
አዲስ አበባ፡- ሕወሓት በጉልበት ከያዛቸው የአማራና የአፋር ወረዳዎች ለቅቆ አለመውጣቱ በዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ። በቅርቡ ዘጠኝ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 146 ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ትግራይ መደረሳቸውን አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ሰብዓዊ ዕርዳታን ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ ክልል ለማድረስ እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጡት መካከል ሕወሓት ከያዛቸው የአፋርና የአማራ አካባቢዎች እንዲለቅ የሚል ቢሆንም ቡድኑ ከያዛቸው ቦታዎች ለቅቆ አለመውጣቱ ዕርዳታው ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ።
ሕወሓት ከአማራና ከአፋር የወሰን አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ አለመውጣቱ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ካለማክበሩም ባሻገር ግጭት የመቀስቀስ አዝማሚያ እያሳየ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና ፤ ሕወሓት የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም ለማደፍረስና ግጭቱን የመቀስቀስ አዝማሚያ ማሳየቱ ካለፈው ሊማር ያልቻለ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ፣ የቡድኑ መሪ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2022 ላይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፃፈው ደብዳቤ ጥቃት የመፈፀም አዝማሚያዎች እንዳሉት ግልፅ ማድረጉንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከምንጊዜውም በተሻለ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ያለምንም ገደብ እንዲደርሱ እያደረገ መሆኑን የገለፁት አምባሳደር ዲና፤ በቅርቡም ዘጠኝ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ 146 የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የዕርዳታ ድርጅቶችም ሆኑ ዕርዳታዎች ምንም የተገደቡበት ሁኔታ አለመኖሩን የገለፁት ቃል አቀባዩ ፤በኢትዮጵያ በኩል ያለው የተረጂ መጠን መጨመርና የለጋሾች እጅ ማጠር ሰብዓዊ ዕርዳታዎች በሚፈለገው ልክ እንዳይሆኑ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በዕርዳታ ሰጪ ማኅበረሰቡ በኩል እጥረት መኖሩ እና በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው የአማራ፣ የአፋርና የትግራይ ክልሎች በተጨማሪ በደቡብ ክልል፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ክልል ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ የዕርዳታዎች መጠን በተገቢው እና በሚፈለገው ልክ ሊሆን እንደማይችል አመላክተዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዕርዳታ እጁን ይበልጥ መዘርጋት እንደሚኖርበትና የሕወሓት ኃይል ከያዛቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች እንዲለቅ ግፊት እንዲያደርግ አምባሳደር ዲና ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል ከኢድ እስከ ኢድ መርሀ ግብር ዜጎች ዓመት በዓልን ምክንያት አድርገው ሃይማኖታዊ በዓላቸውን እንዲያከብሩ፤ አገራቸውን ለመጎብኘት ዕድል እንዲያገኙ ብሎም ለሀገራቸው የሚፈለግባቸውን ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ከዚህ በፊት በዲያስፖራዎች በሀገር ውስጥ እንዲያከብሯቸውና እንዲሳተፉባቸው የተደረጉት መርሀ ግብሮችና በዓላት በአንድ ጊዜ ብቻ የሚያቆሙና በአጋጣሚ የተደረጉ አይደሉም ብለዋል።
አሁንም ከኢድ እስከ ኢድ የሚለው መርሐ ግብርም የዚህ አካል መሆኑን ጠቁመው፣ በመርሃ ግብሩ መሰረትም በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደሚገኝና ከኢድ እስከ ኢድ ኤክስፖ ተከፍቶ የኢትዮጵያ ምርቶች የቀረቡበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል። በዱባይ፣ አንካራና ሳዑዲ ኢምባሲዎች የኢፍጣር ፕሮግራም በማዘጋጀት የዚሁ ሁነት አንድ አካል የሆነ መርሐ ግብር ማከናወናቸውም ተጠቅሷል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም