ዮሐንስ አባይ አማካሪ ድርጅት የአዲስ አበባ ስቴድየም ዕድሳትና ጥገና ዝርዝር ዲዛይን ለመሥራት፣ የግንባታ ሥራውን ለመከታተልና ኮንትራት ለማስተዳደር ከቀድሞው የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ከአሁኑ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር የውል ስምምነት ፈፅሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ድርጅቱ የዲዛይን ሥራዎችን ሠርቶ በወቅቱ ባለመጠናቀቅ፣ የሚጠየቀው የሥራ ትዕዛዞችን በወቅቱ ባለማረጋገጥ፣ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን እንደ አማካሪ ቀድሞ በመሥራት ለአሠሪ ባለማሳወቅ፣ ለተጠየቁ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ባለመስጠት፣ የሥራውን ጥራት የሚከታተሉ በቂ ባለሙያዎች በመስክ ላይ ባለመመደብ፣ የተመደቡ ባለሙያዎችም ቢሆኑ በመስክ ላይ ባለመገኘት፣ የፕሮጀክቱን አንገብጋቢነት በተደጋጋሚ እየተነገረ በተቃራኒው ሥራዎችን በማጉላላትና በጊዜ እንዳይጠናቀቅ በማድረግ ችግር እየፈጠረ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን ችግሮች በማብራራት በስብሰባዎች፣ በደብዳቤዎችና በስልክ ጥሪዎች እንዲስተካከሉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢደረግም ችግሩን ከመቅረፍና የመንግሥት ሀብትን ለመቆጠብ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሥራው እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ይልቅ አማካሪ ድርጅቱ ከነጭራሹ በመስክ ላይ ባለማግኘትና ሥራ ባለማሠራት ፕሮጀክቱን ወደ ባሰ ችግር እየከተተው መሆኑን ጨምሮ ገልጿል፡፡
በመሆኑም ሚኒስቴሩ የአዲስ አበባ ስቴዲየም ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ይሠራ ዘንድ በኮንትራትና በተሠጠው ትዕዛዝ መሠረት በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ተጨባጭ የኮንትራት አስተዳደር ሥራ እንዲገባ ለድርጅቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ጠቁሟል። ይህ ካልሆነ ግን በኮንትራቱ መሠረት እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከሃምሳ አመታት በላይ በርካታ ዓለምአቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮችን እንዲሁም ባህላዊና መንፈሳዊ ክንውኖችን ያስተናገደው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስቴድየም ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም የዕድሳት ሥራው መጀመሩ ይታወሳል።
ዕድሳቱ በቅድሚያ ካፍ የሰጣቸውን አስተያየቶች መሠረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑ በወቅቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የመጫወቻ ሜዳው፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የተመልካች መፀዳጃና የኤሌክትሪክ እንዲሁም የጽዳት ሥራዎችን የሚያካትት ይሆናል።
እድሳቱ በአንድ ዓመት እንዲጠናቀቅ ታቅዶ ሥራው ቢጀመርም፣ በታሰበው ጊዜ እንደማይጠናቀቅ የሚያረጋግጡ ማሳያዎች እየበረከቱ ናቸው። የእድሳት ሥራው በገንዘብ ረገድ ችግር ባይኖርበትም ከተጀመረ በኋላ ብዙ ውጣ ውረዶች ማጋጠማቸውና ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ሥራዎች መገኘታቸው በጊዜ ላለመጠናቀቁ በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰሞኑን በእንድ መድረክ ላይ በሰጠው ማብራሪያ ጠቁሟል።
የስቴድየሙ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያካሂድ መታገዱ ለእድሳቱ ምክንያት እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን የደረሰበት ሁኔታም በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ከሦስት ወር በፊት የመስክ ጉብኝት ተደርጎበታል፡፡
በጉብኝቱም ወቅት አራት የተጫዋቾች መልበሻ፣ የዳኞች ማረፊያ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ክፍሎች እድሳት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ታይቷል፡፡ ካፍ በዋናነት ትኩረት የሚያደርግበት የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ግንባታውም በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ተነግሮ ነበር።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ በየጊዜው ከሚያደርጉት ጉብኝት አንጻር የመልበሻ ክፍሎች እድሳቱ በተያዘለት ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ ከመጫወቻ ሜዳው የሳር ተከላ ጋር በተያያዘ ግን እድሳቱን በማከናወን ላይ የሚገኘው ተቋራጭ ልምድ እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል።
ይህንን ሥራ ሊያከናውኑ የሚችሉ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም በተካሄደው ጉብኝት እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ከአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ተጋባዡ ካምፓኒ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በፈረንሳይ መንግሥት በመከልከሉ ሊቀር መቻሉ ተጠቁሟል።
በጉብኝቱ ወቅት የስቴድየሙ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ እና የግንባታ ደረጃው 40 ከመቶ ላይ እንደደረሰም በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሞ ነበር። በ100 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅም በእቅድ ተይዞ ግንባታው በመከናወን ላይ እያለ ነው ለአማካሪ ድርጅቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው።
በኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች አለመኖራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የትኛውንም አህጉር አቀፍ ውድድር እንዳታስተናግድ መታገዷ ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል የወጣ ሲሆን፤ በቀጣዩ ወር መጨረሻም ውድድሮቹ ይጀመራሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ መኖሩ ለስፖርት ቤተሰቡ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም