦኖቹ ሳላ ባይኖር በታላላቅ ጨዋታዎች በቂ ልምድና ጥራት ያላቸው ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ ከዋክብት እንዳሏቸው መዘንጋት ተገቢ አይሆንም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም