
አዲስ አበባ፡- የብረት አምራቾችን የጥሬ ዕቃ ችግር ለማቃለል ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከስሩ ካሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ግብዓት እንዲያገኙ ከስምምነት ላይ መደረሱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።
የማዕድን ሚኒስቴር ከብረት አምራቾች ጋር ባደረገው ውይይት የጥሬ ዕቃ ችግራቸውን ለመቀነስ ግብዓቱን ከመከላከያ ሚኒስቴርና በስሩ ካሉ ተቋምት ጋር በማስተሳሰር እንዲጠቀሙ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትናንትና አስታውቀዋል።
ለዓመታት ተከማችተው የቆዩ የወዳደቁ ብረቶችን ወደ ምርት መቀየር በአፋጣኝ ችግሩን ለማቃለል እንደሚረዳና ብረቶቹ ወደ አምራቾቹ በፍጥነት መቅረብ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል።
በዘላቂነት ደግሞ በሀገር ውስጥ የብረት ማዕድንን ለማውጣትና አምራቾች ጥሬ ግብአቱን ከሀገር ውስጥ ማግኘት እንዲችሉ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገፃቸው አሳውቀዋል።
በተያያዘ ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማዕድን ጉባኤ ላይ የማዕድን ሀብቷን በሰፊው ለማስተዋወቅ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ኢንጂነር ታከለ ዑማ ገልጸዋል፡፡
ኢንጂነር ታከለ ዑማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት፤ ከቀናት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው “Investing in African Mining (INDABA)” የማዕድን ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በሰፊው ለማስተዋወቅ ዝግጅቷን አጠናቃለች።
ጉባዔው በአፍሪካ ማዕድን ካፒታላይዜሽንና ተያያዥ የማዕድን ልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የማዕድን ኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል።
ጉባዔው ለኢንዱስትሪው የወደፊት ርምጃ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው የማዕድን ሚኒስቴር ገልጾ፤ በማዕድን ዘርፉ አዳዲስ የልማት ስልቶችን፣ የንግድ ግንኙነቶችና የሌሎች አገራት ልምዶች የሚቀርቡበት መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በተያያዘ ኢንጂነር ታከለ ከአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኔብሌት ጋር በጉባኤው ላይ በተናጠል የአውስትራሊያ የማዕድን ኩባንያዎች የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት መስማማታቸውን ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ በሰፊው በማዕድን የወጪ ንግድን፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ማዕድናት እንዲሁም የኃይል ማዕድናትን በማስተዋወቅ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድን ለማሳካት ግዙፍ የማዕድን ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለመሳብ እንደምትሰራም ነው የገለጹት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀው “Investing in African Mining (INDABA)” የማዕድን ጉባኤ ከግንቦት አንድ ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ ይካሄዳል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲሰ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም