በስፖርቱ ዓለም እጅግ አስደናቂ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ረጅም ርቀትን በሩጫ የመሸፈን ብቃት ነው፡፡ በተለይ 42 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነው ማራቶን ከፍተኛ ጽናትና በልምምድ የዳበረ ጥንካሬን ስለመጠየቁ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህንን ፈታኝ ውድድር በተደጋጋሚ ከማሸነፍ ባለፈ የሚገቡበትን ሰዓት በማሻሻል ሳይንስ ሊተነብየው ከሚችለውም በላይ የሰው ልጅ እምቅ አቅም ምን ድረስ እንደሆነ ማሳያ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
የስፖርት ባለሙያዎችም ከዚህ በመነሳት እንዲሁም እጅግ ፈታኝ በሆነው ይህንን ውድድር አሸንፈው ስኬታማ ለመባል የቻሉበትን ምስጢር ለማወቅ ተደጋጋሚ ጥናቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም ሌላኛውን አስደናቂ ውጤት ያገኙ ሲሆን፤ ይኸውም በውድድር አሸናፊ ሊሆኑ የቻሉት ምናልባትም በውድድር ከሚሸፍኑት ርቀት በርካታ እጥፍ የሚሆኑ ኪሎ ሜትሮችን በልምምድ ወቅት በመሮጣቸው ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡
‹‹ስፖርትስ ሜድስን›› የተባለው ጆርናል ያወጣው ጥናት እንደሚያመላክተው ከሆነም የማራቶን አትሌቶች በሳምንት በአማካይ ከ160 እስከ 220 ኪሎ ሜትር በልምምድ ወቅት ይሸፍናሉ፡፡ የመም ረጅም ርቀት እንዲሁም የጎዳና 5 እና 10 ኪሎ ሜትር ሯጮች ደግሞ በአማካይ በሳምንት ውስጥ ከ 130–190 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት በመሮጥ ልምምድ ያደርጋሉ፡፡
ይህንን ከባድ ልምምድ ለመስራትም ሆነ በውድድሮች ላይ ውጤታማ ለመሆንም አትሌቶችም ሆኑ አሰልጣኞቻቸው በቅድሚያ የስልጠና እና የውድድር መርሃ ግብርን ማዘጋጀት የግድ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ከ59 የሚሆኑ ታዋቂ የጎዳና ላይ አትሌቶች እና 16 አሰልጣኞች በተሰበሰበው ናሙና በተጠናቀረው ጥናት መሰረት የአትሌቶችና አሰልጣኞቻቸው ቀዳሚ ስራ የስልጠና መርሃ ግብር ማውጣት እንዲሁም በዓመቱ መጀመሪያ በየትኛዎቹ ውድድሮች መሳተፍ እንደሚፈልጉ ለይተው እቅድ ማውጣት ነው፡፡ ይህ የልምምድ መርሃ ግብር እረፍትንም የሚያካትት ይሆናል፡፡
የመም ረጅም ርቀት አትሌቶች በዓመት ውስጥ ተደጋጋሚ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንደመሆኑ የልምምድና የእረፍት ጊዜያቸውም በዛው ልክ የታቀደ እና አጭር የጊዜ ገደብን ያካተተ ይሆናል፡፡ የጎዳና በተለይ የማራቶን ሯጮች ግን ከመም አትሌቶች በተለየ መልኩ የልምምድም ሆነ የእረፍት ጊዜ ብቻም ሳይሆን የውድድር ተሳትፎ ሂደት ይኖራቸዋል፡፡
አንድ አትሌት በዓመት ውስጥ ከሁለት እስከ ስድስት ውድድሮች ላይ ብቻ የሚሳተፍ ሲሆን፤ በውድድሮቹ መካከል ደግሞ እስከ ሶስት ወራት የሚደርስ የእረፍት ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡፡ የልምምድ ሁኔታውም የተለየ ሲሆን የረጅም ርቀት አትሌቶች በውድድር ወቅት ከሚሮጡበት ፍጥነት ባነሰ(እስከ 80 በመቶ የቀነሰ) መልኩ ለልምምድ የተያዘላቸውን ርቀት እንዲያጠናቅቁ ይመከራል፡፡ ይኸውም ከሶስት እስከ አምስት የሚሆነውን ርቀት በአንድ ሰዓት ውስጥ መሮጥ ሲሆን፤ ምርጥ አሰልጣኞች ይህንን በማመጣጠን በምን ሁኔታ ወደፊት መስፈንጠር ይቻላል የሚለውን በሚገባ ያሳያሉ፡፡
በልምምድ ወቅት አካላዊ ስሜትን ማዳመጥና መቆጣጠርም መሰረታዊ ነገር መሆኑን ከአትሌቶቹ የተገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ጥናቱ ያመላክታል። ልምምዱን ተከትሎ በውስጣዊ የአካል ክፍሎችም ሆነ በውጫዊ አካላት ጫና መፈጠር አለመፈጠሩን መለየትና ከተቻለም መዝግቦ በማስቀመጥ ምን መስራት ይገባል እንዲሁም የትኞቹ መቀነስ አለባቸው የሚለውን ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህም ስልጠናው በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመራ እና ወደ ውጤታማነት መራመድ እንዲቻል ምቹ መደላደልን ይፈጥራል፡፡ ስልጠናው በዚህ መልክ ከቀጠለ በኋላ ልምምድን እየቀነሱ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ ከሁለት እስከ ሶስት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ቀድሞ ከነበረው የልምምድ አጠቃላይ ሁኔታ እና መጠን ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን መቀነስ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ውድድሮች ለመካሄድ ከሰባት እስከ አምስት ቀናት ሲቀሩትም በተመሳሳይ መልኩ ልምምድን መቀነስ በበርካታ አትሌቶች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2014