በአሜሪካዋ ፍሎሪዳ ግዛት አብራሪው መታመሙን ተከትሎ አንዲት አውሮፕላንን ያለምንም ችግር ማሳረፍ የቻለው ተሳፋሪ በበርካታ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኗል። ማንነቱን ለማጣራትም የዜና ወኪሎች ፍለጋ ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል።
ማንነቱ ይፋ ያልተደረገው ይህ ተሳፋሪ በአየር ማረፊያው ከሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ጋር ያደረገው የድምጽ ልውውጥ እንደሚያሳየው ምንም አይነት አውሮፕላን የማብረር ልምድ የለውም። በድምጽ ቅጂው ላይ አውሮፕላኑን እንዴት ማሳረፍና ማቆም እንዳለበት እንደማያውቅ ሲናገር ይሰማል።
አዲስ አውሮፕላን አብራሪዎችን በማለማመድ የሚታወቅ አንድ የበረራ ተቆጣጣሪ ተሳፋሪው አውሮፕላኑን እንዲቆጣጠርና በሰላም እንዲያሳርፍ ሲረዳው እንደነበርም ተገልጿል። ይህ ክስተት ያጋጠመው ባለፍነው ማክሰኞ ዕለት ፓልም ቢች ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ውስጥ ነው።ተሳፋሪው አውሮፕላኑን በሰላም ካሳረፈ በኋላ ከበረራ ተቆጣጣሪው ጋር መገናኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ተቃቅፈውም ነበር ተብሏል።
“በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት። የአውሮፕላን አብራሪው ጥሩ ጤንነት ላይ አይገኝም። እራሱን ሳይስት አይቀርም” ሲል ይደመጣል በሬዲዮ ባስተላለፈው መልዕክት።በሬዲዮ አማካይነት አውሮፕላኗ በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የተጠየቀው ተሳፋሪ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለና የፍሎሪዳ የባሕር ዳርቻን ከላይ እየተመለከተ እንደሆነ ተናግሯል።
“የአውሮፕላን ክንፎቹን አቅጣጫ አስተካክልና የባሕር ዳርቻውን ተከትለህ ወደ ሰሜን አልያም ወደ ደቡብ ዝም ብለህ አብርር። እኛ እናገኝሃለን” ሲል የበረራ ተቆጣጣሪው ነግሮት ነበር።አውሮፕላኗን ለማብረር የተገደደው ተሳፋሪ ደግሞ በምላሹ “የአቅጣጫ መቆጣጠሪያውን እንኳን ማብራት አልቻልኩም። እንዴት መቆጣጠር እንደምችል አላውቅም። አንዴት ማድረግ እንዳለብኝ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?” ሲል ይሰማል። አክሎም “አውሮፕላኑን እንዴት ማቆም እንዳለብኝ አላውቅም። ምንም የማውቀው ነገር የለም፤ እርዱኝ”ብሏል በሬድዮ ባስተላለፈው መልዕክት።
ሮበርት ሞርጋን የተባለው የበረራ ተቆጣጣሪ ይህ ክስተት ባጋጠመበት ጊዜ እረፍት ላይ የነበረ ሲሆን፣ ባልደረባው ስለሁኔታው ሲነገረው በፍጥነት ወደ ሥራ ቦታው ተመልሷል።”አውሮፕላኗ ከሌሎች የተለየች እንዳልሆነች አውቃለሁ። ማድረግ የነበረብኝ አብራሪው ሳይደናገጥ ተረጋግቶ አውሮፕላኑን እንዲያበር መርዳት ነው። በሬዲዮ በኩል ኃይል እንዴት መቀነስ እንዳለበትና ወደ መሬት እንዲወርድ እንዲሁም እንዲያሳርፍ ረድቼዋለሁ” ብሏል።
በስተመጨረሻም አብራሪው አውሮፕላኗን በሰላም ማሳረፉን ሲነግረው በጣም እንደተደሰተና ማመን እንዳቃተው ለመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል።ደፋሩ ተሳፋሪ አውሮፕላኗን በሰላም ካሳረፈ በኋላ ሮበርት ሞርጋን ወደ አውሮፕላን ማሳረፊያው በመሄድ እንዳቀፈውና ፎቶ አብረው እንደተነሱም ገልጿል። ነገር ግን በግርግር ውስጥ ስለነበረ ስሙን እንዳልሰማ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጿል።
“ልክ በሰላም ሳገኘው እምባዬ መጥቶ ነበር። በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለፍነው። አብራሪው ምን ያክል ተጨንቆ ይሆን የሚለውን ሳስብ በእርጋታው በጣም ነው የተገረምኩት” ብሏል ከሲኤንኤን ጋር በነበረው ቆይታ።የአሜሪካ የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር በበኩሉ ያለምንም አደጋ ማረፍ የቻለችው አውሮፕላን የግል እንደሆነችና ምንም አይነት አሳሳቢ ጉዳት አለመድረሱን ገልጿል።
በማብረር ላይ ሳለ የጤና እክል የገጠመው ካፕቴን አውሮፕላኗ በሰላም ካረፈች በኋላ ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014