
አዲስ አበባ፡- ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ተሳስሮና ተከባብሮ በኖረ ማኅበረሰብ መካከል ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን መንግሥት በሕግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደገለፁት፤ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ተሳስሮና ተከባብሮ በኖረ ማኅበረሰብ መካከል ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን መንግሥት በሕግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡
አስተያየታቸውን የተናገሩት አቶ አራጌ አሊ እንደተናገሩት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በሃይማኖት ሽፋን የሚፈፀሙ ተግባራት ኢትዮጵያን ለመሰለች የመቻቻል ሃገር የሚመጥኑ አይደሉም:: ለየትኛውም ሐይማኖት ተከታይም እንደዚህ ዓይነት ነውር ነገሮችን መፍጠር ተገቢ አይደለም::
ድርጊቱ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው ያሉት አቶ አራጌ፤ ለወደፊቱም ተፋቅረን፣ ተዋደን እና ተጋግዘን ልንኖር መቻል አለብን ብለዋል::
ጥፋን በጥፋት መመለስ የማይደገፍ ተግባር ነው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ ሰከን ብለው የሚያስቡ ሕዝቦችና የሃይማኖት እኩልነትን የምታከብር ሃገር አድርገን ልንገነባት ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ሃይማኖትን ተገን በማድረግ የሚንቀሳቀሱ አጥፊዎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል::
ሼህ መከተ ሙሄ በበኩላቸው፤ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተፈፀሙ ተግባራት እጅግ የሚያሳዝኑ ናቸው፤ ከአባቶችም ሆነ ከሃይማኖት መሪዎች አስተምህሮ ወጣ ባለ መልኩ በሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚወሰዱ ጥቃቶች እንደሚወገዙ ገልፀዋል::
ድርጊቱ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያለችበትን አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የሚንድ ስለሆነ ቶሎ ሊታረም የሚገባው ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል::
መንግሥት ይህንን ችግር በፍጥነት እልባት መውሰድ እንደሚኖርበትና የተሳሳቱትን መክሮ መመለስ፤ አጥፊዎች በሕግ ፊት እንዲጠየቁ ማድረግ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል::
ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እንደ አንድ ቤተሰብ አብሮና ተቻችሎ የኖረ ነው ይህ መልካም ተግባር በማስቀጠል ተከባብሮና ተቻችሎ መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል ሼህ መከተ::
በኢትዮጵያ ውስጥ የሌላውን መብት መግፋትና አላግባብ ድርጊቶችን መፈፀም እጅግ አሳፋሪና ከኢትዮጵያውያን ያልወረስነው ዕሴት ነው ብለዋል::
እንደ ሼህ መከተ ገለፃ፤ የመገፋፋት፣ የመጠፋፋትና ዕውቅና ያለመስጠት ዕሴት ዕጅግ አደገኛ እና ሕዝቡንም ሃገርንም የሚጎዳ በመሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባናል:: መንግሥትም ዋናው ተግባሩ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ ይህንን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል::
ያጠፉ ሰዎች ለሕግ መቅረብ አለባቸው ያሉት ሼህ መከተ፤ የተጎዱ ሊካሱ፤ ቤተሰባቸውን በሞት የተነጠቁም ሊፅናኑ ይገባልም ብለዋል::
እንደ ሼህ መከተ ፍትሕ ሊቆም የሚችለው የተስማማንበትን ሕግ በመካከላችን ስንተገብረው ነው:: መንግሥት እንደ መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚተግብራቸው ተግባራትም ሕዝቦች አብረውት ሊቆሙ ይገባል::
አቶ ኢብራሂም ከድር በበኩላቸው የሃይማኖት ተከታይ ነን የሚሉ ሰዎች ከሃይማኖቱ ትዕዛዛት ውጪ የሚፈፅሙት ተግባር ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል::
ይህ ተግባር አንድነትን የሚያፈርስና ለረጅም ዓመታት ተከባብሮ የኖረውን ማኅበረሰብ የሚሸረሽር ነው ያሉት አቶ ኢብራሂም ችግሩን ማስተካከል ያለባቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ አባቶችና መንግሥት የመጨረሻ ዕልባት ላይ እስኪደርስ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል::
እንደ አቶ ኢብራሂም፤ ሃይማኖትን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ማጋለጥ ይገባል መንግሥትም አጥፊዎችን ለሕግ አቅርቦ ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል::
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም