ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬን ከማስገባትና የአገር ገጽታን ከመገንባት አንጻር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም ። ኢትዮጵያ ደግሞ 13 የሚደርሱ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶች ባለቤትና ሁሉም የቱሪስት መዳረሻዎቿ የጎብኚዎችን ቀልብ ስበው የራሳቸው ማድረግን የተካኑ በመሆናቸው ገቢን በማስገኘቱ በኩል ምንም የሚሳናቸው ነገር አይኖርም ። ነገር ግን ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማቱ ይህንን ማድረግ እንዳልተቻለ ይነገራል ።
የሚጠበቅባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስገኙ ነው ለማለትም እንደማያስደፍር ይገለጻል ። እናም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና ነባሮቹንም በማደስ ነገሮችን ለመፍታት እየሞከረ ይገኛል ። በአዲስ አበባ የተገነቡት የአንድነት፣ የእንጦጦና የወዳጅነት ፓርኮች እንዲሁም በገበታ ለአገር መርሀግብር የተጀመሩት ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ ለዚህ ምርጥ ማሳያዎችም ናቸው ።
እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ከሚያስገኙት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ። የቱሪስት መዳረሻዎች ሲስፋፉ በዚያው ልክ የምግብ፣ የመኝታ፣ የትራንስፖርት ወዘተ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ይበዛሉ ። ይህ ደግሞ ውድድርን ፈጥሮ ጥራት እንዲመጣና ደንበኞችን በአግባቡ እንዲስተናገዱ ያደርጋል ። በዚያው ልክ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች እንዲበራከቱ እድል ይሰጣል ። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ኢኒስቲቲዩት ላለፉት 53 ዓመታት በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ ሙያተኞችን እያሰለጠነ ለዘርፉ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ኖሯል ። በዚህ ዓመትም ያሰለጠናቸውን 125 ሙያተኞች አስመርቋል ።
መንግሥት ከያዘው የእድገት አቅጣጫ አንጻር ኢንስቲቲዩቱ የሚያሰለጥናቸው ሙያተኞች የሚያደርጉት እገዛ ምን ሊሆን ይችላል ? በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎች ምን ለመሥራት አስበዋል ? በሚሉትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ተመራቂዎችን እና በእለቱ መልእክት ያስተላለፉትን የመንግሥት ኃላፊዎችን አንኳር አንኳር ሀሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል ።
መጽናናት አባይነህ በ2014 ዓ.ም ኢንስቲቲዩቱ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ስትሆን በውጭ አገር ምግብ ዝግጅት ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ተምራ በሌቭል ሶስት የተመረቀች ነች ። በመጀመሪያ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትምህርት ስትጀምር ይህ ነው የሚባል እውቀት እንደሌላት ትናገራለች ። የትምህርት አሰጣጡ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ መሆኑ ሙያውን እንድትወደው ተጽእኖ እየፈጠረባት እንደመጣና ስለዘርፉ ያላት ግንዛቤም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር እንዳገዛት ታስረዳለች ።
ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ጸጋ እንዳላት የምትናገረው መጽናናት፤ ዘርፉ ትኩረት አግኝቶ ቢሠራበት የብዙዎችን ሕይወት የመቀየር አቅም እንዳለው ትጠቅሳለች ። ከዚህ በፊት የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት መስክ በተማሪዎችም ሆነ በወላጆች አምብዛም አይወደድም ። አሁን ያለው ምልከታ መሻሻሎች ታዩበትም ከቱሪዝም ገቢ አንጻር ግን ታይቶ ካልተሰራበት ብዙ ፈተናዎች እንደሚኖሩም ታነሳለች ። ስለሆነም በዘርፉ ኢኮኖሚያቸውን ካበለጸጉ ታላላቅ የዓለማችን አገራት ተሞክሮ እየወሰዱ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማስረዳትና ተገቢውን ዋጋ መስጠት ይገባል ትላለች ።
የቱሪዝም ዘርፍ በርካታ የሰው ኃይል በመሸከም እያደገ የመጣውን የሥራ አጥ ቁጥር እንደሚቀንስ የምታነሳው መጽናናት፤ ወጣቱ ወቅቱ ከሚፈልገው የሥራ መስክ ጋር አሠራሩን እያዛመደ የራሱንም የአገሩንም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ አለበት ትላለች ። አሁን መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ የያዘው አቅጣጫም ለወጣቱ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራልና እንዲጠቀምበት ትመክራለች ።
ሌላው በተመሳሳይ ሙያ የተመረቀው ብሩክ ጌታቸው ሲሆን፤ ሆቴልና ቱሪዝም ኢንስቲቲዩት ረዥም ልምድ ያለው እንደመሆኑ መጠን በርካታ እውቀትና ክህሎትን ያላብሳል ። የፈለኩትን አቅም ገንብቼበታለሁም ይላል ። ያልተገደበ የተግባር ልምምድ በማድረጉም ብዙ ነገሮችን እንዳወቀ ያነሳል ። በትልልቅ ሆቴል ውስጥ ምግብ ለማዘጋጀት የሚያገለግሉ ቁሳቁስን እየተጠቀመ መማሩ የወደፊት ህልሙን እውን ለማድረግ መደላድል እንደፈጠረለትም ይናገራል ።
ተማሪዎች በእውቀት በልፅገው እንዲወጡ የሚያደርጉ ዝግጅቶች መኖራቸውን የሚያነሳው ወጣቱ፤ ልምምዱና ስልጠናው ከሥራ ፈላጊነት የራስን ሥራ ከመፍጠር አኳያ የማይተካ ሚና አለው ። ሥራው በተፈጥሮው ሰውን ማገልገል፣ ሰውን ማስደሰት ነውና ይህንን እንድናደርግም የሚያስችለን ነው ። ስለዚህም ሰዎችን ማስደሰት ከተቻለ ሁልጊዜም አገልግሎቱን ፈልገው እንዲመጡ ያደርጋል ይላል ።
ብሩክ ትምህርቱን እየተማረም በትርፍ ጊዜው በሆቴሎች ውስጥ በሼፍነት ሲሠራ እንደነበር እና በወር ከአራት እስከ አምስት ሺህ ብር ሲከፈለው መቆየቱን ገልጾልናል ። ይህ ደግሞ ተምሮ ከመመረቁ በፊት ወላጆቹን ሳያስቸግር በሚያገኘው ገቢ የተለያዩ ወጪዎቹን እየሸፈነ እንዲማር ረድቶታል ። በመሆኑም በዘርፉ የተማረ ሰው ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ነገሮች ያመላክታሉም ባይ ነው ።
ከሆቴልና ቱሪዝም የተመረቀ ተማሪ ያለሥራ የሚቀመጥበት አጋጣሚ አይኖርም የሚለው ብሩክ፤ የቱሪዝም ዘርፉ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር በዘርፉ የተማረ ሰውም ተፈላጊነት ይጨምራል ። የራስን ሥራ ለመፍጠርም አመቺነት አለው ። ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎች ላይ የሚሰሩ ምግብ አብሳዮች/ ሼፎች/ እስከ መቶ ሺሕ ብር የወር ደመወዝ ያገኛሉ ። እናም የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት የራስንም የቤተሰብንም ሕይወት የመቀየር አቅም አለውና የተሰጠን እድል መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ያስረዳል ።
ብሩክ ገና ሳይመረቅ በሆቴል ውስጥ እየተከፈለው መሥራት ከቻለ የሥራ ልምዱ እየጨመረ ይሄዳል ። የክፍያው መጠንም እንዲሁ ። ስለዚህም ጅማሮው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይገልጻል ። ከተወሰነ ቆይታ በኋላ የራሱን ምግብ ቤት በመክፈት ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት አቅዷልም ። የውጭ አገር ዜጎች የሚፈልጉትን የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ኢትዮጵያን እንዲወዱና ተመልሰው እንዲመጡ ፍላጎት የማሳደር ሥራንም እንደሚያከናውን ነግሮናል ።
ሌላዋ የኢንስቲቲዩቱ ተመራቂ ርስቴ ደስታው ነች ። የኢትዮጵያን ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳዳግ የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና ማድረግ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች ። ይሁን እንጂ ኢንስቲትውቱ እንደ አንጋፋነቱ የምግብና የመኝታ አገልግሎት ስለማይሰጥ አብዛኛው ተማሪ ከከፍለ አገር ስለሚመጣ ማደሪያ ሳያገኝ ጭምር ይማራል ። ይህ ደግሞ በመማር ማስተማሩ ላይ ጫናን ይፈጥራል ። ይህንን ደግሞ መፍታት ያለበት መንግሥት ነውና እንደሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሁሉንም ነገር ሊሟላለቸው ይገባል ትላለች ።
መንግስት በቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት እንዲፈጠር እየተሰራ ያለው ነገር የሚያስመሰግነው እንደሆነ የጠቆመቺው ርስቴ፤ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በተማሪዎች ላይ ተስፋ ጥሏል ። በዘርፉ የሚመረቁ ተማሪዎች ተቀጥሮ ከመሥራት ባለፈ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩም እያደረገ ነው። አገራቸውን በማስተዋወቅ በኩልም ትልቅ አስተዋዕጾ እያደረገ ይገኛል ። ከዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ተመርቀው ሥራ አጣን በሚል ቁጭ ያሉ ወጣቶችም ሙያዊ ስልጠና እየወሰዱ ዘርፉን ቢቀላቀሉ የራሳቸውን ሥራ መፍጠር ይችላሉና ይጠቀሙበት መልዕክቷ ነው ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በምረቃ መርሀግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ የተመረቃችሁት እውቀትንና ክህሎትን ተላብሳችሁ በአገራችን ትልቅ ክፍተት ባለበት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት በመስጠት የዘርፉን ችግር እንድትፈቱ ነው ። በሂደትም ራሳችሁ ሥራ ፈጥራችሁ ለሌሎች ሥራ ለመፍጠር ነው ። ከምርቃታችሁ በኋላ የምታቀርቡት የግብርና ውጤት ወይም የፋብሪካ ውጤት ሳይሆን አግልግሎት ነው ። ማገልገልና በተገልጋይ ዘንድ እርካታ መፍጠር ጥበብን፣ ብቃትን ፣ ትዕግስትን፣ የሰው ባህሪን ተረድቶ ሰው መሆንን ይጠይቃል ። ስለሆነም ስልጠናችሁን በተግባር አሳዩ ።
ስልጠናው ትልቅ ውጤት /ትልቅ ፍሬ/ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ንድፈ ሀሳብን ከተግባር ጋር እና ከእለት ተእለት ሕይወት ጋር አቆራኝተው የሚሰጡ በመሆናቸው በአጭሩ የሚረሱና የሚያረጁ ሳይሆን አገልግሎት መስጠት በተጀመረ ወቅት የበለጠ እየፈኩ የሚሄዱ ናቸው ። እናም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያልተነካ ሀብት አላትና እንድትጠቀምበት አድርጓት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በዓለም አደባባይ የምንታወቅባቸው፤ ሰዎች ሊጎበኟቸውና ሊያይዋቸው የሚጓጉላቸው እጹብ ድንቅ የሆኑ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ መስእቦች ቢኖሩንም በእውቀት አልመራናቸውም፤ በዚህም የተነሳ አልተጠቀምንባቸውም ። በዚህም ይህንን ድክመት ለማስወገድ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል ። ይህ ዘርፍ በአገር በቀል ኢኮኖሚው፤ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ እንዲሁም በአስር ዓመቱ የሥራ እድል ፈጠራ ፍኖተ ካርታም ልዩ ትኩረት የተሰጠውና ልዩ ድጋፍ የሚደረግለት ይሆናልም።
በአገራችን ከፍተኛ የሥራ እድል የመፍጠር ተስፋ ከተጣለባቸው 11 ዘርፎች ውስጥ የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ እንደሆነ ያነሱት አቶ ንጉሱ፤ ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል ። ስለሆነም ተመራቂዎች ይህንን ዘርፍ በማልማትና በማስፋት አገሪቱ ከዘርፉ እንደትጠቀም የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ ብለዋል። ተማሪዎች በስልጠና ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ዝቅ ብሎ ደንበኞችን በማገልገል የኢትዮጵያን ግጽታ የሚቀይር ተግባር ማከናወን እንደሚችሉበትም ተናግረዋል ።
መንግሥት ዘርፉ በሥራና ክህሎት ሥር እንዲመራ ሲያደርግ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ይዞ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ የመጀመሪያው ዜጎች ክህሎት የሚላበሱበት፣ ችግር ፈቺ እውቀት የሚገበዩበት፣ የተቀናጀና የተሰናሰለ አገልግሎት ለመስጠት ቀና አመለካከት የሚላበሱበት ነው ። ሁለተኛው ምክንያት ይህ ዘርፍ ያልተነካ በመሆኑ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ስለታመነበት መሆኑን አንስተዋል ።
ክህሎት ማሰልጠኛ ተቋማት ሁሉ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ንጉሱ፤ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት፤ ከግብርና ኮሌጆች እና ከሌሎችም የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት የተቀረጸ ዜጋ የማፍራት ኃላፊነት አለበት። ስለሆነም የእለቱ ተመራቂዎች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የኢንስቲቲዩቱ አምባሳደር በመሆን የተላበሱትን እውቀትና ክህሎት በተገቢው መንገድ እንዲተረጉሙ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢንስቲትውቱ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በበኩላቸው እንተናገሩት፤ አንጋፋው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም በዘርፉ እስከ አሁን ከ2መቶ ሺሕ በላይ ሙያተኞችን አስመርቋል ። በዚህም ለሆቴልና ኢንደስትሪው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል ። ዛሬ በሌቭል ደረጃ 124 ተማሪዎች መመረቃቸውም የዚሁ አካል ነውና ትልቅ ሥራ እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ማሰዳግ እንደሆነ የጠቆሙት ወይዘሮ አስቴር፤ በቱሪዝም ዘርፍ እሰከ አሁን ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል 33 በመቶ ብቻ ነው ። ይህ ደግሞ አገልግሎቱን ለማዘመን ሲታሰብ ዘርፉን ኢኮኖሚ አመንጪ ለማድረግ በርካታ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍረት ያስፈልጋል ። ስለሆነም እንደአገር በዘርፉ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማት እያደጉ መምጣታቸው ትልቅ እምርታ እንደሆነ አስረድተዋል ።
ዘርፉ ለተግባር ልምምድ ትልቅ ካፒታል ተመድቦለት ሲሠራ እንደነበርና በ24 ቤተ ሙከራዎች የተግባር ስልጠናዎችን ሲያደርግ እንደቆየ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ዘርፉ ከፍትኛ የሰው ኃይል የሚፈልግና የሚፈጥር ነውና ተማሪዎች ከስልጠናው ጎን ለጎን የኢንተርፕሬነር ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ተናግረዋል ። ኢንስቲትውቱ ሥራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ ተማሪዎችን የሚያሰለጥን በመሆኑ ተመራቂዎች በቱሪዝም ዘርፍ ሥራ በመፍጠር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አድርገዋል ።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም