ኢትዮጵያውያን የተጋመደና የማይበጠስ አብሮነት ያለን ሕዝቦች ነን። ማህበራዊ መስተጋብራችን እንዲጠናከር ከረዱን እሴቶቻችን መካከል መደጋገፋችን፣ መተዛዘናችንና መከባበራችን ተጠቃሽ ናቸው።
ያዘነን ማጽናናት፣ የተቸገረን መርዳት፣ መዋደድና መከባበር ከአባቶቻችን የወረስናቸው መገለጫዎቻችን ናቸው። ኢትዮጵያ የተሠራችው በእነዚህ እሴቶች በተገነቡ ሕዝቦች ነው። በዛሬው የሀገርኛ አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው ሰው አብሮ አደጎቻቸውን በማስተባበር ባደጉበት መንደር የሚኖሩ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት የሚታትሩ ናቸው።
ርቀት አልገደባቸውም፤ ነዋይ አላማለላቸውም፤ በሚኖሩበት አሜሪካ አገር ሆነው ሌሎችንም በማስተባበር በልጅነታቸው እየገሰጹ ሰው ያደረጓቸውንና ዛሬ በጉስቁልና ሕይወት የሚኖሩ የሰፈር ሰዎችን ሲደግፉ በማየታችን አርአያነታቸው ወደ ሌሎች እንዲጋባ በማሰብ የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋቸው ወደደን። ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ቀበና አካባቢ ነው።
በኢትዮጵያውያን ወግና ሥርዓት ተኮትኩተዋል፤ በወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆን በሰፈር ሰው ተገስጸውና ተቆንጥጠው ማደጋቸውን ይናገራሉ። እነዚያ የመንደሩን ልጆች እየመከሩ፣ እየገሰጹና እየቀጡ ለቁም ነገር ያበቁ የአካባቢው ሰዎች በዛሬው ማንነታቸው ላይ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ባለታሪኩ ይናገራሉ። የትም ይኑሩ የት በልጅነት ዕድሜያቸው ቀናውን መንገድ እንዲከተሉ እየመከሩ ያሳደጓቸውን የመንደራቸውን ሰዎች አይረሷቸውም።
ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር የነበራቸው መፈቃቀር፣ መከባበርና መረዳዳትም ያኔ የተገነባ ነው። ዛሬ እርሳቸውም ሆኑ የተቀሩት አብሮ አደጎቻቸው ካደጉበት መንደር ርቀው አስተዳደጋቸውን፣ አካባቢያቸውንና የአካባቢያቸውን ሰዎች እየናፈቁ በሰው አገር ይኖራሉ።
ገርፈውና ገስጸው የሕይወትን መስመር ያስያዟቸው የዚያች መንደር አንጋፋዎች አንዳንዶቹ አርጅተው፣ አንዳንዶቹም ደህይተው፣ አንዳንዶቹም ጤና አጥተው አስቸጋሪ ሕይወትን ሲገፉ ማየታቸው ውስጣቸውን ይረብሸው እንደነበር ገልጸውልናል። እንግዳችን አቶ ሙላት ዘለቀ ይባላሉ። አቶ ሙላት እዚሁ አዲስ አበባ በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ከአምስት አመት በፊት አሜሪካ ሲያትል ከተማ ሄደው እየሠሩ መኖር ጀምረዋል።
አዲስ አበባ በነበሩ ጊዜ ትምህርታቸውን በኮከበ ጽብሃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀው የሆቴልና ቱሪዝም ስልጠና በመውሰድ ከ20 ዓመት በላይ በሆቴል ማናጀርነት እና ሆቴሎች ውስጥ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ሙዚቀኞችን በማደራጀትና በማስተባበር ሠርተዋል።
ያን ጊዜ ታዲያ ያሳደጓቸውን የመንደራቸውን ሰዎች አኗኗር እያዩ ያዝኑ ነበር። ሁል ጊዜም እንዴት ሊረዷቸው እንደሚችሉ ያስቡ ነበር። በ2009 ዓ.ም ወደ አሜሪካ እንደወጡ በውጭ የሚኖሩ አብሮ አደጎቻቸውን በማስተባበር ያሳደጓቸውን የመንደራቸውን ሰዎች ለመርዳት ይነሳሳሉ።
በተለያዩ የዓለም አገራት ከሚኖሩ አብሮ አደጎቻቸው ጋር በማህበራዊ ሚዲያ መገናኘት ይጀምራሉ። በአቅም መድከም፣ በጠዋሪ ማጣት፣ በኑሮ ውድነትና በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ውስጥ የሚማስኑ የመንደራቸው ሰዎች መኖራቸውን ይገልጹላቸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን የጉስቁልና ሕይወትን የሚመሩ የአካባቢያቸውን ሰዎች ፎቶግራፍ ሳይቀር እየላኩላቸው የችግራቸውን ደረጃ እንዲረዱ ያደርጓቸው ነበር።
