አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 11ኛው ክልል ሆኖ በዚሁ ዓመት ህዳር ወር በይፋ መመስረቱ ይታወቃል። በወቅቱ አምስቱ ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን በመደገፋቸው ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስራ አንደኛው ክልል ሆነው በይፋ ተመስርተዋል። አዲሱን ክልል የመሰረቱትም የካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው። ይህ አዲሱ የአገሪቱ 11ኛው ክልል ከተመሰረተ የወራት ያህል እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በእነዚህ ጊዜያት ስላከናወናቸውና ወደፊት ስለሚያከናውናቸው ውጥኖቹ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ከሆኑት ከዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ በማድረግ እንደሚከተለው አቅርቦታል።
አዲስ ዘመን፡- የክልል እንሁን ጥያቄ ለመነሳቱ ገፊ የሆኑ ምክንያቶች ምን ነበሩ ከሚለው ጥያቄ ቃለ ምልልሱን ብንጀምር?
ዶክተር ነጋሽ፡- በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦች ለበርካታ ዓመታት እንደጥያቄ አድርገው ሲያነሱ የነበረው ከሌሎች ወንድሞቻቸው እኩል የመልማት እድል አላገኘንም የሚል ነው። የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት በመኖሩም ይህን መፍታትና መመለስ በሚያስችል አይነት የመንግስት የአስተዳደር ወይም የአደረጃጀት መዋቅር መደራጀት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ጥያቄው ሲቀርብ የነበረው። በተለይ ከነባሩ የክልል መዋቅር በጣም ርቀን በመገኘታችን በቂ መንግስታዊ ድጋፍ እያገኘን አይደለንምና እነዚህን የመልማት ፍላጎት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎችን መመለስ በሚያስችል አደረጃጀት ተደራጅተን የራሳችንን ባህል፣ ቋንቋና እሴት ማጎልበት አለብን የሚል ጥያቄ ነው ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ሲነሳ የሰነበተው።
ነገር ግን ይህንን ጥያቄ በተጨባጭ ችግሩ አለ ወይ የለም የሚለውን በማጥናት ተገቢ ምላሽ ማስጠት ሲገባ ድምጽ ያልተሰማበትና የሚሰማ አካል የሌለበት ዘመን ነበርና በዚህ ምክንያትም በዚህ ክልል ውስጥ የሚተዳደሩ ዞኖች ጥያቄያቸውን በይፋ እያቀረቡ፤ ጥያቄውን የሚያቀርቡ አካላትም በሌላ መልኩ እየተፈረጁ የመጡበት ሂደት ነበር። ይሁንና የዛሬ ሶስትና አራት ዓመት ለውጡ ሲመጣ እነዚህ ጥያቄዎች ይበልጥ እየገነኑ ሊቀርቡ ቻሉ።
የጥያቄዎቹ ተደጋግሞ መቅረብና ባለፉት ጊዜያትም ሲቀርቡ የነበሩትን በማየት የለውጡ መንግስት ይህ ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት በሚል እነዚህን ጉዳዮች እንደገና አጥንቶና አይቶ ምላሽ ወደመስጠት ሄዷል። በዚህም ሂደት በርካታ ምክክሮች በህዝብ ደረጃ እንዲሁም በመንግስት የፖለቲካ አመራር ደረጃ ተካሂዷል። ምንም ልዩነት በሌለው ድምጽ፤ በክልል እንተዳደር ሲሉ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ ህዝቦች በሙሉ በመስማማት፤ ያንንም ስምምነታቸውን በጋራ ቀጥተኛ በሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ በሆነው በሕዝበ ውሳኔ ድምጻቸውን ሰጥተው ክልል መስርተዋል።
ስለዚህም በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይ በለውጡ መንግስትና መሪው የብልጽግና ፓርቲ የወሰደው በሳል አመራር በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና በክልላችን ህዝብ ዘንድም እየተወሳ የሚኖር ታሪካዊ ውሳኔ ስራ ነው ብለን የምንወስደው ነው።
አዲስ ዘመን፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ምንድን ናቸው?
ዶክተር ነጋሽ፡- ይህ ክልል ከተመሰረተ በኋላ ዋና ተግባራት አድርገን የተነሳነው የህዝብና መንግስታዊ ለውጥን ሊያሳልጥ የሚችል የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ስርዓትን ሊያሳልጥ የሚችል አይነት አደረጃጀት መስራት ትልቁ ስራ ነበር። በዚህም ሂደት ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ አባላትን የማደራጀት ስራ ሰርተናል፤ ወደስራም እንዲገቡ አድርገናል።
ሁለተኛው አንኳር ጉዳይ ከነባሩ ክልል ጋር የነበረን የሀብትና የእዳ ልየታ ስራ ሙሉ በሙሉ ባናጠናቅቅም የተወሰኑትን ስራዎችን ሰርተናል። በጀታችንን ተከፋፍለናል፤ አንዳንድ ተንቀሳቃሽ የሆኑ ንብረቶችን እንደዚሁ ክፍፍል አድርገናል። በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ከፌደራል መንግስት ልናገኝ የሚገባውን የድጎማ በጀትን በሚመለከት ከነባሩ ክልል ተቀንሶ ቀመራችን እንዲለይ ተደርጓል። ከዚህ ውጭ ያሉትና ከነባሩ ክልል ጋር በጋራ ያፈራናቸው ሀብቶች በተለይ ቋሚ ንብረቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች አልነካነውም፤ ምክንያቱም ይህ የሲዳማ ክልልንም የሚያካትት በመሆኑ የደቡብ ክልልን እንዲሁም እኛን የደቡብ ምዕራብ ክልልን በተጨማሪም ሲዳማንም የሚያጠቃልል በመሆኑ ሶስታችንም በጋራ መስራት አለብን ብለን ኮሚቴ አደራጅተናል። ነገር ግን ኮሚቴው ሙሉ በሙሉ ወደስራ አልገባም። ምክንያቱም ባለቤት ሆኖ ይዞን ያለው የደቡብ ክልል ስለነበር የሚመራውም እርሱ ስለሆነ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ እያቀረብን ነው። በመሆኑም ኮሚቴው ወደስራ ገብቶ ያለውን ሀብት ክፍፍል እንዲያደርግ እየሰራን ነው።
ሶስተኛው ተግባራችን የነበረው በዚህ ክልል በሚደራጁበት ሰዓት ክልሉ የሚይዛቸው ዞኖችን የመልማት ፍላጎትን ያማካለና ፍትሃዊ የሆነ የልማት ስርጭትን እውን ማድረግ የሚያስችል መሆን አለበት የሚል ነው። ሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን እና አንኳር የፖለቲካ ስልጣን ቦታዎች በአንድ ቦታ ወይ በአንድ ማዕከል ላይ ብቻ መከማቸት የለባቸውም ብለን በጉዳዩ ላይ በጋራ ስናቀነቅን መጥተናል። ይህ ደግሞ በህዝባችን ዘንድ ፍጹም ተቀባይነትን አግኝቶ ክልላችን የብዝሃ ማዕከል፣ የክልል ዋና ከተሞቹ ከአንድ ከተማ በላይ በመሆን ብዝሃ ከተማ መሆናቸውን በህገ መንግስታችን ጭምር የደነገግነው በመሆኑ ይህ ወደፊትም ምናልባት እንደ አገርም ትልቅ ተሞክሮ ይሆናል ብለን መናገር የምንችለው ተግባር ነው።
ይህንን የክልል ማዕከላት ጉዳይ የመነጋገርና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሊፈታ በሚችል መልኩ ደንበኞቻችን ጉዳይ ሊያስፈጽሙ ወደ አንድ ማዕከል መጥተው ከአንድ ማዕከል ወደ ሌላ ማዕከል በማይጉላሉበት ሁኔታ እዛው እንዲጨርሱ የማድረግ ስራ ነው። ተመሳሳይ ባህሪያት ያላቸው ተቋማትን በአንድ ላይ አድርጎ በማዕከላቱ ላይ የማስቀመጡ ተግባር ትልቁ ስራ ነበርና ይህንን የሚሰራ አጥኚ ቡድን አደራጅተን አጥኚ ቡድኑ በርካታ ምክክሮች አድርጎ በአሁን ሰዓት ወደማጠቃለያ ደርሰናል፤ ምናልባት በአዲሱ በጀት ዓመት ይህን የብዝሃ ማዕከላትን ጉዳይ እውን አድርገን ማዕከላቱ በተመረጡ ከተሞች ላይ እንዲቀመጡ የማድረግ ስራ ነው የሚተገበርበት ጊዜ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አካሄድ ክልሉ ስንት ከተሞች ይኖሩታል ብላችሁ ነው በእቅድ ደረጃ የያዛችሁት? ስብጥሩስ ምን ይመስላል?
ዶክተር ነጋሽ፡- በዚህም ሂደት እስካሁን ባለው ደረጃ ክልሉ አራት የክልል ዋና ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት ተግባብተናል። እነዚህም አንደኛው የፖለቲካንና የአስተዳደር ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ፖለቲካ ሲባል የፓርቲ መዋቅር ያለበት ሲሆን፣ አስተዳደር ሲባል ደግሞ ከመስተዳድሩና ከርዕሰ መስተዳደሩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ያሉበት ማለት ነው። ሁለተኛው የህግ አውጪው ወይም የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ይሆናል። ሶስተኛው የህግ ተርጓሚ ወይም የዳኝነት አካል የሚቀመጥበት ይሆናል። አራተኛ ደግሞ የብሄረሰቦች ምክር ቤት የሚቀመጥበት ይሆናል። እነዚህ ትልቅ የፖለቲካ፣ የመንግስትና የህዝብ ስልጣን አካላት ናቸው።
ከዛ ውጭ ያሉ አስፈጻሚ አካላት ያሉ ሲሆን፣ አስፈጻሚ አካላቱ በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ እንደገና በጣም በተጠና መንገድ ተመጋጋቢና ተያያዥነት ያላቸው አስፈጻሚ አካላት አንድ ላይ ይሆኑና በእነዚህ በተከፋፈሉ በአራቱ ላይ የሚሰራጩ ይሆናሉ። ይህ ማለት አንድ ባለጉዳይ አንድ ጉዳይ ይዞ ከሄደ ሳይጉላላ አጠናቅቆ እንዲመጣ የሚያስችለው ይሆናል።
ከተሞቹ እንዲህ አይነቱን እድል ማግኘታቸው የመልማት እድል እንዲኖራቸው የሚያደርግ ይሆናል። በተጨማሪም የስራ አጥነት ችግር በተመጣጣኝ መንገድ በሁሉም ቦታ እንዲቀረፍ የሚያደርግም ነው። ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ አንድ ቦታ ላይ አንድ ማዕከል ብቻ ይዘን ያንኑ ማልማት ነበር፤ በዚህ አካሄድ ደግሞ ሌሎችን ዞር ብለን አናይም ነበር። አሁን ይህ አይነቱ አካሄድ የሚቀር በመሆኑ ሁሉም እንደየሁኔታ የሚለሙ ይሆናል። የግል ባለሀብቱ አካባቢዎችን እንዲያለሙና ኢንቨስት እንዲያርጉ ይደረጋል። በተጨማሪም መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ እንዲሰራጩም እድል ይፈጥራል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ከተሞቹ እኛም በክልላችን ፍትሃዊ ውክልና አለን ብለው በመንግስት ብሎም በፖለቲካ አስተዳደሩ ላይ እምነት እንዲጥሉ ያደርጋል።
ይህ አይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ አይደለም፤ ይህ እንደ አገር ሲታሰብ ራሱን የቻለ አንድ ተሞክሮ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ሌላውና አራተኛው አንኳር ጉዳይ ክልላችን አዲስ የተቋቋመ ከመሆኑ አኳያ አካባቢውን ለልማት ምቹ የማድረግ ስራ ነው። በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ክልል ነው። ምናልባትም 80 በመቶ የሚሆነው የክልላችን አካባቢ በዓመት ውስጥ ሰባት ስምንት ወር ያህል ዝናብ የሚያገኝ ቦታ በመሆኑ ለእርሻ ምቹ ነው፤ የተለያዩ የግብርና ውጤቶች ለአገራዊ ማዕከላዊ ገበያ አልፎም ለውጭ አገር የሚተርፍ ነው፤ በተለይ አካባቢያችን በቡና ምርት በጣም የታወቀ ነው። ከዚህም ሌላ በቅመማቅምም፣ በማር፣ በማዕድናት ምርትም ጭምር የሚታወቅ ነው። እንዲሁም የወርቅና የድንጋይ ከሰል በአገራችን ሲታይ ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው። እያመረተም ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኝ ነው። በተለይ ደግሞ በክልላችን ምዕራቡ አካባቢ በወርቅ ምርት በጣም እንታወቃለን።
አሁን አሁን በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚያስገቡትን የድንጋይ ከሰል ለመተካት እየተጓዝን ነው። በመሆኑም ያለንን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ እምቅ ሀብቶችን አውጥተን በማሳየት ላይ ነንና በዚህ ዙሪያ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ አካላት መጥተው ቢሰሩ በሩ ክፍት ነው።
በተለይ ደግሞ ክልላችን ለቱሪዝም ሀብት ምቹ ነው። ትልልቅ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሐይቆች አሉ። የግቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ የሚገኘው በክልላችን ነው። የኮይሻ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት እየተሰራ ያለ የኃይል ማመንጫም በክልላችን ውስጥ የሚገኝ ነው። ከዛ ባሻገር ሁለት ፓርኮች በክልላችን ውስጥ ይገኛሉ፤ እነዚህም የጨበራ ጩርጩራና የኦሞ ፓርክ ሲሆኑ፣ እነዚህም በጣም በብዝሃ ሕይወት የበለጸጉና ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ናቸው። እነዚህ ትልልቅ የሆኑ የቱሪዝም ሀብት በመሆናቸው ብዙ ኢንቨስተሮች ወደክልላችን በመምጣት መሬትም በመረከብ በመስራት ላይ ናቸው። አምራች የሆኑ ትልልቅ ባለሀብቶችም ስራ ጀምረው ምርታቸውን ወደማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
አምስተኛው አንኳር ጉዳይ በተለይ ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ነው። በክልላችን ሁለት አይነት የጸጥታ ስጋት አለ። አንደኛው የምዕራቡ አካባቢያችን እንደሚታወቀው የአርብቶ አደሩ አካባቢ ነው። ይህ አርብቶ አደር የተለያዩ ባህላዊ ልማድ ያሉት ነው። በተለይ በጋብቻ ወቅት ከአንድ ቤተሰብ አንድ ወንድ ሊያገባ ሲፈልግ ለሴቷ ቤተሰብ የሚሰጥ ቁጥሩ በርከት ያለ የከብት ጥሎሽ አለ። ሁለተኛው ድንገት በተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች ምክንያት አንድ ሰው የሌላኛውን ሕይወት ቢያጠፋ የደም ካሳ ተብሎ የሚከፈለው አሁንም በከብት ነው። አርብቶ አደሩ እነዚህን አይነት ልማዶች ስለነበሩትና እነዚህን ልማዶች ለማስፈጸም ሲል አንዱ አካባቢ ያለው አርብቶ አደር ሌላው አካባቢ ካለው አርብቶ አደር ከብት የመዝረፍና በዝርፊያ ሂደት ውስጥ በሚፈጠር ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋት በተደጋጋሚ ይከሰታል። ይህን የማረጋጋት ስራ አንዱ ተጠቃሽ ነው።
ሌላኛው የጸጥታ ችግር ምናልባት ሁላችንም እንደምናወቅው በ2010/2011 አካባቢ በሸካ ዞን ቴፒና አካባቢው ላይ ሰፊ የእርስ በእርስ ግጭት ተከስቷል። በዚህም የሕይወት መጥፋት የመኖሪያ ቤቶች መቃጠልና ንብረት መውደምም አጋጥሟል። በዚህም በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተፈጥሯል። በመሆኑም ከተማዋ ላለፉት ሁለት ዓመታት አጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋ ወደ ዜሮ ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯልና ይህን የሚፈጥሩና መሳሪያ ታጥቀውና እንደ ሽፍታ ጫካ ገብተው እንደፈለጉ የሚገድሉና የሚዘርፉ አካላት ነበሩ። እነዚህ አካላት ከእዛው አካባቢ የወጡ ናቸው። በእርግጥ ከኋላ በመሆን በሉ እያለ የሚደግፋቸው አካል አለ። ከዚህም የተነሳ አካባቢው ተዳክሞ ቆይቷል።
እኛም አካባቢው እንዲያገግም ባለፉት ስድስት ወራት መጠነ ሰፊ ስራዎችን ሰርተናል። በርካታ ውይይቶችንም አካሂደናል። ማህበረሰቡንም በማወያየት የሸፈቱት እጃቸውን እንዲሰጡና መሳሪያም እንዲያስረክቡ፣ ቀለል ያለ ጥፋት የፈጸሙት ደግሞ ማህበረሰቡም ይቅር እንዲላቸው እንዲሁም ከባድ ጥፋት ያጠፉት ደግሞ ወደ ህግ አግባብ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ በተደጋጋሚ ሰርተን ከህዝብ ጋር የጋራ ምክክር አድርገናል።
በመጀመሪያ አካባቢ ወደ ህዝብ ስንገባ ህዝቡ ደስተኛ አልነበረም፤ ለምን ትመጣላችሁ ሲል ሲጠይቅ ነበር። ሽፍቶቹን ጠቁሙ እያላችሁ ባሳየናችሁ ጊዜ ግን እናንተ አትይዟቸውም፤ ስለዚህ ሽፍቶች መልሰው የሚያጠፉት እኛኑ ነው ሲሉም ቅር ሲሰኙ ነበር። በመጀመሪያ ሰርታችሁ አሳዩን አሉን። እኛም የጸጥታ ኃይላችንን በማደራጀት ሽፍቶቹ እጅ እንዲሰጡ እንዲሁም እጅ አንሰጥም ብለው ግብ ግብ የተፈጠሩትንም የመያዝ ስራ መስራት ቻልን። ሕዝቡን ከዚያ ‹በኋላ እኛ ነን ስራውን የምንሰራው፤ ምክንያቱም መንግስት መኖሩን አሁን በተግባር አረጋግጠናል› ማለት ጀመረ። በመሆኑም ከእኛ ጋር ወደጫካ በመግባትና ሽፍቶቹ መሳሪያ የቀበሩበትምን ቆፍረው የማውጣት እንዲሁም የመሸጉበትን ዋሻ ሁሉ በመጠቆም ስለተባበሩን በርካታ ሽፍቶች እጃቸውን ለህግ ሰጥተዋል። እጅ አንሰጥም ያሉት ደግሞ ከልዩ ኃይሎችና ከሌሎች ጸጥታ አካላት ጋር በተደረገው ቅንጅት እርምጃ ተወስዶባቸዋል። አሁን አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሮ ቴፒ አካባቢ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጣም በተሻለ መልኩ ወደቀድሞ በመመለስ ላይ ነው፤ ይህ ትልቁ ስራ ነው።
ከውጪያዊ ሰላም ጋር ተያይዞ ክልላችን ረጅም የሚባል ወሰን ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል። የደቡብ ሱዳን ሸማቂ ኃይሎች በተለያየ ጊዜ ወደክልላችን ይገባሉ። እነርሱም የአርብቶ አደር ባህሪ ያላቸው ስለሆኑ በከብት ዝርፊያ ምክንያት ሕይወት እስከመጥፋት የሚደርስበት ሁኔታ አለ፤ አንዳንዴ ከዝርፊያና ከግድያ ጎን ለጎን ሰዎችን ከነህይወታቸው በተለይ ሴት ህጻናትን አፍነው ይዘው የመሄድ ነገር አለባቸው። ይህን ችግር በእኛ አቅም የምንፈታ እንደተጠበቀ ሆኖ በተጨማሪነት የፌዴራል መንግስትን ልዩ ድጋፍ ይጠይቃል። ምክንያት እነርሱ በጣም የተደራጁና ከባድ መሳሪያም ጭምር ያላቸው ናቸውና ነው።
በእኛ በኩል ግን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከሚገኙ ግዛቶች መሪዎች ጋር የመነጋገር ኢ-መደበኛ የሆነ ውይይት ጀምረናል። ይህ ወደመደበኛ ውይይት እንዲቀየር መንግስትንም ጠይቀናል። ድንበር አካባቢ የህብረተሰብ አካላት ተመሳሳይ ስነ ልቦናም ሆነ ባህል ያላቸው እንደመሆናቸው ብናቀርባቸው በተለያዩ ጉዳዮች የሚመጣን ተጽዕኖ መለወጥ ይቻላል የሚል እምነት አለን። በእርግጥ ከእኛ ወገን ብቻ ሳይሆን ይህንን የመቀራረቡን ሁኔታ እነርሱም የሚፈልጉት መሆኑን ለማስተዋል ችለናል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ የፌዴራል መንግስቱን ልዩ ድጋፍ የሚጠይቅ ነው። ጉዳዩን ደግሞ የፌዴራል መንግስትም የሚያውቀው ሲሆን፣ የጀመራቸውም ስራዎች አሉ።
የመጨረሻው ዋና ስራ የምንለው የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራን ነው። ከመልካም አስተዳደር አኳያ ይህ ክልል ሲደራጅ በርካታ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ነበሩ። በተለይ የአደረጃጀትና የመዋቅር ጥያቄዎች፤ አንዳንዶቹ የከተማ አስተዳደር ለመሆኑ አንዳንዱ ደግሞ የዞን አስተዳደር ለመሆን ሌላው ደግሞ የወረዳ አስተዳደር መዋቅር እንዲኖረው የመፈለግ ጥያቄዎች ነበሩ። በዚህም የተነሳ መፍታት የምንችላቸውን ፈትተን ሌሎቹን ደግሞ ወቅቱ አይደለም፤ በያዝነው በጀት የመንግስት መዋቅር እያሰፋን የሕዝብ አገልግሎትንና የልማት ስራዎችን መጉዳት የለብንም በሚል መግባባት ፈጥረን ለጊዜው እንዲቆይ አድርገናል። ተገቢነት ያላቸውን ጥያቄዎች ግን ምላሽ ሰጥተናቸው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።
ከልማትም አኳያ ያደሩ የልማት ጥያቄዎች በርካታ ናቸው። በክልላችን የተጀመሩ የመሰረተ ልማት፣ የመንገድ፣ የውሃ እንዲሁም የተለያዩ የማህበራዊ ተቋማት እንደጤና እና ትምህርት ተቋማት ግንባታዎች በተለይም ከእነዚህ ውስጥ ከስምንት እስከ 12 ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸውና ባለችን ውስን በጀት ቅድሚያ የሚሹትን በማስቀደም እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኢፌዲሪ ህገመንግስት የክልሉን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል አንቀጽ ቢኖርም ክልሉ የዘመናት ጥያቄዎቹ አልተመለሱም ነበር፤ ነገር ግን እርስዎም እንዳሉት ለውጡን ተከትሎ ጥያቄዎቹ ተመልሰዋል፤ ይህ የሚያሳየው ምንድን ነው?
ዶክተር ነጋሽ፡- ይህ የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ መልስ ያገኘበት ጊዜ ነው፤ እውነትም የለውጡ መንግስት የሕዝብን ጥያቄ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ሰምቶም ተገቢ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን በተጨባጭ ያረጋገጥንበትና ትልቁን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በተግባር ያየንበት ነው። እኛ ከሲዳማ ቀጥለን ሁለተኛውን ፍሬ ያጣጣምንበት ስርዓት ነው ማለት እችላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጉት ጫና እንዳለ ይታወቃል፤ ለመሆኑ እነዚህን ጫናዎች ለመቋቋም ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ነጋሽ፡- እየደረሱ ያሉ ጫናዎች መልከ ብዙ ናቸው፤ የውጭም የውስጥም ጫናዎች አሉ። አሁን ያለንበት ጊዜ ከምንም በላይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በያለንበት መስክ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን። ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን እስከሆነች ድረስ የሚደረገው መስዋዕትነትም አገር ለማሻገር እንጂ የአንድን አካል ፍላጎት ለማሟላት እንዳልሆነ መረዳቱ ተገቢ ነው። የምናደርገው ርብርብ የሁላችንን ፍላጎት የሆነችውን ኢትዮጵያ ወደፊት ለማስቀጠል የሚደረግ ነውና ከውስጥም ከውጪም የሚሰነዘርብን ጥቃት በጋራ ከቆምን መመከት እንችላለን። አሁንም እስካሁን በመጣንበት ምናልባትም በዚህ በሁለትና ሶስት ዓመት ውስጥም መልከ ብዙ ባህሪ ያላቸው ጥቃቶች ቢደርሱብንም ጸንተን ቆመናልና ይህ ጽናታችን ከጠነከረና አንድነታችን ከበረታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በያለበት በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት ከቻለ አሁን እየደረሰብን ያለው ፈተና ይቅርና በእጥፍ ሊፈትነን የሚችል ፈተና እንኳ ቢመጣ መቋቋም የምንችል ህዝቦች መሆናችን አያጠያይቅም።
ለዚህ ደግሞ እያንዳንዳችን በመንግስትም ሆነ ከመንግስትም መዋቅር ውጪ ያለን ኢትዮጵያውያን አገርን ከብተና ለማዳን በሚደረገው ጥረት ውስጥ በጋራ እንቆማለን። የሚደረጉ ማናቸውንም ድጋፎችን በተለይ የመከላከያ ኃይላችን በማጠናከር እና ከዚህ ባሻገር ደግሞ በልማት ስራዎች በመሳተፍ በተለይ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት መቀነስ የሚያስችል የልማት ስራዎች ላይ ግብርናውን በማዘመንና ቀንና ሌሊት በመስራት የውጪ እጅ የምንመለከትበትን እና የምንለምንበትን የምናስቆም ከሆነ ከገባንበት ችግር በቀላሉ ልንወጣና ልንሻገር እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- የደቡብ ምዕራብ ኢትጵያ ክልል ከሚታወቅባቸው ሃብቶች ውስጥ አንዱ እርስዎም እንደጠቀሱት የቱሪዝም ሃብት ምንጭ መሆኑ ነው፤ ለመሆኑ ይህን ለማሳደግና ክልሉም ሆነ አገር ከዚህ ዘርፍ እንዲጠቀም ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር ነጋሽ፡- በክልላችን በርካታ የቱሪስት መስህብ አለ። መስህቡን ማሳደግ የሚቻለው ግን ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ነው። ለምሳሌ አንዱ ከመንገድ ጋር በተያያዘ መፈታት ያለበት ነው። እንዲሁም ቱሪስቶች ሲመጡ ሊያርፉባቸው የሚያስችላቸውን ስፍራና የአካባቢውን ወግና ባህል ሳይለቅ ቱሪስቶች ከሚመገቡባቸው ጀምሮ ያለውን ቁስ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል።
ሌላው የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ቱር ጋይድ፣ የሰለጠኑ የቱሪስት መሪዎች የተለመዱ አይደሉምና እነዛ ማጠናከር፤ ከዛ ባለፈ ደግሞ ወደ አካባቢው የሚመጣ እንግዳ ያለምንም ስጋት ቆይቶ መሄድ እንዲችል ማድረግ ይጠይቃልና እነዚህን ማድረግ ከቻልን ያሉንን ሀብቶች በቀላሉ ለህዝብ አገልግሎት ማልማት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በክልሉ የፖለቲካ ጥያቄዎች ቢመለሱም የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ግን ገና ብዙ ጥረት ይጠይቃልና ከዚህ አንጻር ያቀዳችሁት ካለ ቢገልጹልን?
ዶክተር ነጋሽ፡- እንዳልሽው ነው፤ የፖለቲካ ጥያቄ ምላሽ ቢያገኝም፤ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ፍትሃዊ የመልማትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎች የመፍታት ጉዳይ ነው ሊሰራበት የተገባው። ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅምን መፍጠር ይጠይቃል። የፖለቲካ ጥያቄውን መልሰናል ብቻ ብለን ዝም ብንል ህዝባችን የሚቀበለውም የሚሸከመውም አይደለም።
እነዚህን ጥያቄዎች ለመምፍታት አሁን ባለንበት ደረጃ እውነቱን ለመናገር ክልላችን የተነሳው ከዜሮ ነው። ከዚህም የተነሳ ብዙ ሀብት አልፈጠረም። ነገር ግን ሀብትን የመፍጠር ተስፋ አለው። ስለሆነም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል በጀት ሊኖረው ይገባል። የበጀት አቅማችን ደግሞ ውስን ነው፤ የአጭር ጊዜ እቅዳችን የራሳችንን የውስጥ ገቢ አቅም ማሳደግ ነው። ሌላው አማራጭ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ሂደትን ወደክልላችን በመሳብ ኢንቨስትመንቱ ሀብትም የስራ እድልም እንዲፈጠር የማድረግ ስራ መስራትን ይጠይቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጪያችንን መቀነስ አለብን። በዚህ አግባብ በክልላችን ያገኘነው የዘንድሮ በጀት 60 በመቶውን ያዞርነው ወደልማት ነው። ለደመወዝና ለስራ ማስኬጃ ያደረግነው 40 በመቶውን ብቻ ነው። ስለሆነም ወጪያችንን እየቀነስን ስንሄድ ለልማቱም የምናተርፈው ሀብት ይኖራል። በመጨረሻ ያየዝነው ጉዳይ ሌሎች እህት ወንድም የሆኑ ክልሎች እንዲያግዙን እንዲሁም የፌዴራልም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶች እንዲያግዙን ይህንን አዲስ ክልል ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል።
