
ሰሞኑን ከመራጭ ሕዝብ ጋር እየተካሔዱ ባሉ ውይይቶች ላይ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል በዋናነት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለ ሌብነት፣ ለውጡን የሚመጥን የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን የሚያመለክቱ እና የመንግሥት ሠራተኛው በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ እንደሚገኝ የሚያመለክቱ ናቸው።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቢሯችን ድረስ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምን ይላል? በማለት ጠይቁልን መባሉን ተከትሎ የኮሚሽኑን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ መሐመድ ሰዒድን ጠይቀን እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡-በአገራችን የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ በሲቪል ሰርቪሱ ላይ የተደረገው የሪፎርም ሥራ ምን ደረጃ ላይ ነው ?
አቶ መሐመድ፡- በሲቪል ሰርቪሱ እየተካሔደ ያለውን የሪፎርም ሥራ በሚመለከት ቀደም ሲል እንደሚታወቀው በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሶስት አሥርተ ዓመታት የመንግሥትን የመፈፀም እና የማስፈፀም አቅም ክፍተትን ለመሙላት ሲተገበሩ የነበሩ የተለያዩ አሠራሮች እንደነበሩ ይታወቃል። የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ሲተገበርም አምስት ንዑስ ፕሮግራሞች ነበሩ። ፕሮግራሞቹ የራሳቸው ጥንካሬ እና ድክመት ያለባቸው መሆናቸውም የሚካድ አይደለም።
በዋነኛነት የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራምን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ መሣሪያዎች ተግባራዊ ተደርገዋል፤ ቢ ፒ አር፣ ቢ ኤስ ሲ፣ የለውጥ ሠራዊት ፣ የዜጎች ቻርተር እና ካይዘን መተግበራቸው አይዘነጋም።
የእነዚህ መተግበር ከነችግራቸውም ቢሆን አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናል። ነገር ግን የራሳቸው በጎ አስተዋፅኦ ነበራቸው ተብሎ ቢታመንም ግን ያመጣሉ ተብሎ ከታሰበው የተገልጋይ እርካታ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላመጡም። እንደውም ችግሩ እየተባባሰ የአገልግሎት አሰጣጣችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በቅሬታ እና በእሮሮ የተሞላ እንዲሆን አድርጓል።
አሁን ላይ እንደሚሰማው የአገልግሎት አሰጣጡ ሲፈተሽ አገልግሎት በገንዘብ እየተገዛ መሆኑ እየታየ ነው።
ክፍተቱ የመጣው የለውጥ መሣሪያዎቹ ችግር የነበረባቸው በመሆናቸው ሳይሆን ምክንያቱ ሌላ ነው። አንዳንዶቹ ከውጪ የተወሰዱ ናቸው። በውጪው ዓለም ያደጉ አገሮች ተጠቅመውባቸው ውጤት ያስገኙ ናቸው። ወደ እኛ አገር ስናመጣው የፈፀምንበት አግባብ የራሱ የሆነ ውስንነት ስለነበረበት ነው። አመራሩም ሆነ ሠራተኛው ለውጡን በባለቤትነት ከመምራት አንፃር ያለ ውስንነት ነው። ለውጡ ቁርጠኝነትን፣ ለሥራው መሰጠትንና ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። ለውጥ የሚከብድ ነው። ይህንን አውቆ ከአመራር እስከ ፈፃሚ ድረስ በባለቤትነት ይዞ ለውጡ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከማድረግ አንፃር ጉድለቶች እንደነበሩበት የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን፡- ለውጥ ሲሉ እነቢ ፒ አርን ማለትዎ እንጂ የአሁኑን ለውጥ በሚመለከት ማለትዎ አይደለም?
አቶ መሐመድ፡- አዎ! 14ቱን የአቅም ግንባታ ፕሮግራሞች እና አምስቱን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ማለቴ ነው። የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ ቢ ፒ አር፣ ቢ ኤስ ሲ፣ ካይዘን እና የዜጎች ቻርተር ሲተገበሩ ነበር።
የመንግሥትን የማስፈፀም አቅም ስንል ሶስት ነገሮችን ነው። በአደረጃጀት፣ በአሠራር እና በሰው ኃይል ማለት ነው። ለምሰሌ ቢ ፒ አር አደረጃጀትን ይቀይራል። ለተገልጋይ ምቹ ማድረግ እና የሥራ ፍሰትን የማቀላጠፍ ሥራዎችን ያደራጃል። ቢ ኤስ ሲ ደግሞ ቆጥረን የምንሰጥበት፤ የሰጠነውን ማለትም አፈፃፀምን ወይም ፍሬውን ቆጥረን የምንረከብበት ነው። የአፈፃፀም መለኪያ መሣሪያ ነው።
የተቋምን ስትራቴጂ እስከ ታች ድረስ የምናወርድበት ነው። የግንኙነት መሣሪያም ነው። ነገር ግን ይህንን ጨምሮ ሌሎችም የለውጥ መሣሪያዎች ተጠቅሞ እና በአግባቡ ይዞ ውጤት ከማምጣት አንፃር በአመራርም ሆነ በባለሙያ በኩል በርካታ ክፍተቶች በመኖራቸው ውጤታማ አላደረገንም። አሁን ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተገልጋይ እርካታ መጨመር ሲገባው የመቀነስ ሁኔታ እየተስተዋለ ነው።
አዲስ ዘመን፡-የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮች ዛሬም እንዳልተቀረፉና በተለይ በአንዳንድ ተቋማት ተባብሰው እንደቀጠሉ ይታወቃል። ለእዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የበፊቶቹ የለውጥ መሣሪያዎች ውጤታማ ያልሆኑት ፖለቲካው እና አገልግሎት አሠጣጡ ባለመነጣጠሉ ስለመሆኑ ይገለፃል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ መሐመድ፡– ትክክል ነው። እነዚህ የለውጥ መሣሪያዎች ስኬታማ ያልሆኑት አተገባበር ላይ በነበረው ክፍተት ነው። በተቋም ደረጃ ለውጥ ያመጣሉ፤ ሕዝብን ያረካሉ፤ አገርን ለትልቅ ደረጃ ያደርሳሉ፤ የኢኮኖሚ ለውጡን ያሳካሉ ተብለው ቢመጡም ሲፈፀሙ ግን ከፖለቲካ ጋር መቀላቀሉ ችግር ፈጥሯል። ለምሳሌ የለውጥ ሠራዊት በሚል አንድ ለአምስት በማደራጀት ጠንካራው ደካማውን እየደገፈው በትጋት በመሥራት ውጤታማ መሆን እንዲቻል ነበር።
ኮሪያ፣ ጃፓን እና ሌሎች አገሮች የለውጥ መሣሪያ በሚል አሁንም ድረስ ለውጥ ያመጡበት ነው። ካይዘንም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን ሥራን መገምገሚያ ሳይሆን እስከ ማኅበራዊ ግንኙነት ድረስ የዘለቀ የፖለቲካ መገምገሚያ መሣሪያ ሆነ።
አሁንም ድረስ በመንግሥት ተቋማት እንዲፈፀም የምናደርገው የዜጎች ቻርተር አለ። የዜጎች ቻርተር ከእንግሊዝ የተወሰደ ሲሆን፤ በ1990ዎቹ ሥራ ላይ የዋለ ነው። የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን በጊዜ፣ በመጠን፣ በወጪና በጥራት ተገማች የሚያደርግ ነው። ይህንንም ለተገልጋያቸው ቃል ይገባሉ። ይህ ዜጎች መብታቸውን የሚጠይቁበት ሥርዓት ነው። በጣም ሳይንስ ነው።
ተቋማት ለይስሙላ ያዘጋጃሉ። ነገር ግን የሼልፍ ቀለብ ከመሆን የዘለለ አይደለም። ለተገልጋዩ እና ለዜጋው ጠብ የሚል መሻሻልን አልፈጠረልንም። የፈፀምንበት እና ያስፈጸምንበት ክፍተት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ብልሹ አሠራርና ሌብነት መስፋፋቱን አገልግሎት ፈላጊዎች ይናገራሉ። ለመሆኑ እነዚህ ችግሮችን ለማቃለል በእናንተ በኩል ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ መሐመድ፡– ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች አፈፃፀም ላይ ጉድለት ነበረባቸው ያስባለው አንዱ ምክንያት ለሁሉም ተቋም አንድ አይነት የለውጥ መሣሪያ እንዲጠቀሙ በመደረጉ ነው። ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት መጠን ያለው ጃኬት እንዲለብስ ማድረግ ማለት ነበር። ጃኬቱ ለአንዳንዱ ይጠባል፤ ለአንዳንዱ ይሰፋል፤ ለአንዱ ሲያጥር ለሌላው ይረዝማል።
የተማከለ የለውጥ ሥራ ነበር። አሁን ግን በአገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ፤ ያልተማከለ የለውጥ መሣሪያ ለመተግበር ታስቧል።
ተቋማት ለሥራቸው የሚመቻቸውን የለውጥ መሣሪያ መተግበር ይችላሉ። ኮሚሽኑ ተቋማት የሚፈልጉትን እና የመረጡትን የለውጥ መሣሪያ ላይ የማማከር፣ የሥልጠና፣ የክትትል ድጋፍ እና ሌሎች የድጋፍ ሥርዓቶችን ያደርጋል። ይህ ሲባል ሁሉም መንግሥታዊ አገልግሎትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሥራዎችን በኮሚሽኑ በመንግሥት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ፍኖተ ካርታ ላይ የተቀመጡ ነገሮች መሆን እንዳለባቸው መዘንጋት የለበትም። የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያዎች አሉ።
አንዱ የዜጎች ቻርተር ነው። ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን ተገማች ማድረግ አለባቸው። በጊዜ፣ በመጠን እና በጥራት የሚሠሩትን ማሳወቅ አለባቸው። ከተገልጋዮቻቸው ጋር መግባባት ይጠበቅባቸዋል። ከተገልጋይ ጋር ከተግባቡ በኋላ ባስቀመጡት መሥፈርት መሠረት አገልግሎት መሥጠት አለባቸው። ባይሠጡ ተጠያቂ መሆን አለባቸው።
ዜጋው ለሚዲያ ሊያጋልጣቸው ይችላል። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ፣ ለእንባ ጠባቂ ለተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋማት ሊጠቁምባቸው ይችላል። አገልግሎት አሰጣጥን በገንዘብ ለሚሰጥ ተቋም ሚዲያው ሊያጋልጠው እና ሊያሳፍረው ጥሩ የሠራውንም ሊያበረታታው ይችላል።
የተለወጠ ዘመን ላይ ያለ የተለወጠ ዜጋ አዳጊ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ይፈልጋል። ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ወደ ቴክኖሎጂ መቅረብ አለበት። አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተገልጋይን በትህትና እና በክብር አነጋግሮ መረጃ መሥጠት አንድ ችግር ነው።
ይህን ችግር የሚፈታ የዜጎችን የአገልግሎት ቅሬታ የሚቀርብበት መመሪያ ተዘጋጅቶ የድሮ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የአሁኑ ፍትህ ሚኒስቴር አጣርቶት ለሁሉም ተቋማት ተልኳል። የዜጎች የአገልግሎት ቅሬታ የሚቀርብበት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ታምኖ እየተሠራ ነው።
በዚህች አገር ላይ ያለው ሌላው ትልቁ ችግር ዜጎች ሕገመንግስቱ በፈቀደላቸው የመገልገል መብታቸው በገንዘብ እየተቀየረ መሆኑ ነው። የእዚህ መንስኤው በዚህች አገር ላይ ተጠያቂነት ባለመኖሩ ነው። ያጠፋ አመራር ሲጠየቅ አይታይም።
አገልጋይን ያንገላታ፣ ያለአግባብ ያመላለሰ ያመናጨቀ ባለሙያ ሲጠየቅ አይታይም። ሕጉ ይላል፤ ነገር ግን ማን ይጠይቅ? ይህ ሥርዓት መኖር አለበት እያልን ነው። ጠዋት መግባት እና ማታ መውጣት መሥራት አይደለም። ተገልጋዩን አርክቻለሁ ወይ? ብሎ ቢሮ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን ተቋማት የተገልጋዮቻቸውን እርካታ ማስጠናት እና ጉድለቶችን ማወቅ አለባቸው።
ሌላው መሠረታዊ ነገር በሥርዓት ደረጃ እየተዘረጋ ያለው ለተገልጋዩም ሆነ ለአገልጋዩ፤ ሠራተኛው ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት መሥጠት የሚያስችለውን ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር ነው።
ይሄ የሠራተኛውን የዕውቀት እና የአስተሳሰብ ክፍተት ካለበት የክህሎት ክፍተቱን መሙላት ይጠይቃል። ለተገልጋዩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያመች በቂ ግብዓት አለው ወይ? ብሎ ያንን መሙላት ያስፈልጋል። ለእናቶች እና ለእህቶች ሕፃን ልጆች ላላቸው ሠራተኞች የሕፃናት ማቆያ መኖር አለበት። ሠራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ቁርስ እና ምሳ የሚያገኝበት ካፍቴሪያ መኖር አለበት። ከመንግሥት የሥራ ሠዓት ቀንሶ ስኳር ፍለጋ ወረዳ ሄዶ መሠለፍ የለበትም።
እዛው አገልግሎት በሚሠጥበት ተቋም የሚሸምተውን ማግኘት አለበት። በተቋማት በተመጣጣኝ ወለድ የቁጠባ ማኅበር ማደራጀት ያስፈልጋል። የትራንስፖርት አቅርቦት መኖር አለበት። የተጀማመረ ነገር አለ። ግን አሁንም ትራንስፖርት ላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሌላው ትልቁ ነገር ቤት ነው።
የመንግሥት ሠራተኛው አራት ሺህ ብር ተቀጥሮ ቤት ስንት ብር ይከራያል? ነባሩም ሠራተኛው ከከተማ ርቆ ስለሚከራይ አገልግሎት ሰጪው በሚፈልገው ሰዓት መገኘት አይችልም። ጠዋት ይረፍድበታል። ማታ ፈጥኖ ይወጣል። ስለዚህ ለአገልግሎት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የቤት አቅርቦት መኖር አለበት።
የመንግሥት ሠራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በቂ አይደለም። በእርግጥ ደሞዝ መጨመር የኑሮ ውድነትን ያባብሳል። ገበያውን ለማረጋጋት ታስቦ ጭማሪ ቢቆምም ለሠራተኛው ማሰብ ይገባል ብዬ አስባለሁ። ይሄ ሲኖር ሰራተኛው ቀልጣፋ አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል። በእነዚህ ላይ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማሻሻያ እርምጃዎች ብለን በፌዴራል ተቋማት ከላይ የተጠቀሰው እንዲሠራ ክትትል እና ድጋፍ እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሲቪል ሰርቫንቱ ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥ በየጊዜው የሚደረጉ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ መሐመድ፡- ሠራተኛው ተገልጋይ ደሞዝ ከፋይን በሚመጥን መልኩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያለበት ክፍተት በእርግጥም መሞላት አለበት። እዚህ ላይ የአገልጋይነት ስሜት ማነስ ሊሆን ይችላል። የክህሎት ችግር ወይም የዕውቀት ውስንነት ሊኖር ይችላል። የግብዓት እጥረትም ያጋጥማል።
ይህንን እየፈተሹ መሙላት ያስፈልጋል። ይህ ሲሞላ የመፈፀም እና የማስፈፀም አቅም ክፍተት እየተሞላ ሲሄድ በአደረጃጀት፣ በአሠራር እና በሰው ኃይል ላይ ትልቅ ሥራ ሲሰራ ውጤት ማምጣት ይቻላል።
የሰው ኃይል ላይ ካልተሠራ አደረጃጀት ቢያምር ቢሮ ቢሽቀረቀር ዋጋ የለውም። ተቋማት በዋናነት የሰው ኃይላቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለባቸው። ተጠያቂ መሆን ያለበትን ተጠያቂ ማድረግ ይገባል። የመንግሥት ሠራተኛ ማለት የመንግሥት ፖሊሲን አስፈፃሚ ነው። የፈለገው የፖለቲካ አመለካከት ቢኖርም ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤት ሲገባ ገዢው ፓርቲ ወይም የወቅቱ መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች ያለምንም መሸራረፍ በውጤታማነት መፈፀም የግድ ነው።
ይሔ በሲቪል ሰርቪስ መተዳደሪያ ሕግ በ1064/2010 ላይ ተቀምጧል። ሲቪል ሰርቪሱ በሚመራበት ሕግ ላይ ማንኛውም ሠራተኛ ቃለ መሐላ ፈፅሞ ሲቀጠር ማንኛውም ሠራተኛ ያለምንም አድሎ ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ይጠበቃል።
ያለምንም ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅም እና መደለያ አድሎ ሳይፈፅም የመሥራት ግዴታ አለበት። አቅም ሲባል ተቋማዊ አቅም ማለት ነው። የሠራተኛ አቅም ሲባል በክህሎትም፣ በአገልጋይነት አስተሳሰብም በሥነምግባር ማለትም የሙያዊ ሥነ ምግባር ላይ ክፍተት አለ ከተባለም ያ ተጠንቶ መሞላት አለበት። የምንዘረጋው የአሠራር ሥርዓት ያንን ክፍተት ለመሙላት የሚያግዙ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከፍ ብለው የአገልግሎት አሠጣጡ ላይ ያሉ የሌብነት እና መሠል ችግሮችን ለመከላከል አመራርም ሆነ ባለሙያን ተጠያቂ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል? ከቋሚ ኮሚቴ ግምገማ ባሻገር በሌላ በኩል ምን መሠራት አለበት? የእናንተ ሚናስ ምን ያህል ነው?
አቶ መሐመድ፡– ከተጠያቂነት አንፃርም ማንም ሰው ባጠፋው ልክ መጠየቅ አለበት። ለዜጋ የሚገባውን አገልግሎት ባለመስጠት ቀርቶ በጥራት እና በፍጥነት ውጤታማ ሆኖ አገልግሎት አለመስጠት ያስጠይቃል። ነገር ግን የሚጠይቅ ስለሌለ እንጂ ያስጠይቃል። በእኛ በኩል ይሄ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ በየደረጃው ተጠያቂ የሚያደርጉት ተቋማት ናቸው ብለን እናምናለን። ራሳቸው ተቋማት ብቻ አይደሉም፤ የዴሞክራሲ ተቋማትም ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
ተጠያቂነት ማለት እስርቤት ማስገባት ወይም ፍርድ ቤት መገተር ብቻ አይደለም። ያልሠራውን የበደለውን ተቋም በሚዲያ ማሳጣትም ተጠያቂነትን ማስፈን ነው። እኛ አገር ላይ ሕዝብን አስለቅሷል ተብሎ የሚነገርለት የትኛው ተቋም ነው?፤ የምናየው እኛ ይሄን ሠርተናል ጥሩ አድርገናል ሲል ብቻ ነው። ነገር ግን ያለአግባብ የእዚህ መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ገንዘብ ጠይቋል ብሎ ማጋለጥ መለመድ አለበት።
ለዚህ በዋናነት ተጠያቂ ማድረግ ያለባቸው ተቋማቱ ራሳቸው ቢሆኑም በሌላ መልኩ በአገር ደረጃ የተዘረጉት የክትትል እና የቁጥጥር አካላት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሚዲያውም መከታተል አለበት ብዬ አስባለሁ። እኛ የምናደርገው የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እና መደገፍ ነው። ችግሮችን ማጥናት ነው። ችግሮችን አጥንተን እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ እንሰጣለን። ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለቋሚ ኮሚቴ ለሚዲያም ግብረመልስ የመስጠት ሥራ እንሠራለን።
ዋናው ሥራ የአሠራር ስርዓት የመዘርጋት የመደገፍ እና ክፍተቶችን እያጠኑ የመፍትሔ እርምጃ የማቅረብ ሥራ ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡-ከለውጡ በፊት ተጀምሮ የነበረው የሲቪል ሰርቫንቱን ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ለማቀራረብ የተጀመረው “የሥራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰን” የፖይንት ሬቲንግ ሥራ ምን ላይ ደረሰ?
አቶ መሐመድ፡- ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የሚለው የሥራ ምዘና እና የደረጃ አወሳሰንን በሚመለከት ሥራዎችን መዝኖ ደረጃ መሥጠት ላይ ያተኩራል። ለሠጠው ደረጃ ክፍያን ይበይናል። እርሱ ሥራ በፕሮጀክት ተይዞ ብዙ ጊዜ የቆየ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሥራ ነው። ሥርዓቱ አዲስ በመሆኑ እዚህም እዚያም ቅሬታዎች ሊነሱ ይችላሉ። በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የተዘበራረቀ የተለያዩ ስኬሎችን ወጥ ለማድረግ የተሠራ ነው። እዚህ ላይ የሚሠራው ክፍል ሌላ በመሆኑ ብዙ ለማለት እቸገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የመንግስት ሠራተኛው በተለይ አሁን ባለው ሁኔታ በኑሮ ውድነት ጉዳት እንዳይደርስበት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ መሐመድ፡– ይህም ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን የአገር አቅም ይጠይቃል። ይህ ሲደረግ በገበያው ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫናም ይታያል። እኛ አገር ላይ ለሠራተኛው መቶ ብር ተጨምሮ፤ ነጋዴው ሁለት መቶ ብር ጨምሮ ይጠብቃል።
አንዳንዴ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝንበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም ሆኖ ግን አያስፈልግም እያልኩ አይደለም። መንግሥት ከአገር አቅም አንፃር አይቶ መፍትሔ መሥጠት እንዳለበት በግሌ አምናለሁ። ነገር ግን ከጥቅማ ጥቅም አንፃር ይሄ ሥራ የሚሠራው በመንግሥት ነው።
መንግሥት ሲቪል ሠርቪስ ኮሚሽንን አጥና ሲለው ኮሚሽኑ ያጠናል። የአገር አቅምን እና ሁኔታዎችን አይቶ ለመንግሥት ሠራተኛው ደሞዝ መጨመር እፈልጋለሁ ሲል ሲቪል ሰርቪስ አጥንቶ ያቀርባል። ሲፀድቅ ይከፈላል። ከዛ ይልቅ ግን ቀድሞ የእርከን ጭማሪ ነበር። የእርከን ጭማሪው ከታገደ አስርተ ዓመታትን አሳልፏል።
ይሄ በሠራተኛውም ዘንድ ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን በአገልግሎት አሰጣጡም ላይ ጫና አሳድሯል። ወደ ፊት ይታሰብበታል ብዬ እገምታለሁ።
ሌሎች በአፈፃፀም ላይ የተመሠረቱ የሠራተኛው ትጋትን የበለጠ የሚጨምር ሌሎችን ደግሞ አፈፃፀምን መሠረት ያደረገ ማበረታቻ ወደ ፊት የሚታሰብበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ መሐመድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014