
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በዩክሬን ቀውስ ዙሪያ ምክክር ለማድረግ በመርህ ደረጃ መስማማታቸውን አስታወቁ።
ዋይት ሀውስ እንዳለው በፈረንሳይ ሀሳብ አመንጪነት የሚካሄደው ውይይት የሚሳካው ሩሲያ ጎረቤቷን ዩክሬንን የማትወር ከሆነ ብቻ ነው።
ይህ ውይይት የሚሳካ ከሆነ ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ በአውሮፓ ያጋጠመውን ትልቅ የደህንነት ቀውስ ለማርገብ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይገመታል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት የሩሲያ ወታደሮች ሙሉ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ለማካሄድ ዝግጁ ስለመሆናቸው በሳተላይት ምሥሎች ጭምር መረጃ አለን ቢሉም ሞስኮ ግን ጉዳዩን ሀሰት ነው ብሏል።
የንግግሩን ሀሳብ ያቀረቡት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሁለቱም አገራት መሪዎች ጋር ለሶስት ሰአታት የፈጀ የስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ መሰረት ይህ ውይይት ምናልባትም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እና የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሐሙስ ዕለት በሚያደርጉት ውይይት ወቅት ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።
ዋይት ሀውስ በበኩሉ የቀረበ ሀሳብ ስለመኖሩ ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን ሩሲያ አሁንም ቢሆን ዩክሬን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ወረራ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቁሟል። ይህ ከሆነም አሜሪካ ፈጣንና ከፍተኛ የሆኑ እርምጃዎችን እንደምትወስድ አሳስቧል።
የባይደን አስተዳደር እንደሚለው ሩሲያ በዩክሬን ድንበር በምትጋራባቸው አካባቢዎች ብቻ 190 ሺህ በሚገባ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮችን ያሰፈረች ሲሆን ይህ ደግሞ ሩሲያ ከምትደግፋቸውና በምስራቃዊ ዩክሬን ከመንግስት ጋር ውጊያ ከገጠሙት አማጺያን ጋር ጭምር ነው።
ሩሲያ ዩክሬንን የመውረር እቅድ እንደሌላት በተደጋጋሚ ብትገልጽም ከ100 ሺህ የሚበልጡ ወታደሮቿን በድንበር አካባቢ ማስፈሯ ድንገት ወረራ ልትፈፅም ትችላለች በሚል ምዕራባውያንን አስግቷል። ረቡዕ ዕለት የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ታንኮች ክሬሚያን ለቀው ሲወጡ ለማሳየት ተንቀሳቃሽ ምሥል አውጥቷል።
ይሁን እንጂ እንደ ዋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆነ ረቡዕ ዕለት የደረሱትን ጨምሮ በቅርብ ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የሩሲያ ወታደሮች ድንበር ላይ ደርሰዋል። ረቡዕ ዕለት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ጄንስ ስቶልተንበርግ የሩሲያ ጦር ውጥረቱን ማርገቡን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደሌሉ ገልጸው፤ ከሩሲያ የሚሰነዘረው ማስፈራሪያ “እየተለመደ መጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው የኔቶ መከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ስቶልተንበርግ፣ ድርጅቱ አዳዲስ የውጊያ ቡድኖችን ማለትም ብቃት ያላቸውና ራሳቸውን የሚችሉ ትናንሽ ወታደራዊ ቡድኖች በመካከለኛው እና በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ለማቋቋም እያሰበ ነው ብለዋል።
ኔቶ ለሩሲያ ስጋት አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሞከሩት ሚኒስትሩ፤ ይህ ሃሳብ እአአ ከ2014 ጀምሮ 270 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት የአውሮፓ መከላከያን ለማጠናከር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አካል መሆኑን አስረድተዋል።
በርካታ ምዕራባዊያን አገራት ሩሲያ ጥቃት ልትሰነዝር ነው ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ አገራት ዜጎቻቸው ዩክሬንን ጥለው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ የሰጡ ሲሆን አሜሪካ፣ ዩኬ እና ጀርመን ዜጎቻቸው ኪዬቭን ለቀው እንዲወጡ ካሳሰቡ አገራት መካከል ናቸው።
ካናዳም እንዲሁም የኤምባሲ ሠራተኞቿን ልቪቭ ወደተሰኘው ከፖላንድ ጋር ወደምትዋሰነው የድንበር ከተማ ያሸሸች ሲሆን በዩክሬን የዩኬ አምባሳደር ሜሊንዳ ሲመንስ ደግሞ ወሳኝ ቡድኑ ኪዬቭ እንደሚቆይ ገልጸዋል። ሩሲያ በበኩሏ ከኪዬቭ አሊያም ከሶስተኛ አገር ትንኮሳ ሊኖር ስለሚችል ዩክሬን ያሉ ዲፕሎማቶቿን ልትቀንስ እንደምትችል ጠቁማለች።
የአሜሪካው ሲቢኤስ ኒውስ የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊዎች የሩሲያ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች በወረራው ሀሳብ እንዲቀጥሉና ልዩ የሆኑ ወታደራዊ እቅዶች እያዘጋጁ ስለመሆናቸው መረጃው እንደደረሳቸው ዘግቧል። ሪፖርቱ እንደሚለው ሩሲያ በመጀመሪያ ዩክሬን ላይ የሳይበር ጥቃት የምትፈጽም ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የሚሳኤል ጥቃቶችን ታካሂዳለች።
የአየር ጥቃትም የሚኖር ሲሆን በመጨረሻ ደግሞ እግረኛ ወታደሮች ዩክሬንን እንደሚወሩ ጠቁሟል። አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ሩሲያ በአሁኑ ወቅት 70 በመቶ የሚሆነውን ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ማዘዟን ጠቁመዋል።
ነገር ግን የዩክሬኑ የመከላከያ ሚኒስትር አሌክሲ ሬዝኒኮቭ በበኩላቸው ‘’ነገ አሊያም ከነገ ወዲያ ጥቃት ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው’’ ብለዋል።
ምክንያታቸውን ሲያስረዱም አንድም የሩሲያ ጥቃት አድራሽ ቡድን በድንበር አካባቢ አለመመስረቱን መጥቀሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014