ያለን በጀት ውስን እንደመሆኑ ሁሉንም ነገር የጀመርነው ከዜሮ ነው፤ ምንም አይነት ማረፊያ ህንጻ የለንም። የምንኖረው ተከራይተን ነው። የተሽከርካሪም እጥረት አለብን። እነዚህን መሰል ችግሮች ስላለብን በዚህ ዓመት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እናዘጋጃለን። በመሆኑም ሁሉም የክልሉ ወዳጅ የሆኑ በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ እጃቸውን እንዲዘረጉልን እንጠይቃለን።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ኢትዮጵያን ወደብልጽግና ለማሻገር ክልሉ ምን ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው፤ በተለይ ሰላምን ከማረጋገጥ አንጻር ምን እየሰራ ነው?
ዶክተር ነጋሽ፡- ትልቁ መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው። ክልላችን በዚህ በብልጽግና ጉዞ ውስጥ አስተዋጽአችን ትልቁና ቅድሚያ የምንሰጠው ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ነው። ለአገርና ለህዝቦች አንድነት ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜም ዋጋ ስንከፍል የመጣንና አሁንም አለንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አቅማችን በፈቀደው በየትኛውም መስክ ቀዳሚ ሆነን መሰለፍ ነው። ከዚሀ ጎን ለጎን ክልላችን በግብርናው ዘርፍ በማሩና በቅመማቅመሙ ልቀን ለመውጣት እንሰራለን። በማዕድን ዘርፍ ላይ ያለንን የወርቅና የድንጋይ ከሰል ምርት ላይ የሚደረገውን ህገ ወጥነት በመግታት ብሎም ዘርፉን በማዘመን አስተዋጽዖ እንዲያበርክት ስራ እንሰራለን። በዚህም የብልጽግና ጉዞ እንደግፋለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከሲዳማ ክልል የወሰዳችሁት ተሞክሮ ይኖር ይሆን?
ዶክተር ነጋሽ፡- አይደለም ከሲዳማ ቀርቶ ከነባሮቹ ሁሉም ክልሎች ተሞክሮ ወስደናል። አንዱን ብቻ ብጠቅስልሽ ሁሉም ክልሎች ተቋማቱ ያሉት በአንዱ በዋና ከተማ ብቻ ነው። ከዚህ የተነሳ የየክልሎቹ ሌሎች ከተሞች በአንዱ ልክ ማደግ አልሆነላቸውም። ከዚህም የተነሳ የሰውም ፍልሰት ወዳደገው ከተማ በመሆኑ የየክልል ዋና ከተሞች ታጭቀዋል። ይህ ሌሎቹ ከተሞች እንዳያድጉ የሚያደርግ በመሆኑ ስጋት ከመፍጠር ውጪ የጠቀመውን ነገር ብዙም አይታዪም። ስለዚህ ከዚህ ትምህርት በውሰድ የከተማ ብዝሃነት እንዲኖረን ለማድረግ እንድንወስን አስችሎናል። ይህ ተሞክሮ ደግሞ የሲውዘርላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የናይጄሪያም ነው። ስለሆነም እንዲያውም አንድ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሶስትና አራት አዲስ አበባ እንዲኖርን ለማድረግ መስራት ያስፈልጋል። ስለዚህም እኛም አንድ ቦንጋ ብቻ ሳይሆን ሚዛንም፣ ታርጫም ቴፒም ከተማ ናቸውና እናሳድጋቸዋለን። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎቹም ከተሞቻችን ማደግ አለባቸው በሚል የህግ አግባብ እያዘጋጀን ነውና ትልቅ ተሞክሮ ነው ያገኘነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ጊዜ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ነጋሽ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም