
አዲስ አበባ፦ ወንጀልን በሌላ ወንጀል ለማረም መሞከር ሕገ ወጥነት ነው ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና በፕሮቴስታንት አማኞች ቤተ አምልኮዎች ላይ የተፈፀመውን ሕገ ወጥና የወንጀል ተግባር አውግዛለሁ ብሏል።
ተግባሩ በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ደረቅ ወንጀልና በህግ ሊያስጠይቅ የሚገባው ተግባር መሆኑንም ጉባኤያችን በጽኑ ያምናል ሲል አስገንዝቧል።
ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የተፈፀመወን አስነዋሪ ተግባርን አስመልክቶ ጉባኤያችን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ተግባሩን አምርሮ በማውገዝ ጥፋትን በጥፋት፣ ወንጀልን በወንጀል ለማረም የሚደረግ ሙከራ እንዳይኖር ማስገንዘባችን ይታወሳል። ይሁን እንጂ ከትናንት በስቲያ በሆነው ሁሉ አዝነን ሳንጨርስ ይህ መከሰቱ በእጅጉ አሳዝኖናል ሲል መግለጫው አመልክቷል።
ሁሉም ሃይማኖቶች ሰላምን የሚሰብኩ፣ ትህትናን የሚያስተምሩና ለሌሎች ስለመኖርና መስዋዕት ስለመክፈል የሚገዳቸው እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በሃይማኖት ስምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀመው ሁሉ ሕገ ወጥና ደረቅ ወንጀል እንደሆነ ታውቆ መንግሥት ሕግና ስርአትን እንዲያስጠበቅ ጉባኤያችን አበክሮ ይጠይቃል። መንግሥት ሕግና ስርአትን ለማስፈፀም እንዲችል ቀደም ብሎ ያወጣቸውን ህጎችን ሁሉ ተፈፃሚ ሊያደርግ ይገባል ብሏል።
ሕዝበ ሙስሊሙም ይሁን ሕዝበ ክርስቲያኑ በየትኛውም አካባቢ የተከሠተው ችግርና የደረሰው ውድመት ሃይማኖታዊ መሠረት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ አካባቢያቸውን በጋራ በመጠበቅ፣ ችግሮች እንዳይባባሱም አንዱ ሌላውን በመጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ መግለጫው አመልክቶ፤ ችግር ፈጣሪዎችንም በማጋለጥና አሳልፎ ለሕግ አካላት መስጠት እንደሚገባ አሳስቧል።
በማኅበራዊ ሚዲያው መልዕክት የምትላላኩ አካላትም በምትጽፉት ጽሁፍና በምታስተላልፉት መልዕክት ሀገራችሁና ወገናችሁ ለከፋ ጉዳት እንዳይጋለጥ ሁሉንም ተግባር በማስተዋል እንድትከውኑ እየጠየቅን በሃይማኖት ስም የሚደረግ የጥላቻ ቅስቃሳን ባለማጋራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን ሲል ጉባኤው በመግለጫው መልዕክት አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም