በብዙዎች በተለየ መልኩ ተወዳጅነት ያገኘውና አዲስ በሆነ አቀራረብና ጠንካራ ሀሳብ መነጋገሪያ የነበረው እረኛዬ ድራማ በዛሬ የዘመን ጥበብ አምዳችን ልንመለከተው ወደድን::
ድራማው ላይ ካየነው ከፍ ያለ ኪናዊ ልህቀት አንዱ አስገራሚ የነበረው የትወና ብቃት ነው:: የአተዋወን ብቃት ለባለሙያ ብቻ ይመስለናል፤ ዳሩ ግን ለታዳሚም ይታየዋል:: በብዙ ፊልሞችና ድራማዎች ውስጥ ‹‹አርቲፊሻል›› የሆነ አተዋወን ማየት የተለመደ ነው:: ‹‹አርቲፊሻል›› አተዋወን ማለት ከነባራዊው ዓለም የራቀ ማለት ነው::
ምንም እንኳን የፈጠራ ሥራ መሆኑ ቢታወቅም በገሃዱ ዓለም የማይታይ አይነት የተጋነነ አተዋወን ማየት አሰልቺ ያደርገዋል:: የተጋነነ አተዋወን ማለት፤ ኃዘንም ሆነ ደስታን፤ ሳቅም ሆነ ለቅሶን በገሃዱ ዓለም ከሚታየው እውነታ አጋኖ ማሳየት ማለት ነው::
በእረኛዬ ድራማ ውስጥ ግን ‹‹አርቲፊሻል›› አተዋወን አልነበረም:: ድራማ መሆኑን የማያውቅ ሰው አንዲት ትዕይንት (ሲን) ተቆርጣ ቢያገኝ ምናልባትም ድራማ ላይመስለው ይችላል፤ እውነተኛ ክስተት ነው የሚመስለው:: ምክንያቱም አስመስለው ሳይሆን ሆነው ነው የሚተውኑት::
የድራማው ዋና ገጸ ባህሪ እማ ቸርነት የምታሳየው እያንዳንዷ የአተዋወን ትዕይንት ገጠር ውስጥ ያሉ እናቶች የሚያደርጉትን ነው:: ምንም እንኳን የምትጠቀማቸው ቃላትና ሀሳቦች የደራሲ ቢሆኑም አተዋወኑ ግን ‹‹ስክሪፕት›› ተጠንቶ የሚተወን ሳይሆን እልም ያለ ገጠር ውስጥ ያሉ እናት የሚያደርጉት ነው::
ከምንም በላይ ግን ተወዳጅ ያደረገው የድራማው ይዘት ነው:: በድራማው ውስጥ የማኅበረሰብ ፍልስፍና ይታያል:: ፖለቲካን፣ ባህልን፣ ትምህርትን፣ ፍልስፍናን፣ ስነ ልቦናን… ያሳየናል:: በድራማው ውስጥ የምናየው ተፈጥሮን ነው፤ የአገር ቤት መልከዓ ምድርን ነው:: የሃገረሰብ ስነ ቃልና ጥበብ ነው::
የሚገርመው ነገር ደግሞ የድራማው ደራሲዎች ሦስቱም አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ መሆናቸው ነው:: በአርትስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው ‹‹በነገራችን ላይ›› በተሰኘው የጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ ፕሮግራም ላይ ሦስቱ ሴቶች ቀርበው ነበር:: አዲስ አበባ ተወልደው አድገው እንዴት ያንን የገጠር ሕይወት በዚያ ልክ ተረድተው እንዳቀረቡት ተጠይቀዋል:: ደራሲዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ በአያቶቻቸውና በሌሎች የቤተሰብ አባላት በኩል የአገር ቤትን ወግ ያውቁታል:: እነርሱ ሲሄዱም ሆነ ዘመዶቻቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የገጠሩን ማኅበረሰብ ስነ ልቦና በጥልቀት ያስተውላሉ::
ከዚህ በተጨማሪ ግን ድራማውን የሠሩት አዲስ አበባ ቁጭ ብለው፣ አልጋቸው ላይ ተኝተው፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመኪና እየተንሸራሸሩ አይደለም:: በቀጥታ የገጠሩ ማኅበረሰብ ውስጥ ገብተው ለዓመታት አብረው ቆይተው ነው:: የገጠሩ ሕዝብ የሚበላውን እየበሉ፣ የሚጠጣውን እየጠጡ፣ የሚተኛበት ላይ እየተኙ… በአጠቃላይ ኑሮውን ኖረው ነው:: በጋ ክረምቱን አብረው አሳልፈው ነው:: ጋራ ሸንተረሩን ወጥተው ወርደው ነው:: ይህ የሆነው ለቀረጻው ሳይሆን ድርሰቱን ለመጻፍ ነው::
ደራሲዎቹ ደግሞ ቅድስት ይልማ፣ አዜብ ወርቁ እና ቤዛ ኃይሉ ናቸው:: ሦስቱም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ውስጥ አሉ የተባሉና በተወዳጅ ሥራዎች የሚታወቁ ናቸው:: በተለይም የድራማው ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ በረቡኒ ፊልም በብዙዎች ቀልብ ውስጥ ገብታለች:: ረቡኒ ከምርጥ ፊልሞች ግንባር ቀደም ፊልም ሲሆን አገር በቀል እውቀትን (በተለይም ሳይንስን) ያሳየ ፊልም ነው::
አዜብ ወርቁም በብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎችና በጋዜጠኝነት ሙያ ትታወቃለች፤ ቤዛ ኃይሉም በጥበብ ውስጥ ቆይታለች:: የቤዛ ኃይሉ ሌላኛው አስገራሚ ነገር፤ በድራማው ውስጥ ያሉ የእረኛ ግጥሞችን የጻፈቻቸው እሷ ናት መባሉ ነው:: ቤዛ ከልጅነቷ ጀምሮ አሜሪካ ነው የኖረች:: አንዳንዶች ለጥቂት ዓመታት አሜሪካ ኖረው የአማርኛ ቃላት ሲጠፉባቸው እናያለን፤ ቤዛ ግን ገጠር ያለው ማኅበረሰብ የረሳቸውን የእረኛ ግጥሞች ሁሉ ጽፋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖረው ሁሉ አስተምራለች::
በእነዚህ ደራሲዎችና አዘጋጆች ብቃት ድራማው ተወዳጅ ሆነ:: ዘወትር ሰኞ፣ ረቡዕና አርብ ምሽት ሦስት ሰዓት በአርትስ ቴሌቪዥን ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ድራማ ነበር:: ድራማው ከተጠናቀቀ ወራት ቢቆጠሩም በቀጣይ ክፍሎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚመለስ አዘጋጆቹ ተናግረዋል::
ይህን ድራማ ያነሳንበት ምክንያት ከኪነ ጥበብነት አልፎ እስከ ትልልቅ ተቋማት ድረስ አጀንዳ ስለሆነ እና ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውይይት ስለተደረገበት ነው::
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል በድራማው ላይ ሙያዊ የውይይት መድረክ አካሒዷል። በውይይቱ ላይም፤ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት (ፎክሎር) መምህር የሆኑት ዶክተር ሰሎሞን ተሾመ ከፎክሎር አንጻር ድራማውን የቃኙባቸውን ዕይታዎች አቅርበዋል::
ዶክተር ሰለሞን ባቀረቡት ሙያዊ አስተያየት፤ እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የታሪክ አወቃቀሩ፣ የገፀባህሪዎቹ አመራረጥ፣ የትወና ብቃት፣ የቦታ አመራረጥ፣ ዳይሬክቲንግ፣ ቀረፃው የሙያውን ደረጃ ከፍ ያደረገና የኢትዮጵያን የፊልም ገፅታ የቀየረ ነው::
የድራማው አዘጋጅና ደራሲ ቅድስት ይልማ፤ ደራሲዎቹ አዜብ ወርቁ እና ቤዛ ኃይሉ በመድረክ ላይ ተሰይመው ስለድራማው አጠቃላይ ይዘት እና ቀጣይ ዕቅዳቸውን ለታዳሚያን አካፍለዋል። በዚህ ወቅት ድራማው የሃገራችንን ባህል፣ ሥነልቦና፣ ትውፊቶችንና እሴቶችን የተላበሰና ሳቢ እንዲሆን በማድረግ ትውልድን ከባህል ብረዛና ከማንነት ቀውስ ለመታደግ ታልሞ እንደተሠራ ገልጸዋል።
በድራማው በትወናና በሌሎች ሥራዎች የተሳተፉ አካላት ሐሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን፤ በውይይቱ የተጋበዙ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተማሪዎችም ገለጻዎቹን ተከትሎ በተካሔደው ውይይት ላይ ተሳትፈዋል::
ተሳታፊዎች ከሰጡት አስተያየት መረዳት የሚቻለው፤ ድራማው የበርካታ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበ፣ በትርጉም ከሚቀርቡ የውጭ አገር ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ቀልብን ወደ ሃገርኛ የመለሰ ተከታታይ ድራማ ነው:: ድራማው ከሰፊ ማኅበራዊ ጠቀሜታው ባሻገር ጉልህ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለውም የተናገሩ ታዳሚያን ነበሩ::
በውይይት መድረኩ ‹‹ጉንጉን›› እና ‹‹የወዲያነሽ’›› በተሰኙ ተወዳጅ የልቦለድ ድርሰቶቻቸው የሚታወቁት እና በዚሁ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ አብዬ በቃሉ ሆነው በመተወን ተወዳጅነትን ያተረፉት ደራሲ ኃይለ መለኮት መዋዕል እና በእማማ ቸርነት የተወከለች ተዋናይት ድርብወርቅ ሰይፉ በድራማው ላይ ስለነበራቸው ተሳትፎ አብራርተዋል።
ወደ ዶክተር ሰለሞን እንመለስ:: የባህል ጥናት መምህሩ ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት፤ በድራማው ውስጥ ሃገርና ሕዝብ ነው የተወከለው:: የአብነት ትምህርት ቤቶች እውቀትን፣ አማኝነትን፣ አብሮነትን፣ ያሳያል:: የማኅበረሰብን ታማኝነትና ቅንነት ያሳያል:: በእማማ ቸርነት የተወከለው ይሄው ነው::
ድራማው የሀሳብ ግጭትም ያለበት ነው:: የአካባቢ ባለቤትነትና ባይተዋርነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ተስፋና ተስፋቢስነት… የመሳሰሉትን የያዘ ነው:: የማኅበረሰብን የፖለቲካ አተያይም የሚያሳይ ነው::
ሦስቱም ደራሲዎች ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያዎች መልስ ሰጥተዋል:: ከተሰጡ አስተያየቶች ተነስተውም ተጨማሪ አስተያየቶችን ሰጥተዋል:: እረኛዬ የሚለው ቃል የታሰበውም ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው›› ከሚለው ከመዝሙር 23 የመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ መሆኑን ተናግረዋል:: ሀሳቡን ቅድስት ይልማ አሰበችው:: ቅድስት አዜብን እና ቤዛን ጠየቀቻቸው:: ቅድስት እንደምትለው፤ ሁለቱን ሴቶች የመረጠችው በሥራዎቻቸው ስለምታውቃቸውና ከእነርሱ ጋር ቢሠራ ውጤታማ እንደምትሆን አምና ነው::
በመድረኩ ላይ ታዳሚውንም ሦስቱን ደራሲዎችም ያሳቀ አንድ ጥያቄ ተነስቶ ነበር:: ‹‹የድራማው ደራሲዎች ሦስታችሁም ሴቶች ናችሁ:: ሦስታችሁም ወንድ ሆናችሁ ቢሆን ኖሮ ምን ይጎለው ነበር?›› በሚል ተጠየቁ:: አዜብ ‹‹ሦስታችንም ወንድ ሆነን ስላላየነው ምን እንደሚጎል አናውቅም›› የሚል ታዳሚውን ፈገግ ያሰኘ መልስ ከሰጠች በኋላ ጥሩ ማብራሪያ ሰጥታለች::
የአዜብ ማብራሪያ ብዙ ነገሮችን ልብ ብለን እንድናስተውል ያደርጋል:: ሦስቱም ሴት መሆናቸው ጥሩ አጋጣሚ የሆነው የሴቶችን ኃላፊነቶች በነፃነት እንዲያወሩና እንዲወያዩ ዕድል መስጠቱ ነው:: ለምሳሌ ወንድ ባለበት ቦታ፤ ስለልጆች፣ ስለቤት ውስጥ ጉዳዮች ሴቶች ብቻቸውን ሆነው የሚያወሩትን ያህል አይወራም:: የእናትነት፣ የሚስትነት ኃላፊነቶች በነፃነት ይወራሉ፣ በነፃነት ይሰራሉ:: ሦስቱም ሴቶች መሆናቸው ነገሮቻቸው የጋራ እንዲሆኑ አድርጓል::
በሌላ በኩል ‹‹ድሮስ በሴት ተሠርቶ›› የሚል ወቀሳ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት መሆኑን አዜብ ተናግራለች:: ሴቶች አይስማሙም፣ አብረው አይሠሩም የሚለውን አስተሳሰብ ለማስቀየር በጥንቃቄ ተሰርቷል::
አብሮነታቸውና የሀሳብ ውህደታቸውን ቅድስት ስትገልጸው ደግሞ፤ የትኛው ሀሳብ የማንኛቸው እንደሆነ እንኳን እስከሚጠፋ ድረስ ውህደት መኖሩን ተናግራለች::
ቤዛ በበኩሏ፤ ሴት መሆናቸው የጨመረው ነገር የገጸ ባህሪያት አሳሳል ላይ ነው:: በብዙ ፊልሞችና ድራማዎች የተለመደው ቆንጆ ሴት መርጦ ‹‹ካስት›› ማድረግ ነው:: ብቃት ይኑራትም አይኑራትም አካላዊ ቁንጅና እንደ መስፈርት ሲያገለግል ቆይቷል:: በዚህ ድራማ ግን ሦስቱም ሴት በመሆናቸው የሄዱት ወደ እናቶቻቸውና አያቶቻቸው ነው:: መስፈርቱ ቁንጅና ሳይሆን ለገጸ ባህሪው ባላቸው ብቃት ነው:: እማማ ቸርነትን ‹‹አቤት እግሯ፣ አቤት ምኗ…›› የሚል አይኖርም ስትል አብራርታለች::
ሴት የመሆናቸው ሌላኛው ጠቀሜታ ነገሮች በትኩረት እንዲታዩ ማድረጉ ነው:: ሴቶች በተፈጥሮ ተረጋግቶ የማስተዋል ችሎታ እንዳላቸው ይነገራል፤ ይህ ተፈጥሯዊም ማኅበራዊም ተሰጥቷቸው ነው:: ስለዚህ ለዚህ ድራማ መወደድና በጥራት መሠራት ሦስቱም ሴት መሆናቸውም ከፍተኛ ድርሻ ነበረው::
ቀደም ሲል መግቢያው አካባቢ እንዳልኩት የእረኛዬ ድራማ አንዱ ተወዳጅነት የማኅበረሰብን ፍልስፍና በቀጥታ የሚታይ ያህል ማሳየቱ ነው:: ልብ ብሎ ላስተዋለው ሰው ስነ ልቦናቸው ሳይቀር ነው የገባቸው::
ለምሳሌ፤ እማ ቸርነት ሲገረሙ፣ ሲመሰጡ፣ ሲያዝኑ… የትወና ሳይሆን አንዲት የገጠር እናት እንደማየት ማለት ነው:: ምንም እንኳን በተንቀሳቃሽ ምስል ሲያዩት ቢሆንም የሚያስታውቅ፤ አንዲትን ትዕይንት በጽሑፍ ለመግለጽ እንሞክር::
እማ ቸርነት እያወሩ ውጭ ውጩን ያያሉ:: ከአጠገባቸው የምታወራቸው ሴትዮ ሀሳብ አልጣማቸውም:: አልጣመኝም ማለት ደግሞ በባህላቸው ሞራላቸው አይፈቅድም:: እያዳመጡ መስለው፤ ውጭ ላይ ያሉ ዶሮዎችን ‹‹እሽ! ምን እንዲያው እነዚህ ዶሮዎች›› ይላሉ:: ዶሮዎች ያን ያህል አስቸግረው ሳይሆን ‹‹ወሬሽን ቀይሪ›› ላለማለት ነው::
በድራማው ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ያስገርም የነበረው ደግሞ አርቲስት ሳያት ደምሴ የምትተውነው የእናና ገጸ ባህሪ ነው:: እናና እረኛ ነች:: ለጥጃዋ፣ ለፍየሏ እንዴት እንደምትሆን ስሜቱን የሚያውቀው የእረኞችን ሕይወት የሚያውቅ ነው:: እረኛ ከሚጠብቃቸው ፍየሎች አንዷ ብትሞት ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል:: እናናም ልክ እንደዚያ ናት::
በአጠቃላይ ድራማው ማኅበረሰባዊ ፍልስፍና የሚታይበት ነው:: ይዘቱን አልነካነውም ማለት ይቻላል:: የማኅበረሰብ ባህልና ስነ ልቦና ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ይወሩበታል:: ሃገራዊ ምስቅልቅሎች በተምሳሌት ይነገሩበታል:: በተለይም ለከተሜው ነዋሪ ደግሞ የስነ ቃል ሀብት ምን ያህል ሀሳብን እንደሚገልጽ ያሳያል::
በኪነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ላሉ ሰዎች ከዚህ ድራማ መማር ያለባቸው ስለሚሠሩት ነገር ጠንቅቆ ማወቅ፣ የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑ ሰዎች ጋር መገናኘትና በጥልቀት ማስተዋል እንዲሁም ይወክላል ያሉትን ማኅበረሰብ ቋንቋና ባህል፣ ስነ ልቦና ማወቅ እንዳለባቸው ነው:: እንዲህ አይነት ድራማዎችና ፊልሞች ከተሠሩ በጥበብ ዘርፉ ላይ የሚታየው ወቀሳ ቢያንስ ይቀንሳል ማለት ነው:: ተባባሪ አካላትም እንዲህ አይነት ሥራዎችን ሊደግፉ ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም