
ከቀናት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ላቀና ፖሊሶችን በየቦታው በተጠንቀቅ ሲንቀሳቀሱ ይመለከታል።
የአሌክሳንድራ ደግሞ የተለየ ነው። ምነው ካሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እና በንግድ በተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች መካከል ጠብ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የሚል ምላሽ ያገኛሉ።
ስጋቱ አሁንም እንዳለ ነው። ስጋት ከገባቸው መካከል ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል። ለዚህ ሁሉ ምክንያት ከሆነው ጉዳይ እንጀምር።እንደ አሌክሳንድራ አይሁን እንጂ በመላዋ ደቡብ አፍሪካ የኑሮ ልዩነት በስፋት ይታይባታል።
ለዚህ ሁሉም የራሱን ምክንያት ያስቀምጣል። አንዳንዱ ሥርዓቱ ነው ይላል። ሌሎች ደግሞ “መጤዎች ናቸው ለዚህ ያበቁን” ባይ ናቸው። ችጋር ተጫወተብን ብለው የሚያማምርሩ ደቡብ አፍሪካውያን ባሉባት አገር በሰማይ በምድር ብለው የገቡ ስደተኞች ደግሞ በኑሮ እየበለጸጉ ነው።
ይህን አወዛጋቢ ጉዳይ አንግበው ሁለት ቡድኖች ብቅ ብለዋል። ‘ዘ አሌክሳንድራ ዱዱላ ሙቭመንት’ እና ‘ኦፕሬሽን ዱዱላ’ የተባሉ።ሁለቱም ሰነድ አልባ የሆኑ መጤ አፍሪካውያን ከአገራቸው እንዲወጡ የሚቀሰቅሱ ናቸው።
ሆድ ለባሰው. . . እንደሚባለው ሆነና ተገፍተናል፣ የድርሻችንን አላገኘንም በሚለው ሕዝብ ዘንድ ሃሳባቸው ገዢ አግኝቶላቸዋል።
እነዚህ ቡድኖች የሚፈልጉት ምንድን ነው?
በአገሪቱ ዜጎች እና በሰነድ አልባ ስደተኞች መካከል ለሚፈጠረው ውጥረት ቀዳሚው ምክንያት ድህነት ነው። ትክክልም ይሁኑ አይሁኑ እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች ምክንያት የሚሉት እነዚህኑ ሰነድ አልባ ስደተኞች ነው።
ዱዱላ በዙሉ ቋንቋ “አስወጧቸው” ወይንም “ይሂዱልን” ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቡድኖቹ ምን እንደሚፈልጉ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ምንም እንኳ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የተለያዩ ቢሆኑም የመደራጀታቸው ምክንያት ግን ተመሳሳይ ነው፤ ሁለቱም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እየመነጠሩ ማስወጣት።
ይህንን በማድረጋቸውም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካ ውያን ሥራ እና የንግድ በሮችን እንደሚከፍቱ በብርቱ ያምናሉ። ይህ ነው ለኢትዮጵያውያኑም ስጋት ሆነው። ይህ ነው እንቅልፍም የነሳቸው።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም