ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መደበኛ የአውቶቡስ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። መቼም ሁሉም ነገር የሚያሳስባችሁ ስትደርሱበት አልያም ሲደርስባችሁ አይደለምን? የትኬቱ ነገር ያሳስበኝ የጀመረው አሁን ነው። ያ ሁሉ አገልግሎት የሰጠ ትኬት የት ነው የሚጣለው? እንደ ጠዋት ፀሐይ አንጋጠን የምንጠባበቀው ሽንጠ ረጅሙ አውቶቡስ፤ ወራጅ አለ የሚባልበት መጥሪያ እንዲሁም አስቂኝ ምስሎችን ማሳያ የትዕይንት መስኮቶችን ይዞ እንዴት ቆሻሻ መጣያ ሳይኖረው? እላለሁ፤ «የደላሽ!» እንደማትሉኝ ተስፋ በማድረግ። ነገሬስ ወዲህ ነው፤ አንድ ቀን ምሬት ይሆን ንዴት ወይም ቁጭት፤ ምን እንዳዘለ ባላውቅም፤ አንድ ሰውዬ ድምጹን አሰምቶ ተናገረ።
ድምጹ ከአውቶቡሱ ወዲያ ጥግ ተነስቶ ተከባብረንና ተደጋግፈን በሌላው ጥግ ከቆምነው ጆሮ ደረሰ። ስለትኬት አይደለም የተናገረው፤ «ምን አለበት በሰላም ብንኖር? እንደው ተመችቶን ሃሳባችን ሞልቶ ሳንተኛ፤ ሌላው ቢቀር ትራንስፖርት አንድም ቀን እንኳ እፎይ ሳንል ይኸው ደግሞ ምርጫ እየደረሰ ነው» አሉ። እመኑኝ! እንደው ነገሩ በጽሑፍ ቀላል መስሎ ይሆናል እንጂ አነጋገራቸውስ አንጀት የሚበላ፤ ሆድ የሚያላውስ ነው። ከድምጻቸው በመነሳት ትልቅ ሰው መሆናቸውን ገምቼ አንቱ እያልኩ የጠራኋቸው እኚህ ሰው ከአነጋገራቸውና ከድምጻቸው ቅላጼ ብዙ እውነት ይቀዳል።
ፍርሃት፣ አለማመን፣ ስጋት፣ ጭንቀት፣ ግራ መጋባትና መሄጃማጣት ዓይነት። «ይህን ያህል ባለፈው ምርጫ ምን ገጥሟቸው ነበር?» ሊል ይችላል፤ ማን? ባለፈው ምርጫ አሥራ ስምንት ዓመት ስላልሞላው ሳይመርጥ የቀረ በባሱ የተሳፈረ ወጣት ካለ። የሕይወት ልምድ ቀላል ነገር ይመስለናል? አይደለም። ሲያልፍ ብዙ ነገር የሚረሳ ቢሆንም፤ ነጮቹ ‹ትራውማ› እንደሚሉት ዓይነት ደርሶ ስሙ ሲጠራ እንደሚያባንን ክስተት ምርጫን የሚፈሩ ብዙዎች ናቸው።
እና የሰውዬውን ንግግር ስትሰሚ ምን ምን አሰብሽ በሉኝ፤ «ላገኘው የማልፈልገው ሰው አማራጭ በሌለው ሁኔታ እንገናኝ ብሎ ቀጥሮኝ፤ የቀጠሮው ሰዓት በተቃረበ ቁጥር ‹ቀረሁ› ብሎ ቢደውልልኝ የመመኘት ዓይነት» ስሜት ተሰማኝ። ቢቀርስ!? መቼ እለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥራቸው ከዛሬ ነገ ቀነሰ ሲባል በእጥፍ አካባቢ መጨመራቸውን ተከትሎ አንዱ ቀልደኛ፤ «በቀጣዩ ምርጫ እነርሱ ናቸው የሚመርጡን» ብሎ ሲያስቀን ነበር። ሰሞናችን እንዲህ ሆኖ የለ? ሊሟገቱልን ስማችንን ተሸክመው ለቆሙት የምንሟገተው እኛ ነን። ልብ በሉና አክቲቪስቶች የሚባሉትን ተመልከቱ! እነርሱ ስለተጎዳ ሕዝብ ከሚሟገቱት በላይ የተጎዳው ሕዝብ በእነርሱ ስም ይሟገታል።
ሙግት ቢሉ ደግሞ ሙግት ነው እንዴ? መሳደብና መሰደብ፤ መዘላለፍ ያለበት ሙግት ነው። እና አንዳንዴ እነርሱ ‹እኛ› ለተባልን ለሰፊው ሕዝቦች የቆሙ ሳይሆን እኛ ሰፊው የተባልን ሕዝቦች ስለእነርሱ ክብርና ዝና ስንል የቆምን ይመስለኛል። እንደው በዛ በፈረደበትና ልንጠቀምበት ስንችል መጠቀሚያ በሆንንበት ፌስቡክ የተባለ ማኅበራዊ ገጽ ላይ፤ እነዚህ አክቲቪስቶች አንዲት ቃል ሲወረውሩ፤ ከታች ተሰጥተው የሚገኙ አስተያየቶች ቢያንስ በሃሳቡ ላይ ከመሟገት ተሽሏቸው የሚገኘው ስድድብ ነው።
በነገራችን ላይ በዚህ ‹አክቲቪስት እኛ ወይስ እነርሱ?› በሚለው ሃሳብ ላይ ተመርኩዤ፣ ተንጠልጥዬ፣ ተንተርሼ… ወዘተ አክቲቪስት መሆን ሳልችል የምቀር አይመስለኝም። እዚህ ላይ ግን ‹ከኑግ ጋር የተገኘህ…› ዓይነት ሆኖብኝ ሁሉንም አክቲቪስት ወቅሼ ይሆን? አላውቅም። ከተበሳጫችሁብኝም አክቲቪስት የሚባለው ነገር ራሱ ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ አልተረዳሁትም መሰለኝና አትቀየሙኝ። ሲገባኝ እንደውም አሁን ባለው አረዳድና ሁኔታ ከሆነ ስብሰባና ቀብር መኖሩን ጠዋት ማታ ሰፈራችንን እየዞረ የሚነግረን የሰፈራችን ጥሩንባ ነፊም አክቲቪስት መባል አለበት ብዬ ሳልሟገት አልቀርም።
ምነው አክቲቪስቶች ላይ ችክ አልኩ? ምርጫ ላይ ነን። ታድያ ምርጫ ሲቃረብ የምርጫ ካርድ የሚለው ሀረግ አክቲቪስት ከሚለው ስያሜ በተሻለ ስሙ ተደጋግሞ ይጠራል። ሁሉም ነገር የምርጫ ግብዓት፤ ነገሩም ሁሉ ስለምርጫ ይሆናል። ገሚሱ ‹ትራውማ› ያልለቀቀው ስለሆነ ‹ኮሮጆው ቀለሙ እንደድሮው ነው? ውጤትስ በስንት ቀን ውስጥ ነው ይፋ የሚሆነው?› እያለ ይጨነቃል። አዲሱ መራጭ ደግሞ ‹ተመራጩ ራሱ ማን ማን ነው?› እያለ ይጠይቃል። ማለዳ ላይ ሥራ ለመሄድ ልጁ አልለቅህ ያለው አባት ‹ስመጣ ብስኩት እገዛልሃለሁ… ሽርሽር እወስድሃለሁ… አንበሳ ግቢን አሳይሃለሁ… እንድትጫወት እፈቅድልሃለሁ› እያለ ቃል እንደሚገባው ሁሉ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ላለመውረድ እልፍ አእላፍ ቃል ይገባል። የተሻለ ሃሳብ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ተፎካካሪ የተባለ ፓርቲም በተመሳሳይ ቃሉን ይሰጣል። ሁለቱም በሚመሳሰሉበት ገጻቸው ደግሞ አንዱ ሌላውን ያዳፋል፣ ያጣጥላል። ይህ ነገር ለመራጩ ግራ አጋቢ ነው።
ነገሩ ‹አልማዝን አይቼ አልማዝን ሳያት› ዓይነት እንዳይሆንበትም ይሰጋል። ተመራጭ ደግሞ ይህን ግራ መጋባት የበለጠ ይጠቀምበታል። ምርጫ ለአንዲት አገር የተሻለ ፖሊሲና አሠራር ለማምጣት የሚደረግ ክርክር ሳይሆን አንዱን ጎትቶ ጥሎ፤ ተጎታች ከወረደበት ወንበር ላይ የመቀመጥ ፉክክር ይመስል ነበር። በዚህ ትግል መካከል መራጩ ሕዝብ የተመራጮች ካርድ ሆኖ ይገኛል። ግብዓት ይሆናል፣ መስዋዕትነት ይቀበላል፣ ጉዳቱን ይቀምሳል። ራሱ ምርጫ ደግሞ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ዓይነት ሰው፤ ሊያስታውሱት የማይፈልጉትና ቢቀር የሚመኙት፤ አልያም በእንቅልፍ አሳልፈውት ‹አልፏል› ተብለው እንዲቀሰቅሱ የሚፈልጉት ክዋኔ ወደመሆን ይሻገራል። በዚህኛው በተቃረበው ምርጫ ይህ ነገር ይደገማል ወይ? በነፍስ ወከፍ የወከሉን የሚመስሉ ፓርቲዎች ምን እንዳሰቡ ባናውቅም፤ አስጨናቂ እንደማይሆንብን ተስፋ እናደርጋለን። እንደ ቀደመው ጊዜ ድምጽ ለማግኘት ሕዝብን ግብዓት ማድረግ ቀርቶ አሁን ላይ አጀንዳ ፍለጋ አገርን እንዳንሰዋ ግን ማሰብ ያስፈልጋል። በነፍስ ወከፍ የወከለውን ሕዝብ ‹እገሌ ጠላትህ ነው› በሚል በየትኛውም ዘመን አገልግሎት በማይሰጥ ሃሳብ ሳይሆን ‹ይሄን መንገድ ተመልከት› የሚል አማራጭ የሚያቀርብ የ21ኛው መቶ ክፈለ ዘመን ፖለቲከኛ።
‹የለመዱት ሠይጣን ይሻላል…› ብሎ ላለመውረድ ተመራጭን የሚሰዋ ሳይሆን ‹ደስ እንዳላችሁ…› የሚል የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሥልጣን ላይ የሚገኝ ፓርቲ አምሮናል። ይህኛው ምርጫ ይህን እንዲያሳየን ነው የምመኘው። ከዛ ትዝታችን ተቀይሮ ‹የእነ እገሌ ክርክር ትዝ ይልሃል!› የምንባባልበት፤ ባስ ውስጥም ሁላችን ሰፋ ሰፋ ብለን በተመቻቸ ወንበር ተቀምጠን ‹ምርጫው ተጎትቶም ቢሆን ደረሰልን… ደግሞ አዲስ ሃሳብ ማን ያመጣ ይሆን?› የሚባልለት እንዲሆን እመኛለሁ። እና በጥቅሉ መራጮች እንጂ የተመራጮች ካርድ እንዳንሆን ይጠብቀን፤ እኛም እንጠንቀቅ ለማለት ነው። የኔ ነገር! ምርጫው’ኮ ገና ነው አትሉኝም? ቢሆንም! መድረሱ አይቀርም ብዬ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በሊድያ ተስፋዬ