
– የኦሮሚያ ክልል ለአብርሆት ከ20 ሺህ በላይ መጻሕፍትን አበረከተ
አዲስ አበባ፡- አንድ አብርኾት ቤተመፃሕፍት ብቻ ሳይሆን ብዙ አብርኾቶች ያስፈልጉናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
“አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ“ በሚል መሪ ሃሳብ መጻሕፍት ለማሰባሰብ የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተከትሎ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ትናንትና ከ20 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርኾቶች አበርክቷል።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለኢትዮጵያ አንድ አብርኾት ብቻ ሳይሆን ሌሎች እሱን የሚመሳስሉ ትልልቅ ቤተመጻህፍትም ያስፈልጓታል ብለዋል፡፡
አብርኾት የኢትዮጵያ ብልፅግና በዕውቀት በዳበረ ትውልድ እንዲሳካ የመጻሕፍት ልገሳ መርሐግብሮች በየዕለቱ እየተከናወኑ ይገኛል
በማሰብ የተገነባ ቤተመጻሕፍት ነው፤ የቤተ መጻሕፍቱ ዋናው አላማ ኢትዮጵያ በዕውቀት ብርሃን ይበልጥ እንድትጠቀም ማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩም የአብርኾትን አላማ ይዞ በሁሉም ክፈለከተሞች ቤተመጻሕፍቶችን የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በቅርቡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ የተሰራው ቤተመጻሕፍት ለዚህ ሥራ ማሳያ ነው፤ ጅማሮው በሌሎች ክፍለከተሞችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
እንደአብርኾት ያሉ ትውልድ የሚታነጽባቸውን ቤተመጻሕፍት በግብዓት ማጠናከር ደግሞ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፤ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፤ መጻሕፍት ቤቱን በውጭ አገር እትሞት ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ መጻሕፍትም ጭምር መሙላት ያስፈልጋል። ለዚህ ተግባር መሳካት የአገር በቀል ማንነትን መሰረት ያደረጉና ባህላችንን ይበልጥ ለመረዳት የሚረዱ እትሞችን ማምጣት ያስፈልጋል።
የኦሮሚያ ክልል ለአብርኾት ያበረከታቸውን ከ20 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ያስረከቡት በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱላኪም ሙሉ በበኩላቸው፤ በኦሮሚያ የዜግነት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ከሁሉም አካባቢዎች የመጻሕፍት ማሰባሰብ ሲካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።
መፃሕፍቶቹም የተለያየ ይዘት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን ባህላቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ የንባብ ባህል ሊዳብር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ክልሉ የኦሮሞ ህዝብ ታሪክን የሚዳስሱ፣ ልብወለድ መጻሕፍት፣ የስነልቦና እንዲሁም ለመማሪያ የሚሆኑ 20ሺህ በላይ መጻሕፍትን ማበርከቱን ጠቁመዋል።
የንባብ ባህልና ልማድ ዝቅተኛ እየሆነ መጥቷል ያሉት አቶ አብዱላኪም፤ ክልሉ የንባብ ባህልን በማዳበር ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
መሰል ቤተመጻሕፍቶች የንባብ ባህልን ለማሻሻል የማይተካ ሚና አላቸው፤ በዚህ ረገድ መምህራንና ቤተሰቦች ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይም ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ከ500 መቶ በላይ መጻሕፍት፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት 567 መጻሕፍት፣ የኢትዮጵያ ጥናት ምርምር ተቋም 335 መጻሕፍት ትናንትና ለአብርኾት አበርክተዋል። በተጨማሪ ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት ከመምህራን የተማሪ ወላጆች ያሰባሰባቸውን 1ሺህ 651 መጻሕፍት ለአብርኾት ቤተመጻሕፍት ለግሷል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23 ቀን 2014 ዓ.ም