
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ታምርት በሚል መሪ ቃል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የተዘጋጀው የንቅናቄ መድረክ በይፋ ተጀመረ፡፡
ትናንት በአዲስ አበባ በጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፤ ተሰፍሮ የማያልቅ ተፈጥሯዊ ሀብትን በታደለችው ከመቶ ሚሊዮን በሚልቀው የሕዝብ ቁጥሯ ውስጥ አብዛኛው በአምራች ዕድሜ ክልል በሚገኝባት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን ተባብረን ከሠራን በአጭር ጊዜ ብልፅግና ላይ መድረስ እንችላለን ብለዋል። ብልፅግና ያለ አድካሚ ሥራና ጥረት ከቶውንም ሊሳካ አይችልም ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በአገራችን ከተሞች ለሥራ ፈላጊዎች የተለያዩ አማራጮችን ለማመቻቸት የከተሞችን የሥራ ዕድል ማጠናከር እና የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ድጋፍን ማከናወን ለነገ የምንለው ተግባር አይደለም ዋና አጀንዳችን ነው ብለዋል፡፡
የሥራ ዓይነት ሳያማርጡ፤ ለሰማያዊና ነጭ ኮሌታ ክብር ሳይጨነቁ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው የሠሩ የደረሱበትን ከፍታ አይተናል ያሉት ከንቲባዋ፤ የሥራው መዳረሻ አላማው የሥራ ክቡርነትን ባህል በማድረግ፤ የማምረትና የአገር ውስጥ ፍጆታን ከመሸፈን ባሻገር የዓለም ገበያ ውስጥ በብቃት መግባትን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ለኢንዱስትሪው የምናደርገውን ድጋፍ በመፈተሽ አዳዲስ አሠራሮችንም በመተግበር የተሻለ ውጤት እንደምናስመዘግብ እምነቴ ነው በማለት የከተማ አስተዳደሩ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ የሚሠሩ እጆችን ከሥራ ጋር ለማገናኘት በከተማዋ ከተያዘው እቅድ አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለው ንቅናቄ አንዱ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ከዘርፉ በአመት የሚገኘውን ምርት ከፍ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።
ከተለመደው መንፏቀቅ ለመውጣት የተለየ ንቅናቄ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም አገር ውስጥ ምርት መሻሻል እና የሥራ ባህልን ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡
ንቅናቄው በአሁኑ ጊዜ ካሉ 10 ሺህ 500 አምራች ኢንዱስትሪዎችን ቁጥር ወደ 22 ሺህ ለማሳደግም እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት።
በተጨማሪም ያለ ኢንዱስትሪ ልማት ያደገ አገር አለመኖሩን ያነሱት አቶ ጃንጥራር ዐባይ፤ «እኛም እንደ አገር ለመበልፀግ የተለያዩ ፖሊሲዎችን አሻሽለን ከኢንዱስትሪያሊስቶች ጋር ተቀራርበን መሥራት አለብን» ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም