
• መገናኛ ብዙኃን መረጃ የሚከለክሉ ተቋማትና አካላትን ሊያጋልጡ ይገባል
አዲስ አበባ:- የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች በስራው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደፈጠሩበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገለጸ። መገናኛ ብዙኃን መረጃ የሚከለክሉ ተቋማትና አካላትን ማጋለጥ እንደሚኖርባቸው የሕግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ገምግሟል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የሐሰት መረጃና የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት በኩል አሁንም ፈተና ሆኗል። ሚዲያ የአገር ግንባታ፣ የሕዝብ አብሮነትን የሚያጠናክሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ችግር ሲፈጠርም ችግር አመላካች ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት።
የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃ ይዘትና በአገር ሰላምና ደህንነት ላይ ተጽእኖ የመፍጠር አዝማሚያ ያላቸውን በመለየት የህግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ መረጃ በማደራጀት ለሚመለከታቸው የሕግ አስፈጻሚ አካላት ማቅረቡንም ጠቁመዋል።
መረጃ በሌለበት ሁኔታ ሚዲያው ሚዛን አልጠበቅክም ማለት አንችልም። ጋዜጠኞች ለተሳሳተ መረጃ ከሚዳርጋቸው መካከል አንዱ የመረጃ እጥረት መሆኑንም አመልክተዋል። መረጃ የሚከለክሉ አካላት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባና ባለስልጣኑ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሚዲያ የአገር ግንባታና የሕዝብ አብሮነትን የሚያጠናክሩና በእውነት ላይ ሊመሰረቱ ይገባል ያሉት አቶ መሐመድ፤ ምክር ቤቱ መረጃ በማይሰጡ አካላት ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት አሰራር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ሚዲያው በገለልተኝነት መረጃን፣ ህግንና ህሊናን መሰረት አድርጎ መስራት አለበት። የሚወግነው ለሐቅና ለእውነት መሆን አለበት እንጂ፤ በጽንፈኞች አጀንዳ ውስጥ መጠለፍ የለበትም። ገንዘብ፣ ፖለቲካ ዓላማ ባላቸው አካላት ተጽእኖ ስር መግባት የለበትም።
የምርመራ ጋዜጠኝነትን በጥንቃቄና በጥሩ ስነ ምግባር ካልተመራ ይበላሻል። የምርመራ ጋዜጠኛው ጥሩ ስነ ምግባር ያለው መሆን አለበት። ካልሆነ ግን ማሕበራዊ ፍትህን ከማስፈን ይልቅም በተቃራኒ ሊቆም ይችላል፣ የግል ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ለሚፈልጉ አካላት ዕድል ይከፍታል ብለዋል።
አሰራሩን ስርዓት ለማስያዝ ከስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና ከሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማ ጋር በመቀናጀት አሰራሩ የሚመራበት የአዘጋገብ መመሪያ ስርዓት እየተዘጋጀ መሆኑንና ለባለሙያዎቹ ተገቢ ጥበቃ የሚደረግበትም አሰራር እንደያዘም ተናግረዋል።
የክልል መገናኛ ብዙሃን ያቋቋማቸውን ሕዝብ አብሮነት፣ ብልጽግና የሚያመለክቱ አጀንዳዎች ላይ መስራት አለባቸው፣ የአካባቢያቸውን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ብለዋል።
በአገር ማዳን ዘመቻ አንዳንድ ብዙሃን መገናኛ የሚሰሩት ስህተት ለሽብር ቡድኑ አቅም የሚጨምር ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ተጽኖዋቸው አገር አፍራሽና የማይታለፉ ሆነው በመገኘታቸው ማስተካከያ ማድረግ ማስፈለጉን አመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ፤ ሐሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩ ሲ ኤን ኤን (CNN)፣ ቢቢሲ(BBC) ፣ ሮይተርስ (Reuters) እና አሶሺዬትድ ፕረስ (Associated Press) ትኩረት ሰጥቶ የወሰደው ርምጃ፣ የተገልጋይ ርካታን ለማሳደግ የሰራውን ስራ በጠንካራ ጎን አንስተዋል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ምክር ቤቱ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ የሚከለክሉ ተቋማትና አካላትን ሕጉን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ከሚያደርገው ተግባር ባሻገር ሚዲያው ራሱ መረጃ የሚከለክሉ አካላትን ሊያጋልጥ ይገባል ብለዋል።
የምርመራ ዘገባ የመልካም አስተዳደር፣ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ መጓደልን በማጋለጥ ለሕዝቡ እፎይታ የሚሰጥ ስራ የሚሰራበትን ቁመና እንዲላበስ የቁጥጥርና ክትትል ስራውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
ሚዲያ በተለይ ዩቲዩበሮች ከአፍራሽ አስተሳሰቦች ርቀው አገርን በማቆም ተግባር ላይ እንዲሰማሩ፣ የክልል ሚዲያዎች የሕብረተሰብ ድምጽ እንዲሆኑ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ መንግሥት መስርታ የኖረች ረጅም ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም፤ እድሜዋን የሚመጥን የሚዲያ አውታር አልዘረጋችም፤ የተወዘፈ ችግርን ሊያርም የሚችልና ኢትዮጵያን የሚመጥን የሚዲያ ተቋም እንዲፈጠር ባለስልጣኑ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም