
አዲስ አበባ፡- ጥፋትን በጥፋት ለማረም የሚደረግ እንቅስቃሴ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ወገን ከዚህ ድርጊት እንዲታቀብ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ጠየቁ።
ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ከሰሞኑ በጎንደር የተከሰተውን አለመረጋጋት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ጥፋትን በጥፋት ለማረም የሚደረግ እንቅስቃሴ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ተጨማሪ ችግር እንዳይከሰት መረጋጋት ያስፈልጋል።
በጎንደር በተፈጠረው ችግር ተዋናይ የሆኑ አካላት ለህግ ለማቅረብ ብሎም በሌሎች አካባቢዎች መሰል ጥፋቶች እንዳይከሰት ሕዝቡ በሰከነ መንፈስ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅበታል።
በጎንደር ለቀብር የወጡ ሙስሊሞች ላይ በታጠቁ ሀይሎች የተቃጣው ጥቃት ከሃይማኖት አስተምህሮና ከኢትዮጵያዊ ባህል ያፈነገጠ ድርጊት መሆኑ ሁሉንም ያሳዘነ ክስተት ነው። ነገር ግን ጥፋትን በጥፋት ለማረም የሚደረግ እንቅስቃሴ የከፋ ቀውስ ከማስከተል ውጪ ሌላ ፋይዳ የሌለው ነው። አጥፊዎችንም ለሕግ ለማቅረብ ብሎም ተጨማሪ ችግር ለማስቀረት መረጋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአጥፊዎቹ ዓላማ የሙስሊምን ማህበረሰብ ከሃይማኖታዊ እሴቱና ከስብዕናው ወርዶ እነሱ በሚፈልጉት አንሶ እንዲታይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ ወንጀለኞቹን ለሕግ ለማቅረብ ብሎም የእምነቱን እሴቶች ለማረጋገጥ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የጥፋትና የመለያየት አጀንዳ ባለመቀበል ሰላምን ሊያስቀድም ይገባል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋርም በትጋት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ጥፋትን በሌላ ጥፋት ለመድገም መነሳሳት የጸጥታ አካላት አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በእጅጉ ያደናቅፋል። በመሆኑም ሌላ ገጽታ ያለው መጠነ ሰፊ ጉዳት እንዳይከሰት ሕዝቡ ስሜቱን መቆጣጠርና ህመሙን ማስታገስ እንዳለበት መክረዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት የተፈጠረውን ችግር ወደ ሰላም ለመመለስ ብሎም ጉዳቱን ለመቀነስ ያደረገውን ጥረት ያደነቁት ኡስታዝ አቡበከር፤ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው በይበልጥ አጠናክሮ መሥራት ክልሉ ይጠበቅበታል ብለዋል። የጥፋቱ መንስኤ የሆኑት አካላት ተራ ቀስቃሽ ሳይሆኑ በደንብ የተደራጁና የጸጥታ አካላትንም እየፈተኑ በመሆናቸው ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ለቤተ እምነት መቃጠልና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ኡስታዝ አቡበከር ገለጻ፤ ነውርን በነውር መመለስ ኢትዮጵያዊነት እሴት ባለመሆኑ ከዚህ ድርጊት መቆጠብ ይገባል። አስቀድሞ ጥፋት መከላከል ሲገባ ይህ ሁሉ ጥፋት መከሰቱ ሁላችንንም ተሸናፊ ያደረገ አስከፊ ገጽታ ነው። ከድርጊቱ የምንማረው ጥፋት ለማስቀረት ፊት ወጥቶ መስዋእት እንኳ ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።
የመስጅድም ሆነ የቤተክርስቲያን ጉዳይ የእምነቱ ተከታይ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን አሁን ከተፈጠረው ችግር መረዳት ይቻላል ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ ሃይማኖት ሌላ ጉዳይ ሆኖ ስለሰብዓዊነት ሁላችንም የሚከነክን ነገር በመሆኑ ከአሁን በኋላ መሰል ችግር እንዳይፈጠር ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም