
አዲስ አበባ፡- መንግሥት አገርን አደጋ ላይ በሚጥሉ ጽንፈኞችና አክራሪዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶክተር) በአገራዊ ወቅታዊ የጸጥታና የሰብአዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ማንኛውንም ግጭቶችን የሚያባብሱና ግጭት አባባሽ የሆኑ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ አካላትን መንግሥት አይታገስም።
የግጭት ነጋዴዎችና ጽንፈኛ የሆኑ አክራሪ ኃይሎች የሚያተርፉት አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር፣ አንዱን አካባቢ ከሌለው አካባቢ በማጋጨት ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ብቻ ነው።
እንደ ሚኒስትሩ መግለጫ፤ ፍትሕን በመጠየቅ ሰበብ ሕዝበ ሙስሊሙን አነሳስቶ ከክርስትና እምነት ተከታይ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ደም ለማቃባት የሚደረግ እንቅስቃሴ በየትኛውም ሃይማኖት፣ እምነት፣ ሕግና ስርዓት የማይደገፍ ነው። አብሮነትንና አንድነትን የሚያናጋ ብሎም አገራዊ አንድነትንና ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በመግለጽ፣ ግጭቶችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፋት የሚደረግ የትኛውንም እንቅስቃሴ መንግሥት አይታገስም ብለዋል።
እንደ ለገሰ (ዶክተር) መግለጫ፤ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ ተቀብለው ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው በእኩይ ተግባር የተሳተፉ ወንጀለኞችን አንድ በአንድ በመልቀም ለሕግ ለማቅረብ የተጀመረው ተግባር ፈጥኖና ተጠናክሮ ይቀጥላል። አንድን ወንጀል በሌላ ወንጀል ለማካካስና ችግሩ እንዲወሳሰብ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከወንጀል ፈጻሚዎች እኩል የሚያስጠይቅ መሆኑን መታወቅ አለበት ብለዋል።
ሰሞኑን በተከሰተው ችግር ግጭት ለማስፋፋት ታዋቂ የማህበራዊ አንቂዎች ሳይቀር ግጭት አባባሽ የሆኑ ሀሰተኛ መልዕክቶችን ሲያስራጩ ታይቷል ያሉት ለገሰ (ዶክተር)፤ ታሪካዊ የሆኑ ጠላቶቻችን አጀንዳ ይዘው በሚሰሩ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል።
ችግሮቹ በተፈጠሩባቸው አካባቢዎች መንግሥት ከህብረተሰቡ፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በመቀናጀት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በግጭት የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር እያዋለ ነው።
አክራሪነትና ጽንፈኝነት እንዲስፋፋ ሆነ ብለው አቅደው የሚሰሩ የሽብር ኃይሎች አገራችን ወደ አለመረጋጋት እንድትገባ እየሰሩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት በመላ አገሪቱ ሕግና ስርዓት እንዲከበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ሰሞኑን የሽብር ጥቃት ለመፈጸም በተንቀሳቀሱ ኃይሎችና በሽፍታው ሸኔ ላይ የተጀመረው እርምጃ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰዱ እምርምጃዎችም ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያስታወሱት ለገሰ (ዶክተር)፤ የስንቅና የሎጂስቲክስ ማቅረቢያውን ጨምሮ በርካታ የሸኔ ቡድን አባላት ተደምስሰዋል፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላቱም መማረካቸውን አንስተዋል። በዚህም በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱን ለገሰ (ዶክተር) ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ በየብስና በአየር ትራንስፖርት የህክምና ቁሳቁሶች፣ አልሚ ምግቦች፣ መድኃኒቶች፣ በተጠናከረ መልኩ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ36 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና ቁሳቁሶች፤ 712 ሜትሪክ ቶን ጥቅል የህክምና መገልገያ ቁሶች በዓለም ጤና ድርጅት በኩል መጓጓዙን ጠቅሰዋል። እስካሁን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች አማካኝነት ከ50 ሜትሪክ ቶን በላይ መድኃኒት ወደ ክልሉ መጓጓዙንም አስታውሰዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም