
አዲስ አበባ፡- በሚቀጥለው ሐምሌ ወር ተግባራዊ መደረግ ለሚጀመረው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አሰራር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ።
የታለመ የነዳጅ ድጎማና የዋጋ ማሻሻያን በተመለከተ ለሚዲያ ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ሰሞኑን በተዘጋጀ መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳስታወቁት ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳደር በሚል የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ተቋቁሞ ሲሰራም ቆይቷል፤ ዓላማውም በዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋ ላይ በሚከሰተው ጭማሪ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅ ገበያ ዋጋን ማረጋጋት ነው።
የሀገሪቱን ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የሕብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋና የዓለም አቀፉን ዋጋ በማጥበብ በኩል ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር የሚሄድ የዋጋ ማስተካከያ ሳይደረግ መቆየቱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፤ በዚህ የተነሳም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ እዳ በዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ ተከማችቶ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ነዳጅ ከዓለም ገበያ ከተገዛበት ዋጋ ከግማሽ በታች ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ሁኔታ ከጎረቤት ሀገሮች የነዳጅ ዋጋ አንጻር ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ የነዳጅ ህገወጥ ግብይትና ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በሥራ ላይ የቆየው ድጎማ ለሁሉም ተጠቃሚዎች ማለትም መደጎም ያለባቸውንና የሌለባቸውን ሳይለይ በእኩልነት ሲሰራበት እንደቆየ ጠቅሰው፣ ይህም ሁኔታ ኢፍትሃዊነት በስፋት ይታይበታል ብለዋል።
የዓለም ነዳጅ ዋጋን ያገናዘበ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ለተጠቃሚው በየወቅቱ ባለመተላለፉም የተነሳ እስከ መጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ድረስ 124 ቢሊዮን ብር እዳ ተመዝግቦ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
እስከ አሁን በህግ ወይም በአሰራር ሳይደገፍ የቆየው የነዳጅ ድጎማ በዓላማ የተገደበ አለመሆኑ፣ ተጠቃሚውን በውል ያልለየና ለብክነት የተዳረገ መሆኑን አብራርተው፣ አሰራሩን ፈትሾ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ አመልክተዋል። ለእዚህም በመንግሥት በኩል ጥልቅ ጥናት በማካሄድ አሰራሩን ለመቀየር የሚያስችል የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አሰራር ውሳኔ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኀሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም መጽደቁን ጠቅሰዋል።
በዚህም ውሳኔ መሰረት ቀድሞ ይሰራበት ከነበረው በተሻለ መልኩ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማው አነስተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና ለማቃለል እንደሚሰራም አስታውቀዋል። ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሚተገበረው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ሥርዓቱ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ሁለት ወራት የዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ በሚቀጥለው ሐምሌ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
ለዚህ ትግበራ ስኬታማነት መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ሀገራዊ እቅድ ወጥቶ ለትግበራ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። መገናኛ ብዙሃን በዚህ ረገድ ሚዛናዊ ዘገባዎችን በመስራት ኃላፊነታችሁን እንደምትወጡ አምናለሁ ሲሉም አስገንዝበዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ቱሳ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ሥርዓቱን መንግሥት ከዛሬ ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል ፤ ዋጋው ባለበት ይቀጥል ፤ ትንሽ እንታገስ፤ ይቺን ወር እንለፍ እያለ እንዳቆየው ጠቅሰው፣ አሁን ነገሮች አስቸጋሪ ሆነው ሲመጡ ወደ ትግበራ ለመግባት መወሰኑን አስታውቀዋል።
አሁን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ሲታይ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መተግበር ውስጥ እንደተገባም ጠቅሰው፣ ከዚህ የተሻለ ነገር ቢኖር እንዲህ አይነት ውሳኔ ውስጥ እንደማይገባም ነው ያስገነዘቡት።
በበጀት የተደገፈ፣ መንግሥት የሚከፍለው ድጎማ እንኳ ይቁም ቢባል ይህ ሰዓቱ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጫናው በማስገደዱና ሌላ አማራጭም ባለመኖሩ እንጂ ይህ ከድጎማ የሚወጣበት ትክክለኛ ወቅት አይደለም ሲሉም አስታውቀዋል።
ይህ ህዝብ ሌላውን ችግር ተጋግዞ ተመካክሮ እንደፈታ ሁሉ ድጎማውን ለማንሳት የተቀመጠውን መፍትሄም በእዚሁ መልኩ ለማለፍ የተቀመጠ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተወሰነ ማስተካከያ ካልተደረገ በእስከ አሁኑ መንገድ መቀጠልና ነዳጅ መግዛት እንደማይቻል አመልክተዋል።
ነዳጅ ድርጅት ነዳጅ ለመግዛት 124 ቢሊዮን ብር ለብሄራዊ ባንክ ከፍሎ ዶላር ለማግኘት ብር ከሌለ ነዳጅ ማምጣት አይቻልም፤ ብሩ መተካት አለበት ያሉት ነዳጁን የተጠቀሙ አካላት ብሩን መተካት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ለእዚህም ያለውን ፈተና ተቋቁመን የማይፈለግ መፍትሄ ትግበራ ውስጥ ገብተናል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ቁጥጥር ላይም መስራት እንደሚገባም አስታውቀዋል። ለትናንሽ ጥቅሞች ሲባል ሀገር የሚያፈርስ ህዝብን የሚጎዳ ነገር የሚፈጽሙ እንዳሉ ሁሉ፣ በዚያው ልክ በኃላፊነት የሚሰሩ አሉና እነሱን ይዞ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
ወደ ትግበራው ለመግባት ሁለት ወራት ጊዜ እንዳለም ጠቅሰው፣በእነዚህ ሁለት ወራት የሙያተኞች ስልጠናዎች እንደሚሰጡም አስታውቀዋል። ህዝቡን የማንቃት የማስተማር የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ፣ ሚዲያውን በመያዝ አመራሩንም ህዝቡንም ለማድረስ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
‹‹ሥራውን የሚመራ የሚኒስትሮች ካውንስል አለ፤ ቴክኒካል ኮሚቴም ተቋቁሟል፤ ሥራውን ለመጀመር አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ተገምግሞና የውሳኔ ሀሳብ ቀርቦ በመንግሥት ውሳኔ እንደሚተላለፍ ጠቁመዋል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሚያዝ 30 ቀን 2014 ዓ.ም