
አዲስ አበባ፡- የሕዝቡን ሰላም በማወክ የአገር ህልውና እያፈኑ ያሉ ጽንፈኛና አሸባሪ ኃይሎች ላይ ተመሳሳይ አቋም መያዝ ያስፈልጋል ሲሉ ፖለቲከኛና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ አቶ ቶሎሳ ተስፋዬ ተናገሩ::
አቶ ቶሎሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ የዜጎች የመኖር ዋስትና በጽንፈኞችና በአሸባሪዎች ሴራ አደጋ ላይ ወድቋል:: ለዚህም በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ጽንፈኞችና አሸባሪዎች የግላቸውን ፍላጎት በኃይል ለማሟላት ልማት ከማስተጓጎል፣ሕዝብና ሃገር ከማሸበር በዘለለም ለየትኛውም ወገን ጠቃሚ አለመሆናቸው ከአገራችንና ከዓለም ተሞክሮ በቀላሉ መረዳት ይቻላል ያሉት አማካሪው፣ ማንንም የማይጠቅሙትን የጥፋት ኃይሎች በሁሉም አካባቢ ተመሳሳይ አቋም ተይዞ ዕርምጃ ካልተወሰደ የሚያስከትሉት መዘዝ የማንወጣው ይሆናል ብለዋል።
ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ሰሞኑን የዜጎችን ደህንነት አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ቢዘገይም ተገቢ ነው፤ ሰው እየተገደለ፣ንብረት እየወደመ፣ልማት እየተስተጓጎለ በጥቅሉ የሰላም መድፍረስ እየተባባሰ መምጣቱን በማመን ምክር ቤቱ መግለጫ ማውጣቱ የሚደገፍ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት ሕዝቡን በማስተባበር በየትኛውም አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሰላም ኃይሎች ለአንዴና ለመጨረሻ አደብ ለማስያዝ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል። ዕርምጃውም በተግባር መደገፍ አለበት ብለዋል::
እንደ አቶ ቶሎሳ ማብራሪያ፤ ጽንፈኞችና አሸባሪዎች በየክልሎቹ ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል:: በእነዚህ ቡድኖች በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭትና የሰላም እጦት ውስጥ አገራዊ ምክክር ማካሄድ አጠያያቂ ነው::
መንግሥት ቡድኖቹን ለማጥፋት ከባድ መስዋዕት እየከፈለ መሆኑ ሲናገር ይደመጣል:: ነገር ግን ሕዝቡ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ጋር ሲነጻጸር እምብዛም አይደለም:: ያም ሆኖ የሽብር ቡድኑ ጥፋት አሁንም ባለበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ጽንፈኛም ሆነ የአሸባሪ ኃይሎች በዋናነት የሚጎዱት የገዛ ወገኖቻቸው አለፍ ሲል ደግሞ ሃገራቸው መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው ያሉት አቶ ቶሎሳ፣ከዚህ አንጻር የሸኔ ሽብር ቡድኖች በግንባር ቀድምትነት የኦሮሞ ሕዝብ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በመግታት ለከፋ ችግር እንዲዳረግ አድርጓል ብለዋል።
በተጨማሪ አሸባሪ ቡድን ለበርካታ ሰዎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል::
የኦሮሞ ሕዝብ በተለይ አርሶ አደሩ አርሶ ወይም ነግዶ መደበኛ ኑሮውን መምራት ተስኖታል ያሉት አማካሪው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በምስራቅና በምዕራብ ሸዋ፣በምስራቅ ወለጋ ጽንፈኞች ሕዝቡ ላይ የፈጸሙት በደል አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ላይ በኦሮሚያ ሕዝቡ ሸኔንና ጽንፈኞቹን እንደሚያወግዝ ሁሉ በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ ጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ ወጥ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል::
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም