
አዲስ አበባ፡- የኢድ በዓል ገበያ በአቅርቦትና ግብይት የተቀዛቀዘ መሆኑን ነጋዴዎችና ሸማቾች ገለጹ፡፡
በአፍሪካ ትልቁ ገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶ የኢድ ገበያን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት ሪፖርተሮች ተዘዋውረው ያነጋገሯቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች የኢድ በዓል ገበያ በአቅርቦትና ግብይት ተቀዛቅዟል፡፡
በመርካቶ የቅመም ተራ የተለያዩ የቅመማቅመም መሸጫ መደብሮች ባማረ መልኩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አንድም ከላዩ ላይ የተነኩ ወይም የተሸጡ አይመስሉም፤ ለውበት የተቀመጡ ጌጦች በሚመስል ሁኔታ በማዳበሪያ አፍ ጢም ብለው ሞልተው ይታያሉ።
በመርካቶ ገበያ ግብይት የቅመማቅመም ነጋዴው አቶ ሳሚር ሽኩር እንደገለጹት፣ የኢድ በዓል ገበያ በአቅርቦትና ግብይት ተቀዛቅዟል፡፡
እንደ አቶ ሳሚር ገለጻ፣ የበዓል ገበያው መቀዛቀዝ ሊከሰት የቻለው ከፋሲካ በዓል ማግስት የቀጠለው የዒድ ገበያ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ለሸመታ ካለመውጣቱና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገበያው ዋጋ ያሻቀበ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡
የቅመማ ቅመም ገበያው የተቀዛቀዘ ነው ያሉት አቶ ሳሚር፤ የሸማቾችም ሆነ የሻጭ እንቀስቃሴ ተቀዛቅዟል። የገበያው አቅርቦትና ሽያጭ እንደ ከዚህ በፊቶቹ የበዓላት ግብይቶች አይደሉም ብለዋል፡፡
የእርድ እንስሳት፣ የስጋ፣ የወጥ እህሎች ከፋሲካ ገበያ በተመሳሳይ የግብይት ሽያጭ ቀጥሏል፡፡ ቀይ ሽንኩርት የችርቻሮ ዋጋው ኪሎ በ48 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 60 ብር፣ ዝንጅብል 60 ብር እየተሸጠ ሲሆን ከፋሲካ በዓል ወዲህ የተወሰነ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናግረዋል።
የዘይት ዋጋ በመርካቶ ገበያ ፈሳሹ ዘይት 890 እስከ 980 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለማየት ችለናል።
ዶሮ የአበሻ ከ700 እስከ 750 እና የሸኮ ዶሮ ከ800 እስከ 850 ብር ድረስ ሲሸጥ፤ የሥጋ ግብይትም አንድ ኪሎ ከ300 እስከ 450 ብር መሸጡን ተዘዋውረን ተመልክተናል። የቅቤ ዋጋ ግብይት ከ700 እስከ 750 ብር ድረስ በመርካቶ ሲሸጥ በፒያሳ የበዓል ባዛር ገበያም ደግሞ ከ490 እስከ 550 ብር ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡
በሾላ ገበያ የኢድ ግብይት ሲያደርጉ የነበሩት ወይዘሮ ራዉዳ ሳኒ እንደገለጹት ደግሞ፤ የዘንድሮ የኢድ ገበያ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ አንድ ኪሎ ቀይሽንኩርት 50 ብር ተሸጧል ብለዋል፡፡ የአንድ ኪሎ አይብ ዋጋ ከ 200 እስከ 250 ብር፣ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከ340 እስከ 450 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ገልጸው፤ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡
ሌላኛው ሸማች አቶ አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው ዶሮ በዘንድሮ የኢድ ገበያ ከ350 እስከ 800 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ገልጸው፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ እንደታየበት ተናግረዋል፡፡
በሾላ ገበያ የቅመማቅመም እና ዶሮ ነጋዴ የሆኑት አቶ ሱልጣን አሊ በበኩላቸዉ እንደሚናገሩት፤ ዶሮ እንደ ክብደቱ መጠን ከ600 እስከ 800 ብር፣ በርበሬ በኪሎ 340 ብር፣ ሚጥሚጣ 250 ብር፣ እንቁላል የአበሻ ከ8 ብር ከ50 ሳንቲም እንዲሁም በተለምዶ የፈረንጅ እንቁላል የሚባለው ስምንት ብር፣ የምግብ ቅቤ በኪሎ 650 ብር፣ ቡና በኪሎ ከ350 እስከ 400 ብር እየሸጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮ ገበያ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሙሳ ሙሐመድ፣ በኃይሉ አበራና መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም