
አዲስ አበባ፡- ከቡና፣ ከሻይ፣ ከቅመማ ቅመምና ከአበባ ምርት እንዲሁም ከሌሎች የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ አበረታች መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትን የዘጠኝ ወር ሪፖርት በትላንትናው ዕለት በገመገመበት ወቅት በሰጠው ማጠቃለያ እንደገለጸው፤ በግብርናው ዘርፍ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ የሚያበረታታ ነው፡፡
በግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ሆነው የተደራጁት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን እንደ ቅደም ተከተላቸው በዶክተር አዱኛ ደበላ እና በኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀማቸውን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል::
ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ከአዳመጠ በኋላ ቀደም ብሎ ካደረገው የመስክ ጉብኝት ጋር በማጣመር የየተቋማቱን ጠንካራና ደካማ ሥራዎች ለይቶ አሳይቷል:: በሁለቱ ተቋማት በኩል የታዩ ጠንካራ ጎኖች የሚበረታቱ መሆኑንና ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸውን በዝርዝር አስቀምጧል::
የግብርና ምርቶች በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት መቻላቸው የተቋማቱ ድምር ውጤት መሆኑንና ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የታየው ለውጥ አበረታች ነው ብሏል::
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን ላሌ በማጠቃለያው እንደገለፁት፤ በምግብ ራስን መቻል እና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶችን ማምረት ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠ ኃላፊነት ነው:: እንዲሁም የኢኮኖሚ ሽግግር በሀገሪቱ ማምጣት እና የሥራ ዕድል ፈጠራውም በግብርና ዘርፉ ይፈጠራሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው::
በቋሚ ኮሚቴው ግምገማ መሰረት ግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ተጠሪ ተቋሙ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የውጭ ምንዛሪ ለሀገሪቱ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል:: በዘጠኝ ወራት ውስጥ በቡና ምርት ብቻ ዓምና ከነበረው 72 ነጥብ 7 በመቶ የውጭ ምንዛሪውን ማሳደጉ እጅግ በጣም ውጤታማ ሥራ መሆኑ ተነስቷል:: በዚህም የቡና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ 894 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማስገኘት በመቻሉ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል::
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዳሉት፤ በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም በጋራ ሲታይ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 525 ነጥብ 13 ሚሊዮን ዶላር ወደ 907 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት መቻሉ ትልቅ እምርታ ነው::
በአጠቃላይ እንደ ሀገር ሲገመገም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል::
በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ጥቂት የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርት መዳረሻ ወደ 33 ሀገራት ማሳደጉ በጥንካሬ ተነስቷል::
በሌላ በኩል የአንድ ሄክታር አማካይ የቡና ምርት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሆንም ቋሚ ኮሚቴው ወርዶ ባረጋገጠ ጊዜ አንዳንድ አካባቢዎች ደቡብ ምእራብ ለአብነት በሄክታር እስከ 15 ኩንታል በሄክታር ማምረታቸውን ገልጸዋል:: ተቋሙ እነዚህን መሰል ተሞክሮዎች አጥንቶ ሊያስፋፋቸው ይገባልም ብሏል ቋሚ ኮሚቴው::
ሕገ ወጥ የቡና ዝውውር በርካታ የውጭ ምንዛሪ የሚያሳጣ ስለሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ቁጥጥር መጠናከር እንዳለበትም ተነስቷል::
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን ያለፉት ዘጠኝ ወራት ሪፖርት በኮሚሽነር ፍርዓለም ሽባባው አማካኝነት ቀርቧል:: ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ካዳመጠ በኋላ ጠንካራና ደካማ ያላቸውን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም አስቀምጧል::
ሕብረት ሥራ ማህበራት የኑሮ ውድነቱን በማረጋጋት እና የአርሶ አደሩ ምርቶች በተገቢው ጊዜ እንዲነሱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል:: ሸማችንና አምራችን በአጠረ ሰንሰለት በማገናኘትም ሕብረት ሥራ ማህበራት ትልቅ አስተዋፅዖ እያረከቱ መሆኑን ገልጸዋል::
ተደራሽነት እና የአባል ብዛት በመጨመር ረገድ በዘጠኝ ወራት አፈፃፀሙ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንና የማደራጀት እና የማጠናከር ሥራዎችም አበረታች መሆናቸው ተገልጿል::
የሕብረት ሥራ ማህበራት አባላት ቁጥርንም አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ማድረሱ በበጎ መልኩ የተነሳ ሥራው ሲሆን የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች እንደሆነም ተነግሯል:: ከማዳበሪያ ሥርጭት ጋር ተያይዞ ማህበራት የሠሩት ሥራ ቋሚ ኮሚቴው በአካልም ወርዶ ያየው በመሆኑ በጥሩ ጎኑ ኮሚቴው በግብረ መልስ አንስቷል::
ከደላላ ጋር ተያይዞና ምርትን ለታሰበለት ዓላማ ሳይውል የመጥለፍ አዝማሚያዎች በጉድለት የሚታዩ በመሆኑ ማስተካከል እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል:: አምራቹና ሸማቹ ምርቱን በስግብግብ ነጋዴዎች እና በደላሎች እየተነጠቀ በመሆኑ በጣም አሳሳቢ ስለሆነ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባውም ተጠቅሷል::
በተያያዘ የዋጋ ሥርዓት ተበጅቶ ተመጣጣኝ የዋጋ ትመና ሊኖር ይገባል:: ምንም ዓይነት እሴት ያልጨመረ ደላላ በመካከል እየገባ የዋጋ ንረት መፍጠሩን ለማስቆም በትብብር አመርቂ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ተመላክቷል::
በሕብረት ሥራ ማህበራቱ ችግር ፈቺ ኦዲት ሊሠራ እንደሚገባውና ለዚህም ተቋማቱን በተማረ የሰው ኃይል መምራት እንደሚያስፈልግ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል::
ውብሸት ሰንደቁ
አዲሰ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም