
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ፖሊስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ፈጣን እርምጃ ለመውሰድና ወንጀለኛን ለፍትህ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኛን የመቆጣጠርና የመከላከል አቅሙ ማደጉን የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂ በፊቼ ጫምባላላ በዓል መጠቀሙንና በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም በሰላም እንዲካሄድ መከታተሉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚደረጉ ሁነቶችን የሚከታተልበት ሥርዓት መዘርጋቱ ይታወቃል። ኮሚሽኑ በመደበኛ ስፍራ የተተከሉና በሰዎች አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ ሚስጥራዊ ዘመናዊ ካሜራዎችን ነው እየተጠቀመ የሚገኘው።
ካሜራዎቹ በማዕከል ላይ ከተተከለ መቆጣጠሪያ ክፍል ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ በመሆኑ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሁነቶቹን በቀጥታ እንዲከታተሉ እድል ፈጥረዋል።
እነዚህ ሚስጥራዊ ካሜራዎች ወንጀልና ወንጀሎኞችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
በኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ ማስፋፋያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የቴክኖሎጂ ውጤቱ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ ነው።
ካሜራዎቹ ትናንትናና ዛሬ በደማቅ ሁኔታ በተከበረው የፊቼ ጫምባላላ በዓል ላይ በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል።
በተመሳሳይ በዛሬው የአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሀ ግብርም እነዚሁ ዘመናዊ ሚስጥራዊ ካሜራዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሰላማዊው ሕዝብ ያለምንም ስጋት እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ነውም ብለዋል።
ኮማንደር ደምሴ አክለውም ሚስጥራዊ ካሜራዎቹ ለነዚህ ሁነቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ወንጀልን መከላከል የሚያስችሉ ናቸው።
ካሜራዎቹ በዚህ ወቅት ዓለም ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በማዕከል ያለው የፖሊስ አባልና ቦታው ላይ ያለው ፖሊስ በቀላሉ መረጃ መለዋወጥ እንዲችሉ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። ይህም መሆኑ ችግሮች ሳይፈጠሩ የመቆጣጠር አቅምን አሳድገዋል ነው ያሉት።
እነዚህ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ካሜራዎች መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ኮማንደር ደምሴ።
ይህ ብቻ ሳይሆን ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ፣ ወንጀለኛን ለፍትህ ለማቅረብም ትልቅ ጥቅም እየሰጡ ነው ብለዋል።
እንደ ኮማንደር ደምሴ ገለጻ፤ የካሜራዎቹ ሚስጥራዊነት በተጠበቀ መልኩና ዘመኑን በሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ደኅንነታቸው ይጠበቃል።
ለዚህም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ፖሊስ እየተጠቀመ በሚገኘው ዘመናዊ የደኅንነት ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ሰሞኑን በጎንደር ከተፈጠረው ችግር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑም ታውቋል።
በዚህም ከ370 በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም