
አዲስ አበባ፡- መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የገባውን ቃል እንደማያጥፍ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ለሠራተኞች የኑሮ ሁኔታ መሻሻል እና በተለያዩ የሥራ ከባቢዎች የሚነሱ ቅሬታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥልቅ ጥናቶች እየተካሄዱ ነውም ተብሏል፡፡
መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የገባውን ቃል እንደማያጥፍ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፍሪያት ካሚል ገለፁ፡፡
ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የዓለም የላብ አደሮች ቀን (ሜይዴይ) በትናንትናው ዕለት ሲከበር ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የገባውን ቃል አያጥፍም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ በጥልቅ ጥናት ታይቶ ሊሠራ የሚገባው ስለሆነ ጥናቶች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የአነስተኛ ደመወዝ ወለል ጉዳይ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የሠራተኞች ታሪክ ተከድኖ ይብሰል ከተባሉ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ነበር ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት በአጠቃላይ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል፤ በተለይ ደግሞ የሠራተኞችን ሕይወት ለማሻሻል በወሰደው ቁርጠኝነት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ውሳኔ ከነውርነት ወጥቶ የአደባባይ አጀንዳ ሆኗል ብለዋል፡፡
የሠራተኞች ዝቅትኛ የደመወዝ ወለል የሕግ ጉልበት እንዲያገኝ ተደርጎ ፀድቋል፡፡ ሆኖም ወደ ተግባር ለመግባት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ በዝርዝር ጥናትና በጥንቃቄ ላይ ተመርኩዞ መሠራት ስለሚኖርበት እንጂ ሥራዎቹ አልቆሙም ሲሉም አክለዋል፡፡
እየተሠሩ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተጠ ናቀቁ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንሸጋገራለን ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
የሠራተኛውን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ወደ ኋላ አይልም ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ሠራተኛው የተለያዩ ጥያቄዎች እንዳሉት እናውቃለን፡፡ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ከሠራተኞች እና ከአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች ጋር የበለጠ ተቀራርበን እንሠራለን ብለዋል፡፡ በሠራተኛውና በኮንፌዴሬሽኑ በኩል የተጠየቁ ጥያቄዎች አብዛኞቹ ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት የሚፈልጉ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ሙፈሪያት ገለጻ፤ ቀጣይነት ያለው የኑሮ መሻሻል እና ዘላቂነት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍ ጠር እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል የሠራተኛና የአሠሪ የግንኙነት ሁኔታ አንዱ ነው፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርም የተቋማዊ ለውጥ ሥራው አንድ አካል አድርጎ ይዞታል፡፡
የአሠሪዎችና የሠራተኞች ግንኙነትን ለማዳበር ከአሠሪዎች ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጀመርነው ጉዞ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አንዳንድ የተጀመሩ ሥራዎች ግን ምክንያታዊ ጊዜን የሚፈልጉ መሆናቸው ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት ሲሉ ገልፀዋል።
በሠራተኛው በኩል ክህሎትን ያለማቋረጥ ማሻሻል እና የሠራተኛውን የመደራጀት መብት ማስከበር የመደራደር አቅሙን ስለሚጨምርለት እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።
የሠራተኛው መደራጀት ለተጀመረው የዴሞክራሲ ትግል እና የልማት ጉዞ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የገለፁት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ለአሠሪ ተቋማት የሠራተኛው መደራጀት አቅምና ሥንቅ እንጂ ሥጋት ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት አገራዊ ለውጡን መሠረት ባደረገ አኳኋን ሕጎችንና ፖሊሲዎችን የመፈተሽ ሥራዎች ተሠርተዋል። የሠራተኛውን ድምፅ የሚወክሉ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ላይ በርካታ ጥረቶች እየተደረገ ይገኛል።ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ ያሉ ተደማሪ ውጤቶች ያሉ ቢሆንም በቂና አርኪ አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ሠራተኛው በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች እንዳሉት ተናግረዋል።የኢትዮጵያ ሠራተኞች የሰላም፣ የኑሮ መሻሻል እና የሥራ ላይ ደህንነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ሊመለሱ ይገባል ብለዋል፡፡
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አለመወሰን፤ የኑሮ ውድነቱ ሠራተኛው ላይ ያስከተለው ጫና፤ በነፃነት የመደራጀት እና የመደራደር መብት እና ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች በሠራተኛው ላይ የተጋረጡ አንገብጋቢ ችግሮች መሆናቸው መታወቅ አለበት።የባለድርሻ አካላት ትብብር እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠን በኢትዮጵያ ሠራተኞች ሥም አጥብቀን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተከበረው የዓለም ላብ አደሮች ቀን (ሜይዴይ) ዛሬ ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በዓለም ለ133ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ47ኛ ጊዜ ተከብሮ ይውላል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም