ዘመኑ እአአ 1954 ነበር፤ የእንግሊዝ ዋና ከተማ በሆነችው ለንደን የኮመንዌልዝ የወንዶች ማራቶን ውድድር እየተካሄደ ነው:: ቀዳሚው አትሌት ረጅሙን የጎዳና ላይ ሩጫ በአስደናቂ ብቃት ሸፍኖ ውድድሩ ወደሚጠናቀቅበት ስታዲየም ገብቷል:: ርቀቱን ለማጠናቀቅም የ200 ሜትር ርቀት ብቻ ቀርቶታል::
በድንገት ግን አትሌቱ የመዳከም ሁኔታ አሳየ፤ ሩጫው ወደ እርምጃ ጥቂት ወደፊት ከዚያ ወደጎን ደግሞ ወደሁዋላ እያለ በመጨረሻ ራሱን ስቶ ወደቀ:: ብርቱው አትሌት አሸናፊነቱን ሳያረጋግጥ በስታዲየም የተገኘው ስፖርት ወዳድም የናፈቁትን አስደናቂውን ብቃት ሊመለከቱ የማይችሉበት አሳዛኝ ክስተት ተፈጠረ:: ይህ ታሪክ እንግሊዛዊው አትሌት ጂም ፒተርስ
የስፖርት ተግባር ማወዳደር እና ማፎካከር እንደመሆኑ ተሸናፊና አሸናፊ መኖሩ የግድ ነው:: የተሻለው አካል አሸናፊ ሲሆን፤ በብቃቱ ደከም ብሎ የተገኘው ደግሞ የተሸናፊነት ጽዋን መጎንጨቱ የግድ ነው::
አንዳንድ ጊዜ ግን በስፖርታዊ ውድድሮች አሳዛኝ የሚባሉ ተሸናፊዎች ይታያሉ:: ተወዳጁን የእግር ኳስ ስፖርት እንደማሳያ ብናነሳ በጨዋታና በግብ ብልጫ ሲመራ የቆየው ቡድን በመጨረሻ ሰዓታት በሚቆጠርበት ግብ ተመትቶ ከውድድር ውጪ ሲሆን አሳዛኝ ተሸናፊ ይባላል:: የዛሬው የስፖርት ማህደር ገጽ ደግሞ በአትሌቲክስ ስፖርት አሳዛኝ ከሆኑ ክስተቶች መካከል አንዱ የሆነውን የዚህን የጂም ፒተርስ ታሪክ ያወሳል::
ይህ አትሌት እአአ 1918 የተወለደ እንግሊዛዊ የረጅም ርቀት አትሌት ነው:: በረጅም ርቀት አትሌት የጀመረ የሩጫ ሕይወቱ እንደሚጠበቀው ስኬታማ ባይሆንም ፊቱን የጎዳና ላይ ውድድር ወደሆነው ማራቶን ማዞሩ የስኬቱን መንገድ በግልጽ
አመላክቶታል:: በማራቶን የዓለም ክብረወሰን የሆነ ሰዓትን ከ2ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች በመግባት የግሉ በማድረግ አስደናቂ አቋሙን ያረጋገጠ አትሌት ነው:: ይኸውም ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩት የማራቶን አትሌቶች ወደ አራት ደቂቃ የሚሆን ብልጫ ያለው ሲሆን፤ ይኸውም አትሌቱ የተለየ ተሰጥኦ ያለው መሆኑን ያመሳከረ ነበር::
የመጀመሪያውን ክብረወሰን እአአ በ1952 ያስመዘገበ ሲሆን፤ የገባበት ሰዓትም 2፡20፡42 ነበር:: በቀጣዩ ዓመት በተካሄደ ሌላ ውድድር ላይ ደግሞ 2፡18፡40 በሆነ ሰዓት በመግባት የራሱን ክብረወሰን በማሻሻል በርካቶች ሊያደርጉት ቀርቶ ሊያስቡት የማይችሉትን ጀብድ ፈጸመ:: ቀድሞ በመግባት አሸናፊ ከመሆን ባለፈ ፈጣን ሰዓትን ማስመዝገብ የፉክክሩ አንድ አካል በሆነበት የአትሌቲክስ ስፖርት ሰከንዶችን ማሻሻል የሚያስገኘው ክብር ግልጽ ነው:: በአንጻሩ ይህ አትሌት ደቂቃዎችን በማሻሻልም ጭምር የወቅቱ የማራቶን ቁጥር አንድ አትሌት ለመሆን ችሏል::
ብርቱው አትሌት ፒተርስ በዚያው ዓመት በሆላንድ በተካሄደ ውድድር ላይ በድጋሚ ሰዓቱን ለማሻሻል አቅዶ ቢሮጥም፤ 2:19:22 በሆነ ሰዓት ነበር የገባው:: ይኸውም ሁለተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት ነበር::
በቀጣዩ ዓመት የኮመን ዌልዝ ውድድር አትሌቱ ተሳታፊ ሲሆን፤ በተለመደው ብቃት ርቀቱን ከመሸፈን ባለፈ የራሱን የቀደመ ሰዓት በድጋሚ ሊያሻሽል እንደሚችልም ግልጽ ነበር:: ምክንያቱ ደግሞ በሁለተኛነት እርሱን ከሚከተለው አትሌት 17 ደቂቃዎችን አስቀድሞ በመሮጥ የጎዳና ላይ ሩጫውን አጠናቆ ወደ ስታዲየሙ መገስገስ ችሎ ነበር:: በኢምፓየር ስታዲየም ውስጥም ተዓምረኛውን አትሌት ለመመልከት 35ሺ የሚሆኑ ተመልካቾች ተገኝተው ድጋፋቸውን ይሰጡ ነበር::
የተጠበቀው አትሌት በስታዲየሙ ብቻውን እየሮጠ፤ ሕዝቡም ደስታውን እየገለጠ ባለበት ሁኔታ ግን ድንገተኛ ክስተት ታየ:: ይኸውም አትሌቱ በመልካም ጤንነት ላይ አለመሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፤ ከመንገዳገድ አልፎ 200 ሜትር እየቀረው ተዝለፍልፎ ወደቀ:: በቦታው የነበሩት የሕክምና ባለሙያዎችም ሕይወቱን ለማትረፍ ፒተርስን የሐኪም ድጋፍ እንዲያገኝ ተረባረቡ:: ለሶስት ሰዓታት ራሱን ከሳተ በኋላ ቢነቃም በነበረበት አደገኛ ሁኔታ አንጻር በድጋሚ ግን ወደ ሩጫ ሕይወት ሊመለስ አልቻለም::
ውድድሩን ሙሉ ለሙሉ ባያጠናቅቅም የውድድር አዘጋጆቹ ተወያይተው ርቀቱን የሸፈነበት 2ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ የሆነ ሰዓት ሶስተኛው ክብረወሰን ሆኖ ሊመዘገብለት ችሏል:: አትሌቱ ጤናው ከተመለሰለት በኋላም ሕይወቱ የነበረበትን አደገኛ ሁኔታ ‹‹በዚያን ዕለት አለመሞቴ እድለኛ ስለነበርኩ ነው›› በማለት ነበር የገለጸው::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም