
አዲስ አበባ፡- የጀግኖች አባቶች የመስዋዕትነት ውጤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ትውልዱ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት አገልግሎት ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን 81ኛው የኢትዮጵያ የድል በዓል ቀንን ምክንያት በማድረግ የጀግኖች አርበኞችን ተጋድሎ የሚዘክር አውደ ርእይ ትናንት በከፈተበት ወቅት ልጅ ዳንኤል ጆቴ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ትውልዱ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡
ጀግኖች አርበኞች ደማቸውን አፍስሰው ያቆዩአትን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ፍቅርንና መቻቻልን ከጀግኖች አባቶቹ ተምሮ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአንድነት ሊሻገር ይገባል ብለዋል ልጅ ዳንኤል ጆቴ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የቀድሞ አባቶች በጀግንነት፣ በመቻቻል፣ በመዋደድ እና በፍቅር ሀገርን ለማቆም ሲሉ የነፍስ ዋጋን ከፍለዋል፤ አሁን ያለው ትውልድም ኢትዮጵያ የጀግና አባቶች የመስዋዕትነት ውጤት የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማጽናት ኃላፊነት አለባቸው::
ጀግኖች አርበኞች ዋጋ ከፍለው አገር እንዳስቀጠሉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ከአርበኞች አንድነትን ትብብርን እና ጀግንነትን በመማር አገርን ለቀጣይ ትውልድ ማኖር ይገባቸዋል ብለዋል። የጀግኖች አርበኞች ታላቅ አደራ የሆነችው ኢትዮጵያ ጸንታ ለቀጣይ ትውልድ እንድትሸጋገር ሁሉም ሰው ዘብ ሊቆም ይገባል::
ኢትዮጵያን በሚመለከት ጉዳይ እያንዳንዱ ዜጋ መንግሥት ነው፤ ሀገርን ለመንግሥት ብቻ መተው አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ከፈለግን የምንሰማውን ነገር በብዙ ወንፊት እያጣራን ልናደምጥ ይገባል›› ያሉት ልጅ ዳንኤል፤ ለሀገር ሰላም መስፈን ሁሉም ህብረተሰብ የየግሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል:: የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፃህፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ተቋሙ ጀግኖች አርበኞችን የሚዘክር ሥራ በመስራቱ ትልቅ ኩራት ይሰማዋል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመፃሕፍት አገልግሎት የከፈተው አውደ ርዕይ ጀግኖች አርበኞች አገርን ለማስቀጠል የከፈሉትን ዋጋና በአንድነት መሻገር የማይቻል ችግር እንደሌለ ለትውልዱ ለማስተማር ያለመ ሲሆን፤ እስከ ሚያዝያ 28 ድረስ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲሰ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም