
አዲስ አበባ፡- ስለኢትዮጵያ የሚወራውን መጥፎ ዜና ለማረቅ ክርስቲያን ሙስሊሙ በሰላም የሚሳተፍበትን እንደ ኢፍጣር ያሉ መርሐ ግብሮችን በአግባቡ ማስተዋወቅ ይገባል ስትል በአሜሪካ ዳላስ የቢላል ኮሚዩኒቲ አባል የሆነችው ሃናን መሐመድ ተናገረች።
ከኢድ እስከኢድ አገራዊ ጥሪን ተከትሏ ወደኢትዮጵያ የመጣችው ሃናን መሐመድ በአሜሪካ ዳላስ ቴክሳስ ነዋሪ ስትሆን፤ ከ13 ዓመት በኋላ ወደአገሯ መመለሷን ትገልጻለች።
ወደአገሯ ከገባች በኋላም ብዙ መጥፎ ጉዳዮችን ብትሰማም እነደኢፍጣር ያሉ ክርስቲያን ሙስሊሙ በሰላምና በፍቅር የሚታደምበት መርሐ ግብር ላይ መሳተፍ መቻሏን ተናግራለች።
ሰባት ወር የሆናት የታናሽ እህቷን ልጅ ይዛ በአዲስ አበባ ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብር ላይ በሰላም መሳተፏን ገልጻ፤ በዚህም ዝግጅት በውጭው ዓለም የማይዘወተረውን ልምድ መካፈል በመቻሏ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።
ይህን አይነቱን መርሐ ግብር በዓለም ደረጃ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም መስህብነትም መጠቀም እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፋለች።
እንደ ሃናን ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያን ያለንን በጎ ልምድና መልካም ነገር ሳይሆን መጥፎ መጥፎው ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው ፤ ይህ አይነቱ አካሄድ መቀየር አለበት። በውጭው ዓለም ያለውን ልምድ በመውሰድ የእራስን በጎ ነገር መሸጥ ላይ ማተኮር ይገባናል።
በተለይ ወቅትን ጠብቀው የሚከሰቱና ሕዝብ በብዛት የሚታደምባቸውን ዝግጅቶቻችንን በማስተዋወቅ ጎብኝዎች እንዲመጡ ማድረግ ይቻላል የምትለው ሃናን፤ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐግብሩንም በተለይ ለዓረቡ ዓለምና ለሩቅ ምስራቅ ዜጎች በማስተዋወቅ ጥሩ የቱሪዝም ገቢ መፍጠር እንደሚቻል ነው የጠቆመችው።
የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብሮች በየከተሞቹ እንደሚደረጉ መረጃዎች ያሳያሉ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉት የኢፍጣር ሥነሥርዓቶች ከአክራሪነትና በጽንፈኝነት አካሄድ በተለየ መንገድ በፍቅርና በሰላም የሚከናወኑ ናቸው። ይህ በእራሱ ልዩ የሆነ ስሜትን የሚሰጥ አብሮነትንና ሰላምን የሚሰብክ አጋጣሚ በመሆኑ በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብላለች።
በየክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ቢሮዎችም ሆነ የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም በአስጎብኚነት የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት ሁሉ የተገኘችውን በጎ አጋጣሚ በመጠቀም የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለባቸው ስትልም ገልጻለች።
በዚህ ረገድ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐ ግብሮችን በይበልጥ የአብሮነትና የመተሳሰብ ስሜታቸውን እንዲጎለብት በማድረግ ይገባል የምትለው ዲያስፖራዋ፤ መርሐግብሮቹን በአግባቡ በማስተዋወቅ ስለኢትዮጵያ የሚወሩትን መጥፎ መጥፎ ዜናዎችና መረጃዎች የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽእኖን መቀነስ ይቻላል ስትል አስረድታለች።
ዜጎች በሰላምና በአንድነት ተከባብረው የሚያከብሩት ሥነሥርዓት መሆኑን ለዓለም በማስተዋወቅ ስለኢትዮጵያ በጎ በጎው እንዲወራ እድል የምንፈጥርበት አጋጣሚ በመሆኑ በየዓመቱ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን የቱሪዝም ሥራ ማከናወን ይገባል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም