
ነውረኛ ተግባር የሚፈጽሙ ሁሉ ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በሃይማኖት ግጭት ሰበብ መለያየትን የተመኙልን የታሪክ ቀበኞች ያሰቡት አልተሳካላቸውም ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ትናንት ሁለተኛው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖት ግጭት ሰበብ መለያየትን የተመኙልን ያሰቡት አልተሳካላቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመከባበር ያጌጠ ውብ ባህል ያላት አገር ናት። መለያየትን በሚመኙ መሳሳብን ሳይሆን መገፋፋትን በሚሹ የታሪክ ቀበኞች ኢትዮጵያውያንን ከቶውንም ሊነጣጥሉን አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል።
ላይበጠስ የተጋመደው አብሮነታችን በግጭት ጠማቂዎች የተነሳ አይላላም። እዚህም እዛም ብቅ ጥልቅ የሚሉና የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ አካላትንም ከንቱ ሙከራቸውን በአብሮነት መመከት ይገባል ብለዋል።
አብሮነታችን የማይላላ እና በጽኑ አለት ላይ የተመሰረተ ነው፤ በቀጣይም በመተባበር እና በመከባበር መርህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የእስካሁኑ የሃይማኖት ግጭት ሴራም የክርስትናና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች አማካኝነት ከሽፏል፤ ለዚህም መላው ሕዝብ ምስጋና እንደሚገባው ጠቁመዋል።
ሰላምን የሚሰብኩት ሃይማኖቶቻችን ለከፋፋዮች የማይመቹ መሆናቸውን ጠላቶቻችን ሊያውቁት ይገባል ብለዋል።
በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋሉ ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በታላቁ ረመዳን ወር በሃይማኖት ግጭት የተነሳ የተፈጠረው ሞትና ውድመት እጅጉን አሳዝኖናል። በድርጊቱም አፍረንበታል ያሉት አቶ ዣንጥራር፤ይህንን ወንጀል የሰሩ የትኛውንም አካላት በሕግ ፊት ቀርበው ቅጣቱን ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
እንደ መንግሥትም ጥፋተኞችን በተመለከተ የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ ያሉት አቶ ዣንጥራር፤ እንደዚህ አይነት ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ወንጀሎችን በአጭር መቅጨት ካልተቻለ አደጋው እየከፋ እንደሚሄድ አያጠያይቅም ሲሉ ተናግረዋል።
አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ሽፋን ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላትን ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነቱን ሴራ ልትሸከምበት የምትችልበት ትከሻ እንደሌላት መረዳት አለባቸው። በመሆኑም ሁሉንም በሰላምና በእኩልነት መቀበል ኃላፊነታችን መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ተመሳሳይ ጥፋቶች በመዲናዋ እንዳይከሰት ነዋሪው ከጸጥታና ደህንነት አካላት ጋር በትብብር ሊሰራ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች መሆን የማይገባቸው እና ኢትዮጵያውያንን የማይገልጹ ጸያፍ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
ነውረኛ ተግባር የሚፈጽሙ ሁሉ ተገቢው ህጋዊ ቅጣት ማግኘት አለባቸው ያሉት ኡዝታዝ አቡበከር፤ ይሁን እንጂ ጥፋትን በጥፋት ነውርን በነውር አናክመውም ሲሉ ተናግረዋል።
ቀሳውስቶችና የእስልምና ዕምነት አባቶች ይህን በአገራችን የተከሰተውን ጥፋት አውግዘዋል፤ይህ አንድነታችን ነው የሚያምርብን። ጥያቄያችንንም በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ አለብን ብለዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም