በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ስምንት አገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው የተፋለሙበት የመካከለኛውና ምሥራቅ አፍሪካ(ሴካፋ) የሴቶች ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ተለይተዋል። በውድድሩ እየተካፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ከሶስት ጨዋታ በኋላ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ከሆኑ አራት አገራት አንዱ መሆን ችሏል።
የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛንዚባርን አምስት ለምንም በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ የቻሉት ሉሲዎቹ፣ የምድባቸውን ሁለተኛ ጨዋታ ባለፈው ቅዳሜ ከታንዛኒያ ጋር በማድረግ ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ሉሲዎቹ የምድባቸውን ሶስተኛና የመጨረሻ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ደቡብ ሱዳንን በመግጠም አራት ለዜሮ ማሸነፋቸውን ተከትሎም የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችለዋል።
ሉሲዎቹ ከምድባቸው ሰባት ነጥብና ዘጠኝ ግብ ይዘው ሁለተኛ በመሆን የግማሽ ፍጻሜውን ፍልሚያ የተቀላቀሉ ሲሆን፣ በዚሁ ምድብ የምትገኘው ታንዛኒያ ሶስተኛውን ጨዋታ ዛንዚባርን በአንድ ደርዘን ግብ አስራ ሁለት ለዜሮ በመርታቷ በግብ ክፍያ በልጣ ከምድቡ አንደኛ በመሆን ግማሽ ፍጻሜውን ልትቀላቀል ችላለች። በዚህም ሉሲዎቹ በሌላኛው ምድብ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችው የውድድሩ አስተናጋጅና ጠንካራ ቡድን ያላትን ዩጋንዳን በግማሽ ፍጻሜ የሚገጥሙ ይሆናል።
የምድብ ጨዋታዎቿን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ የቻለችው ዩጋንዳ በተለይም የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ ቡሩንዲን ሶስት ለአንድ መርታቷ የሚታወስ ሲሆን ቡሩንዲ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፏ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያውን ተቀላቅላ ያለፈው ውድድር የፍጻሜ ተፋላሚዋ ታንዛኒያን የምትገጥም ይሆናል።
በሶስቱ የምድብ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ከመረብ ያሳረፈችው የታንዛኒያዋ ተጫዋች ኦፓህ ክሌመንት የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር በቀዳሚነት ትመራለች። ከደቡብ ሱዳን ጋር በነበረው ጨዋታ ሶስት ግቦችን ለሉሲዎቹ ማስቆጠር የቻለችው አረጋሽ ካልሳ እንዲሁም በሶስቱ ጨዋታዎች ግቦችን ማስቆጠር የቻለችው የሉሲዎቹ ወሳኝ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሎዛ አበራ አራት አራት ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር በቅርብ ርቀት ይከተላሉ።
ዩጋንዳ ለአምስተኛ ጊዜ እያስተናገደች በሚገኘው የሴካፋ ውድድር የፍጻሜ ተፋላሚ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ይህንን ለማሳካት ግን ከአዘጋጇ ዩጋንዳ የግማሽ ፍጻሜ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃታል። አዲሱ የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከበርካታ ወራት በፊት በሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር የሉሲዎቹን ተተኪዎች እየመራ የውድድሩ አዘጋጅ የነበረችውን ዩጋንዳን በፍጻሜ ጨዋታ ከመመራት ተነስቶ ሶስት ለሁለት በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል። ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋርም ዩጋንዳ የውድድሩ አዘጋጅ ሆና በግማሽ ፍጻሜ ተገናኝተዋል።
አሰልጣኝ ፍሬው ከ20 ዓመት በታች የሴካፋን ዋንጫ ከስኬታማው የወጣቶች ቡድን ጋር ሲያነሱ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል። ከሴካፋው ጣፋጭ ድል በኋላም ያንኑ ቡድን እየመሩ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ እስከ መጨረሻውና አራተኛው ዙር መጓዛቸው ይታወሳል።
አሰልጣኙ በወጣቶች ቡድን ያስመዘገቡት ውጤት በዋናው ብሔራዊ ቡድንም ተመሳሳይ ስኬት ለማስመዝገብ ተስፋ እንዲጣልባቸው አድርጓል። ለዚህም ከሳምንታት በፊት ሉሲዎቹን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው የቡድን ስብስባቸውን ስኬታማ ከነበረው የ20 ዓመት በታች ቡድን በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በማሳደግ ከነባሮቹና ልምድ ካካበቱት ጋር በማጣመር ሲዘጋጁ ቆይተዋል።
ሉሲዎቹ ከዩጋንዳ ጋር በሚኖረው የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ አሸንፈው ለፍጻሜ መድረስ ከቻሉ ለአሰልጣኙም ይሁን ለብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ታሪክ ትልቅ ስኬት ሆኖ ይመዘገባል። ኢትዮጵያ ባለፉት አራት የሴካፋ ዋንጫዎች እኤአ በ2016 እና 2018 ዩጋንዳና ሩዋንዳ ላይ በተዘጋጀው ውድድር ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ታሪክ ትልቁ ውጤት ሆኖ ይታወሳል። አሰልጣኝ ፍሬውና ሉሲዎቹ ከዩጋንዳው የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ በኋላ ይህን ታሪክ የማሻሻል ወይም የመጋራት እድሉ በእጃቸው ይገኛል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2014