እነዚህን የዚያን ዘመን ትውልድ ባለውለታዎች መርዳት የሞራል ግዴታ እንደሆነ አምነው ከአብሮ አደጎቻቸው ጋር ገንዘብ ለማሰባሰብ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በዚሁ መሠረት አርባ አምስት የሚደርሱ አባላትን ያሰባስባሉ። ከዚያም የቀበና ቀበሌ አስራ ስድስት አብሮ አደጎች መረዳጃ ማህበርን ይመሰርታሉ። አቶ ሙላት የማህበሩ መስራችና ሰብሳቢ ይሆናሉ። በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአረብ አገራትና በሌሎችም የዓለም አገራት ከሚኖሩ አብሮአደግ ጓደኞቻቸው ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በጥልቀት መነጋገር ይጀምራሉ።
ወቅቱ ኮቪድ-19 የተከሰተበት ወቅት ስለነበር አብዛኛው ሰው ሥራውን አቋርጦ እቤቱ የሚያሳልፍ በመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ እየተገናኙ ለማውራት ምቹ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል። የቀበና አካባቢ ቀበሌ አስራ ስድስት ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንዶችም በዚህ የተቀደሰ ዓላማ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ይሆናሉ።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ ይጀመራል። እያንዳንዱ አባል ቢያንስ በወር አምስት መቶ የኢትዮጵያ ብር ከፈለገም ከዚያ በላይ እንዲሰጥ ይወሰናል። የሚሰበሰበውን ብር ለተቸገሩ ሰዎች በፍትሃዊነት የሚያሰራጭ አንድ ኮሚቴ በትውልድ አገራቸው እንዲቋቋም ያደርጋሉ።
ውጭ ያለው ማህበርና አገር ውስጥ ያለው ኮሚቴ እየተነጋገሩ መሥራት ይጀምራሉ። በተከፈተው አካውንት ብር ከውጭ እየተላከ ኮሚቴው ማን ከማን ይሻላል የሚለውን እየለየ ድጋፍ ማድረጉን ይጀምራል። በዚሁ መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ተሰባስቦ ለተረጂዎች እንዲሰጥ ተደርጓል። እንደ አቶ ሙላት ገለጻ ከኑሮ ውድነቱ አንጻር እያደረጉ ያለው ድጋፍ በቂ ባይሆንም የመንደሩን ልጆች በሥነ ሥርዓት አንጾ በማሳደጉ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ አዛውንቶችን ለመርዳት እያደረጉ ያለው ድጋፍ ለእርሳቸውና ለአጋሮቻቸው የህሊና ርካታ ሰጥቷቸዋል። ወደፊትም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ህልም አላቸው።
ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደ ጤና ጣቢያና ሌላ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋም በመክፈት አቅመ ደካሞች በነፃ፤ ሌሎችም በቅናሽ ዋጋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ተቋም መመስረት የረዥም ጊዜ እቅዳቸው መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ገብረጻዲቅ ሳህሌ የአገር ውስጥ ኮሚቴው ሰብሳቢ ናቸው።
እርሳቸው እንደተናገሩት ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በኮሚቴው አካውንት እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ማን መታገዝ እንዳለበት ከኮሚቴው አባላት ጋር በመሆን አስቀድሞ ሰዎችን የመለየት ሥራ ይሠራል። እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩ ሰዎች በኮሚቴው አባላት ችግረኛ መሆናቸው የታመነባቸውና እና ይሁንታ ያገኙ መሆን አለባቸው።
ችግረኞችን ለመለየት እንደመስፈርት ከሚያገለግሉት ነገሮች ጥቂቶቹ አቅመ ደካማ መሆን፣ ጠዋሪ ማጣት፣ አካል ጉዳተኝነት፣ የገቢ መጠን ማነስ ወይም አለመኖር፣ የመጠለያ ችግር ወዘተ ናቸው። በዚህም ላይ የኮሚቴው አባላት ለረዥም ዘመን በአካባቢው የኖሩ በመሆናቸው የሰዎችን የአኗኗር ደረጃ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ተጨምቀው ከታዩ በኋላ እንደችግሩ ደረጃ እየታየ ድጋፍ ይደረጋል። በዚህ አሠራር መሠረት መጀመሪያ 104 ተረጂዎች ተለይተው ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።
አንዳንዶቹ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው፤ ሌሎቹም በተደረገ የማጣራት ሥራ መስፈርቱን የማያሟሉ ሆነው በመቀነሳቸው አሁን የተረጂዎቹ ቁጥር ወደ 77 ቀንሷል። ኮሚቴው በዓመት ሦስት ጊዜ ያህል በተለይም ታላላቅ አመት በዓሎች ሲደርሱ ለሚፈልጉት ዓላማ እንዲያውሉት ለተረጂዎች ጥሬ ብር ይሰጣቸዋል።
በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ለእያንዳንዱ ሰው አንድ ሺ ሦስት መቶ ብር ይሰጥ እንደነበርና አሁን ለተከታታይ ጊዜ ለእያንዳንዱ አባል አንድ ሺ አምስት መቶ ብር እንደተከፈለ የማኅበሩ ሰብሳቢ አቶ ገብረጻዲቅ ገልጸውልናል።
ኮሚቴው ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ የሚገልጽ የባንክ ስቴትመንት በመያዝ የሚከፍለውንም ገንዘብ እያስፈረመ ለተረጂዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሚያሰራጭ
መሆኑን የሚያስረዳ የተሟላ ሰነድ እንዳለው ሰብሳቢው ገልጸዋል። በውጭ አገር ለሚገኘውና ርዳታ ለሚያደርገው የቀበና ቀበሌ አስራ ስድስት ተወላጆች መረዳጃ ማህበር በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ስለክፍያው አፈጻጸም በየጊዜው ሪፖርት ይደረግለታል።
ኮሚቴው ግልጽ አሠራርን በመከተል የተሰጠውን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ ገብረጻዲቅ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በራሳቸው ተነሳሽነት ያሳደጓቸውን ሰዎች በዚህ መልክ መርዳታቸው እጅግ የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል።
የኮሚቴው አባላት ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለተረጂዎች በማድረሳቸውና በእንዲህ ዓይነቱ የበጎ አድራጎት ሥራ በመሳተፋቸው ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቀበና ቀበሌ አስራ ስድስት አብሮ አደጎች ማህበር የሚልከውን ገንዘብ ኮሚቴው ከባንክ አውጥቶ በታማኝነት ለተረጂዎች ማከፋፈል መቻሉ የተጣለበትን አመኔታና ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ቢሆንም ከዚህም በላይ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በተረፈ እንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ዓላማ አንግበው በሰው አገር እየኖሩ ወገኖቻቸውን የሚረዱ ኢትዮጵያውያንን በኮሚቴውና በተረጂዎች ስም ማመስገን እንደሚገባ ሰብሳቢው ተናግረዋል። ሌሎችም የእነርሱን ተሞክሮ አይተው በየአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ጥላሁን ሀብቴ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ ናቸው። ከልጅነታቸው ጀምሮ አንድ እግራቸውን በአደጋ ምክንያት ያጡ አካል ጉዳተኛ ናቸው። እንደዚያም ሆኖ ቀደም ሲል የውሃ ቦኖ እየቆረጡ በሚያገኗት አነስተኛ ገቢ ይተዳደሩ ነበር። አሁን ግን ጡረታ ወጥተዋል። የሚከፈላቸውን የጡረታ ገንዘብ እንዲህ ነው ብሎ መናገር ስላሳፈራቸው ዝም ማለትን መርጠዋል።
ከሃምሳ አምስት ዓመት በላይ በአካባቢው እንደኖሩ የተናገሩት አቶ ጥላሁን እርጅና ቤት ካስቀሯቸው በኋላ የጉስቁልና ሕይወትን እየገፉ እንዳሉና በየጊዜው እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት መቋቋም እንዳቃታቸው ይናገራሉ።
የቀበና ቀበሌ አስራ ስድስት አብሮ አደጎች መረዳጃ ማኅበር የገንዘብ እርዳታ የሚያደርግላቸው ማህበር ብቻ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ የሚጠይቃቸውና የሚንከባከቧቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ለአካባቢው አቅመ ደካሞች ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በተወካዮቹ አማካኝነት የታመሙ ሰዎችን ቤት ለቤት እየሄደ ይጠይቃል።
ስለማህበሩ ድጋፍ አውርቼ አልጨርስም ያሉት አቶ ጥላሁን ፈጣሪ እድሜ፣ ጤናና ጸጋ እንዲሰጣቸውና በያሉበት እንዲጠብቃቸው እመኛለሁ ብለዋል። አቶ መንገሻ ሲሳይ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሰባት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው።
እንደእርሳቸው አባባል በርካታ ድርጅቶች በበጎ ፈቃድ ማህበር ተደራጅተው አቅመ ደካሞችንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ ይተባበራሉ።
የቀበና ቀበሌ አስራ ስድስት አብሮ አደጎች መረዳጃ ማህበርም ከእነዚህ አንዱ ነው። የተለየ የሚያደርገው ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ አገር ውስጥ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት የከፋ ችግር ያለባቸውን ሰዎች እየለየ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑ ነው።
ቀበሌው በልማታዊ ሴፍቲኔት መረዳት አለባቸው ብሎ የለያቸውን ሰዎች ኮሚቴውም በተመሳሳይ የለያቸው መሆኑ የአሠራሩን ፍትሃዊነት የሚያሳይ አንድ ማረጋገጫ ነው። አስተዳደሩ የቀበሌ አስራ ስድስት ተወላጆች መረዳጃ ማህበር የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያውቅና፤ ኮሚቴው ለሚያቀርበው የትብብር ጥያቄ አስተዳደሩ መልስ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ማህበሩ ለአቅመ ደካሞች የሚያደርገው ድጋፍ ቀበሌው በሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚሠራውን ሥራ የሚያግዝ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት ባህል ከማሳደግ አንጻር ማህበሩ ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህ አርአያነቱ አስተዳደሩ ትልቅ ምስጋና ያቀርባል ሲሉ አቶ መንገሻ ተናግረዋል።
የዚህ ማህበር አባላት በውጭ የሚኖሩ ቢሆኑም ርቀት ሳይገድባቸው ያሳደጓቸውንና ያስተማሯቸውን ወገኖቻቸውን ችግራቸው ምንድነው ብለው ማየት መቻላቸው ያስመሰግናቸዋል ብለዋል።
ይህን ማህበር አርአያ አድርገው ወደ ሰባት የሚደርሱ የወጣት ማህበር አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል ያሉት አቶ መንገሻ ደም በመለገስ፣ ችግኝ በመትከል፣ አካባቢን በማስዋብና ለአቅመ ደካሞች የበዓል ስጦታ በማቅረብ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሌሎችም በዚህ ዓይነት ሥራ እንዲሰማሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
‹‹ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ›› እንዲሉ ኢትዮጵያውያን የተሰጡንን መክሊቶች ጥቅም ላይ በማዋል በመተዛዘን፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ አንድነታችንንና ፍቅራችንን ማጎልበት በሚያስችሉ ነገሮች ላይ እናተኩር እንላለን። ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014