
በዋና ከተማዋ ጁባ ውስጥ የሚገኘውን የምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻርን መኖሪያ ቤትን ከበው የነበሩት የደቡብ ሱዳን መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው መልቀቃቸው ተገለጸ።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ በሬክ ማቻር መኖሪያ ቤት ዙሪያ ተሰማርተው የነበሩት ኃይሎች ተነስተዋል።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ የፕሬስ ክፍል ኃላፊ ፖክ ቦዝ ባሉዋንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማቻር ዛሬ ሰኞ ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ገብተው መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው።
የምክትል ፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ከሰዓት በኋላ መግለጫ ያወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
የፀጥታ ኃይሎቹ የማቻርን ቤት የከበቡት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ይፋ ያደረጉትን የአገሪቱ ብሔራዊ ጦር የሚመሠረትበትን መመሪያን የሚቃወም መግለጫ ካወጡ በኋላ ነው።
ከአራት ዓመት በፊት ሁለቱ ተቀናቃኝ መሪዎች ከሰላም ስምምነት ላይ ሲደርሱ ከተስማሙባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ብሔራዊ ሠራዊት መመስረት አንዱ ነበር።
ነገር ግን ማቻር በሰላም ስምምነቱ ላይ እንደሰፈረው ፕሬዚዳንት ኪር በጦር ሠራዊቱ እና በፖሊስ ኃይሉ ውስጥ ያሉ ሥልጣኖችን በእኩል እያጋሩ አይደለም ሲሉ ከሰዋል።
ጨምረውም ፕሬዚዳንቱ እየወሰዱት ያለው የተናጠል እርምጃ ከሰላም ስምምነቱ ተቃራኒ እና እየተካሄደ ያለውን ድርድር በግልጽ የሚቃወም ነው ብለዋል።
የምክትል ፕሬዚዳንቱን ክስ በተመለከተ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጽህፈት ቤት ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።
የሪክ ማቻር መኖሪያ ቤት በአገሪቱ ጦር መከበብ በአገሪቱ የተደረሰውን የሠላም ስምምነት እንዳያደናቅፍ ስጋት አሳድሯል።
የደቡብ ሱዳን ልዩ ኃይሎች የምክትል ፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ቤት የከበቡት፤ ማቻር ከጥቂት ቀናት በፊት የመንግሥት ወታደሮች የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሰዋል ብለው ቅሬታ ካሰሙ በኋላ ነው።
ጦሩ የምክትል ፕሬዚዳንቱን መኖሪያ ቤት ለምን እንደከበበው ይፋ አላደረገም።
በአሁኑ ወቅት በማቻር እና በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ ቀጥሏል።
ማቻር ባለፈው ሳምንት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት በዩኒቲ እና በላይኛው ናይል ግዛቶች በመንግሥት ጥቃት እንደተፈጸመ አስታውቀው ነበር።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሁለቱ ወገኖች መካከል እስከ ጦር መማዘዝ የደረስ ግጭት ተከስቷል።
ተቃዋሚው የአገሪቱን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ ያገዘውን የ2018 የሰላም ስምምነት ለማክበር መንግሥት ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽ ከስምምነቱ መውጣቱን አስታውቋል።
የስምምነቱ ተፈጻሚነት ከታቀደለት ጊዜ ቢዘገይም አገሪቱን ወደ ሠላም ይመልሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ከሆነ ደቡብ ሱዳን በስድስት ዓመቱ ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ወደ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ ወደ ጎረቤት አገራት ተፈናቅለዋል።
ይህም በአፍሪካ ትልቁ የስደተኞች ቀውስ ነው ሲል ገልጾታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014