
ሀዋሳ ከወትሮው በተለየ መልኩ ደምቃለች። ዙሪያ ገባውን በሲዳማ ብሄር ባህላዊ አልባሳት ያሸበረቁ ወጣቶች፣ እናቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች ይታያሉ። በእጃቸው ላይ ከቀርክሃ፤ ከወይራና ከጽድ የተዘጋጁ ባህላዊ ምርኩዝ “ሲቆ” ይዘዋል። ሁሉም “አይዴ ጫምባላላ” በማለት በምላሹ “ኢሌ ኢሌ” ይባባላሉ። በአሉን ምክንያት በማድረግ እንኳን አደረሳችሁ የሚል ትርጉም አለው። ዋዜማውን የፍቼ በዓልና የአዲስ ዘመን መለወጫ የሆነውን ጫምባላላ በታላቅ ደስታና ተቀብለውታል። ዋናው የጫምባላላ በዓል የሚከበርበት ጉዱማሌ የተባለ ሰፊ ሜዳም በእለቱ በአባቶች ባህላዊ የ “ቂጣላ” ዜማ ደምቆ ውሏል።
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ታዳሚዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በተሳተፉበት በዓል ላይ “የፍቼ ጫምባላላ መሰረታዊ እሴቶች መሰረት የተጣሉት የሚታረቁበት ቂምና ቁርሾ የሚጠፋበት፣ እርቅና ፍቅር የሚጎለብትበት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ክብር የሚሰጥበትና አብሮነት የሚጠናከርበት ነው” ብለዋል። አሁን አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንፃር ይህ እሴት በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነም ይናገራሉ።
ፕሬዚዳንቱ “መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትን፣ መቻቻልን፣ መረዳዳትን፣ ተጋግዞና ተባብሮ ወደፊት መሄድን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል” በማለትም ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ በመሆኗ ለሁሉም ትበቃለች የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
በጉዱማሌ የፊቼ ጫምባላላን ለማክበር በእንግድነነት የተገኙት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፣ ላለፉት ዘመናት የሲዳማ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ ለመወሰን ታግሎና መስዋእትነት ከፍሎ ለዛሬው ቀን በቅቷል። ከአሁን ወዲህ ወደ ሰላም፣ ትምህርት፣ ልማት መመለስ አለበት ነው ያሉት።
“የሲዳማ ህዝብ ባህሉና የአገር ሽማግሌዎቹ ናቸው ጠንካራ ያደረጉት” የሚሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በዚህ እሳቤም መላው ኢትዮጵያውያን የውጭና የውስጥ ጠላቶቹ ያቀነባበሩትን ሴራ በዚህ መንገድ ማክሸፍ ይኖርበታል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
በፍቼ ጫምባላላ በዓል ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል የሆኑት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አንዱ ናቸው። እርሳቸው በኢትዮጵያ ላይ ጋሬጣ ሆኖ የቆየው “እኔ” ብቻ የሚል አስተሳሰብ ነው በማለት ይህ ዘመን እንዳበቃ ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ መሰረቷ እየጠነከረ ፍላጎቶቿን ለማሳካት እየተጋች ትገኛለች” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያዊነት እኛነት ነው። እኛ ውስጥ አብሮ የመኖርና የመተባበር እሴት አለ። የእኔ ሃይማኖትና ብሄር የበላይ ነው የሚሉት ኋላ ቀር አስተሳሰቦች መሆናቸውን ይገልፃሉ። ይህን መንገድ የሲዳማ ህዝብ በባህሉ አቃፊ መሆኑን በማሳየት የፍቅርና የትብብር አቅም መሆኑን በኢትዮጵያ ምድር ላይ እያስመሰከረ መሆኑን በመልዕክታቸው ላይ አንስተዋል።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል ከዚህ ቀደም ከነበሩት ስነስርዓቶች በተለየ የመላው ኢትዮጵያውያን “ባህላዊ ምሰሶ” መሆኑን ያስመሰከረ እንደሆነ በስፍራው የተገኙ እንግዶችና በክልሉ የሚኖሩ ብሄረሰቦች ሲገልፁ ተደምጠዋል። ፊቼ ጫምባላላ በዩኒስኮ ከማይዳሰሱ ባህላዊና መንፈሳዊ የሰው ልጅ ቅርሶች ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 መዝግቦ በይፋ እውቅና እንደተሰጠው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም