
አዲስ አበባ፡- “ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ አንድ ሚሊዮን መጻሕፍትን የማሰባሰብ ዘመቻ ሊካሄድ ነው።
የመጻሕፍት አሰባሳቢ ኮሚቴው ትናንት በሰጠው መግለጫ፤ የመጻሕፍት መሰባሰብ ዓላማው፤ ለአብርኆት ቤተ መጻሕፍት የሚሆኑ መጻሕፍትን በአይነትና በብዛት ማሰባሰብ፤ ለሌሎች ክልሎችና ከተማዎች ለሚገኙ አብያተ መጻሕፍት ለመለገስ፤ እንዲሁም የንባብ ባህልን በማዳበር ፣አንባቢና አሰላሳይ ትውልድ እንዲፈጠር ለማበረታታት እንደሆነ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ዕውቀት መር ማህበረሰብ ለመገንባት እውቀት የሚሸጋገርባቸው መንገዶችን ማሳለጥ ያስፈልጋል ፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ መጻሕፍት ዋነኞች እንደሆኑ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ፊደል ቀርጸው፣ ብራና ፍቀውና ቀለም በጥብጠው፣ ከድንጋይ ዘመን እስከ ወረቀት ዘመን እውቀትን ለማስተላለፍ የተጉ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊዋ፤ በዚህ የፊደል ቀረጻና የእውቀት ምርት ያላቸው ቦታ ያህል ከታሪካቸው፣ ከቋንቋና ባህል ብዝኃነታቸው ከህዝብ ቁጥራቸው ጋር የሚመጣጠኑ አብያት መጽሐፍት እንደሌሉም ተናግረዋል። ይህም እውቀት መር የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ማጓተቱት ጠቅሰዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ይሄንን ችግር ለመፍታት ከዛሬ 75 ዓመታት ጀምሮ ዘመናዊ አብያተ መጻህፍትን ለመገንባት ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን የህዝቡን ቁጥር፣ ብዝኃነትና የሥነ ጽሁፍ ሀብት የሚመጥን አይደለም።
የለውጡ አመራር ቁልፍ ቦታ ከሰጣቸው ተግባራት አንዱ እውቀትና ኪነ ጥበብን ማበረታታት መሆኑን አመልክተው፤ ለዚህም የሚሆኑ መሠረተ ልማቶችን እየገነባ እንዳለና በ10ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ውስጥ ይህ ጉልህ ቦታ መያዙን ተናግረዋል።
የአብርኆት ቤተ መጻሕፍ፤ እውቀት መርና አመክንዮአዊ የሆነ ትውልድ ለመገንባት፣ ከግንባታው ጀምሮ በያዛቸው አካላዊና ዲጂታል መጻህፍት ድረስ ወደ ፊት ለሚገነቡ አብያተ መጻሕፍት አርአያ እንዲሆንና ለሌሎች አብያተ መጻሕፍት ማሠራጫ ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል እንደተገነባ ዶክተር ሂሩት ገልጸዋል። በዚህ መሠረትም ይሄን ቤተ መጻሕፍት ለኢትዮጵያውያን በሚጠቅሙ አካላዊና ዲጂታል መጻሕፍት ለማሟላት እየተሰራ እንዳለ አስታውቀዋል።
ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2014ዓ.ም አንድ ሚሊዮን መጻሕፍት እንደሚሰበሰቡ ይህም የሚከናወነው በአብርኆት ቤተ መጻሕፍ ውስጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለሥራው መሳካት፤ የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ተጠሪ ተቋማት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የህክምና ተቋማት፣ የኮንስትራክሽን ተቋማት፣ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ተቀማጭነታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊት፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ አሳታሚዎችና ማተሚያ ቤቶች፣ የታክሲና የረጅም ርቀት ሹፌሮችና ረዳቶች፣ ሊስትሮዎች፣ የቀን ሠራተኞችና ሌሎችም በልዩ ልዩ የኢትዮጵያና የውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ እንዲሁም ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎችን የሚያስረዱ መጻሕፍትን በመለገሥ አሻራቸውን ለትውልድ እንዲያቆዩ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው፤ ዜጎች ራሳቸውን በእውቀት እንዲያጎለብቱ አብርኆት ቤተ መጸሀፍት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። በአሁን ወቅት በመጻህፍት ቤቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሮኒክስ መጻህፍት ክምችት እንዳለ ጠቁመዋል። አራት ሚሊዮን አካላዊ መጻሕፍትን የመያዝ አቅም እንዳለውም ጠቅሰዋል። ይህንን ለማሳካትም ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ የቻለውን ያህል መጻህፍት እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
በአንድ ወር አንድ ሚሊዮን መጽሐፍት ለመሰብሰብ በተጀመረው ተግባር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተወጣጡ አካላት በኮሚቴ ተዋቅረው እየሰሩ እንደሚገኘ ታውቋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም