
አዲስ አበባ፡-ተስፋ የተጣለበት ሃገራዊ ምክክር ዕውን እንዲሆን የበኩሉን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) አስታወቀ፡፡
የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ ፓርቲው ለሃገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የትኛውንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡
ሃገራዊ ምክክሩ ዕውን ሆኖ ችግሮች እንዲቃለሉ ፓርቲያቸው ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፤ ለዚህ ስኬትም በግልም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ማንኛውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኝነቱ አለ ብለዋል።
አቶ ተክሌ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከባዕዳን ጋር ካደረገችው ጦርነት በተጨማሪ ለበርካታ ዘመናት የእርስ በእርስ ጦርነትን አስተናግዳለች፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነቱን የመጣው ደግሞ እርስ በእርስ መግባባት ባለመቻላችን ነው፡፡ በቀጣይ ሊካሄድ የታቀደው ሃገራዊ ምክክርም ይህን ችግር አስወግዶ መግባባትን እንደሚፈጥር ይታመናል።
ንጹሕ አየር እየተነፈሱ የልማት መሠረት የሆነውን ሠላምን መገንባትና አስተማማኝ ልማትን ማራመድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ስኬት ሃገራዊ መግባባቱ ወሳኝነት አለው። ለምክክሩ ሂደት መሳካትም ወሕዴግ የድርሻውን ይወጣል ሲሉ አስታውቀዋል።
ዜጎች የተደላደለ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችል ሃገር ለመፍጠር አለመግባባቶች መፈታት አለባቸው ያሉት አቶ ተክሌ፤ ብረት አንስተው ጫካ የገቡ እንዲሁም የተለያየ ርዕዮተ ዓለም መርጠው ጽንፈኝነትን የሚያቀነቅኑም አሉ። ነገር ግን ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በጦርነትና በአለመግባባት ሳይሆን በሃገራዊ የምክክር መድረክ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ መግባባት ጽንሰ ሀሳብ ለበርካታ ዓመታት በመፈክርነት ተይዞ የቆየ ጉዳይ መሆኑ አቶ ተክሌ አስታውሰው፤ በተለይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ይሄንን ሀሳብ ሲያራምዱ እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ላይ ጊዜው ፈቅዶና መንግሥትም አምኖበት ለሃገራዊ ምክክር ዝግጅት መደረጉ ችግሮቻችንን ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ሆኗል ብለዋል።
ተስፋው ዕውን እንዲሆን በሃገራዊ ምክክሩ የአገሪቷ ችግር ምን እንደሆነ፣ ለምን ዜጎች እንደሚሰቃዩ፣ በጥልቀት በማየት ችግሮችን መለየት እንደሚገባ አቶ ተክሌ ተናግረዋል፡፡
አጀንዳዎቹ የችግሮችን ምንነት ነቅሶ በማውጣትና መግባባትን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ በማስቻል ላይ የምክክሩን ውጤታማነት ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ተሰምቶናል ብለው ቢያፈነግጡ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን ገልጸው፤ በሌሎች አገሮች የታዩ አገር አፍራሽ ተግባሮች በኢትዮጵያም እንዳይከሰቱ ከጽንፈኝነትና ከጎጠኝነት በራቀ መንገድ በምክክሩ ተሳትፎ ማድረግና ለውጤታማነቱም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ፓርቲዎች ጽንፍ በረገጠ አካሄድ ከመዝለቅ ይልቅ በመግባባት ላይ በተመሠረተ አካሄድ በመሳተፍ ምክክሩ እንዲሳካ ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
አቶ ተክሌ እንዳስታወቁት፤ የአገራዊ ምክክሩን ዓላማ የሚያበላሽ ነገር በምንም አይነት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ ለዚህም እያንዳንዱ ፓርቲና ግለሰብ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም