
አዲስ አበባ፡- ትውልዱ ልዩነትን ትቶ አገርን ካጸኑ አባቶች የአንድነት መንፈስ ሊማር ይገባል ሲሉ አባት አርበኛ ዳኛቸው ተመስገን ተናገሩ።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል አባት አርበኛ ዳኛቸው ተመስገን የአርበኞች የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ትውልዱ በልዩነት እንዲራመድ ተሰብኳል። ይሁንና ይህን ክፉ ሃሳብ ትቶ አገርን በደምና በአጥንታቸው ካጸኑ አባቶች የአንድነት መንፈስ ሊማር ይገባል።
ጀግኖች አርበኞች ልዩነት ሳይገድባቸው፤ ፈተና ወደ ኋላ ሳይጎትታቸው፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለያቸው ጠላት አገርን ለመውረር በመጣ ጊዜ ሁሉ መከትው መልሰዋል፡፡ ድሉ የተገኘው ልዩነትን ወደ ጎን በመተውና አንድነትን በማጠናከር በመሆኑ ትውልዱም ከዚህ ተምሮ አገርን የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
እንደ አባት አርበኛው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ለምና የበፖለቲካውም ስትራቴጂክ ቦታ ላይ እንደመሆኗ ጠላቶቿ በየጊዜው የተለያዩ ሴራዎችን ለማሴርና የጀርባ ተንኮል ለመስራት አቅደው ይንቀሳቀሳሉ:: በተለይም በቀይ ባህርን ተንተርሶ በሚመጣ ፖለቲካ የተነሳ ግንባር ቀደም የትኩረት ማዕከል መሆኗ አይቀርም።
ስለዚህም ከፋፋይ ሴራዎችን ሁሉ አሸንፎ ለመጓዝ ልክ እንደአባቶች አንድነትን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል። ወራሪ በመጣ ጊዜ ሁሉ ይህ አንድነታችን ነው አሸናፊ ያደረገን ብለዋል።
ጠላት በአድዋ ድል ወቅት በሰማይና በመሬት በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ ታግዞ ጥቃት ቢፈጽምም፤ አባቶች ከልዩነታቸው ታቅበው አገርን በማስቀደም በእግራቸው ጭምር በመጓዝ ታላቅ ተጋድሎን ፈጽመዋል:: ከዚያ በኋላ የነበሩትም አባቶች ይህንኑ ደግመዋል፤ ትውልዱም ከዚህ ብዙ ሊማር ይገባል።
በወቅቱ አባቶች ጠላትን ድል ለማድረግ የነበራቸው ቁልፍ ጉዳይ አንድነታቸው ነበር ያሉት አባት አርበኛው፤ ጣሊያን በአድዋ ከተሸነፈ በኋላ በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች የነበሩት መሳፍንትና መኳንንቱ እርስ በእርሳቸው ይጋጩ ነበር። ነገር ግን ጠላት ዳግም ሲመጣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለዩ ስለ ልዩነታቸው ከድል በኋላ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘው አገርን በማስቀደም ነበር ጠላትን መፋለም የቻሉት ሲሉ አስረድተዋል።
በወቅቱ ይጣላ የነበረው፣ በመሬትና በሚስት ይጋደል የነበረው፤ እኔ ነኝ የበላይ የሚለውና ይጋጭ የነበረው ሁሉ ጠላት በመጣ ጊዜ ግን የእርስ በእርስ ሽኩቻውን አቁሞ ጠላትን በመፋለም አገር ማጽናት ችሏል ሲሉ ገልጸዋል::
ከጦርነት በኋላ ገበሬው ባለው አቅም አርሶ እንዲበላ፣ አንዱ ከሌላው ጋር በመተዋወቅ ብሄር፣ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይለዩ በአንድነትና በፍቅር አገራቸውን በመጠበቅ ለዛሬው ትውልድ ማቆየታቸውን ተናግረዋል::
ይህም አንድነት ኃይልና ፍቅርን ያሳየ በመሆኑ አዲሱ ትውልድም የአባቶቹን ዓርአያ በመከተል አገሩን የሚያጸናበትን የአንድነት ኃይል አጥብቆ ሊይዝ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አባት አርበኛው፤ ትውልዱ “አባትህን ጠይቅ ይነግርሀል” የሚለውን ብሂል መጠቀም እንዳለበት በመምከር፤ አባቶች ምን ያህል ፈተና ውስጥ ሆነው ጠላትን ማሸነፍ እንደቻሉም ጭምር ትውልዱ በሚገባ መማር አለበት። ታሪካቸውን በአግባቡ ሲያውቁም ጸብና ክርክርን ትተው ለወገን የሚጠቅመውን ፍቅርና አንድነትን መላበስ ይችላሉ ብለዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲሰ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም