የ2014 ዓም የክለቦችና ክልሎች አገር አቀፍ የውሃ ዋና ሻምፒዮና ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በቢሾፍቱ መኮንኖች ክበብ የመዋኛ ገንዳ እየተካሄደ ይገኛል። በተለያዩ የውድድር አይነቶች ባለፉት ቀናት በተደረጉ የፍጻሜ ፉክክሮችም የአማራ ክልል ዋናተኞች በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችለዋል።
ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 4/2014 ዓ.ም በተደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች ብቻ የአማራ ክልል ስድስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠቅልሎ በመውሰድ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን ውጤት ከወዲሁ እየሰበሰበ ይገኛል። ክልሉ በበላይነት ካጠናቀቀባቸው ውድድሮች መካከል የስምንት መቶ ሜትር የወንዶች ነጻ ቀዘፋ አንዱ ሲሆን ጥላሁን አያል ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። አማኑኤል አዱኛና አብዲ ሁሴን በተመሳሳይ ከአማራ ክልል የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ሆነዋል።
በመቶ ሜትር ሴቶች ጀርባ ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር ስፍራሽ ደምሴ ከአማራ ክልል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን ሐና ሽመልስ ከኦሮሚያ ፖሊስ የብር ሜዳሊያ አስመዝግባለች። እንጉዳይ አለሙ ደግሞ ከአማራ ክልል ቀሪውን የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፋለች።
በሃምሳ ሜትር የወንዶች ደረት ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር እዮብ ደባሱ ለአማራ ክልል ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ ቢኒያም ፀጋዬ ለቢሾፍቱ ከተማ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። ቀሪውን የነሐስ ሜዳሊያ ወንድወሰን ዘነበ ከኦሮሚያ ፖሊስ ማሸነፍ ችሏል። በሻምፒዮናው እየተሳተፉ ከሚገኙ ጥቂት ክለቦች አንዱ የሆነው ዳዊት ሕንጻ ተቋራጭ በመቶ ሜትር የሴቶች
ደረት ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር በብርሀን ደመቀ አማካኝነት የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ ችሏል። በዚህ ውድድር ቅድስት ወግደረስ ከኦሮሚያ ፖሊስ የብር ሜዳሊያ ስታሸንፍ ቅድስት ካሴ ከአማራ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቃለች። ዳዊት ህንጻ ተቋራጭ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ በሃምሳ ሜትር የሴቶች ቢራቢሮ ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድርም የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግቧል። ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውሃ ዋና ውድድሮች በመወከል የምትታወቀው ራሔል ፍስሐ የውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን በእምነት ደመላሽ ከአማራ ክልል የብር ሜዳሊያ፣ ብርሃን ደመቀ ከዳዊት ሕንፃ ተቋራጭ የነሐስ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ጠንካራ ፉክክር አድርገዋል።
በመቶ ሜትር ወንዶች ቢራቢሮ ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር ጥላሁን አያል ለአማራ ክልል ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበ ዋናተኛ ሲሆን ከተመሳሳይ ክልል አማኑኤል አዱኛ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችሏል። እዮብ እያሱ ከሲዳማ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ክለቦችና ክልሎች ጠንካራ ፉክክር ባደረጉበት አራት በመቶ ሜትር የሴቶች ነፃ ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር አማራ ክልል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ኦሮሚያ ፖሊስ የብር ሜዳሊያና ቢሾፍቱ ከተማ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል ። በተመሳሳይ አራት በሁለት መቶ ሜትር የወንዶች ነፃ ቀዘፋ የፍፃሜ ውድድር አማራ ክልል የወርቁን ሜዳሊያ ሲወስድ ኦሮሚያ ፖሊስ የብር ሜዳሊያ፣ ቢሾፍቱ ከተማ የነሀስ ሜዳሊያ በማግኘት ውድድራቸውን ያጠናቀቁ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኛው መረጃ ያመላክታል ።
በውድድሩ የአማራ፤ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ተሳታፊ ሲሆኑ የድሬዳዋ ከተማ እና የቢሾፍቱ ከተማ ተወዳዳሪዎችም በተለያዩ ፉክክሮች ተሳታፊ ናቸው። በክለብ ደረጃ ዳዊት እምሩ የሕንፃ ተቋራጭ፤ ሳምሶን ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ እና ኦሮሚያ ፖሊስ የሚሳተፉ ሲሆን አቻላ ያኮቤ በግል ተወዳዳሪ በመሆን ቀርቧል።
‘’ስፖርት ለሰላም ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የ2014 ዓ.ም የክልሎች እና የክለቦች የውሃ ዋና ቻምፒዮና እስከ ሚያዝያ 8/2014 ዓም በተለያየ የውድድር አይነቶች በርካታ ፉክክሮችን አስተናግዶ አሸናፊዎቹ የሚለዩ ይሆናል።
ሻምፒዮናው በዋና ስፖርት ተወዳዳሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ፣ ለ2022 አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን በመወከል ምርጥ ስፖርተኞች የሚመረጡበት እንደሚሆን ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014