
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የበርካታ ማዕድናት ሃብት ባለቤት ብትሆንም ይህንን ሃብቷን ጥቅም ላይ በማዋል የዜጎቿን ኑሮም ሆነ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በተለይም ማዕድንን በዘመናዊ መንገድ በማምረት ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት ያለመቻሉ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ከውጭ እንድስታስገባ አስገድዷታል። በዘርፉ ለዘመናት በዘለቀው ብልሹ አሰራር ምክንያትም ሃብቱ ለብዝበዛ ተዳርጎ እንደነበርም ይታወቃል።
ይሁንና በቅርቡ በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፍ ስርነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣትና ለሌሎች የልማት መስኮች ዋነኛ አውታር ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ ስራ ተሰርቷል። በአጠቃላይ በዘርፉ እየተሰራ ያለውን የሪፎርም ስራ በሚመለከት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድንና ነዳጅ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን አነጋግሮ እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ሚኒስቴር ራሱን ሪፎርም ካደረገ በኋላ የተገኙ ውጤቶችን ያብራሩልን እና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሚሊዮን፡- ባለፉት አራት ዓመታት እንደሚታወቀው ሀገር አቀፍ የሪፎርም ስራዎች ናቸው እየተካሄዱ የቆዩት። ከእነዚህ የሪፎርም ስራዎች መካከል ከኢኮኖሚ አንፃር የሚደረገው የሪፎርም ስራ ነው። ሀገር በቀል የሪፎርም አጀንዳ በመቅረፅ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንፃር ሰፊ ሥራ ሲሰራ ነበር የቆየው።
በተለይም የመንግስት፣ የግሉ ባለሃብትና ሌሎች የልማት አጋሮችን ሚናን በአግባቡ በለየ መልኩ ነው ስራዎቹ እንዲከናወኑ እየተደረጉ ያሉት። ከዚህ አንፃር ወደ ማዕድን ሚኒስቴር ስንመጣም ከትልቁ ሀገራዊ ምስል ላይ በመነሳት ነው ሥራችንን ለማከናወን የተነሳነው።
ወሳኝ ከሚባሉ የልማት አጀንዳዎች ውስጥ ማዕድንን በተመለከተ ከእይታ ጀምሮ ያለውን ዝንፈት ከማስተካከል ነው የጀመርነው። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው አፍሪካ ውስጥ ማዕድን የትርምስና የግጭት ምንጭ ነው።
ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ማዕድንን ለዘላቂ ልማት በሚሆን መልኩ እንዴት ነው መጠቀም የሚቻለው? የሚለውን ነገር ከተቃዋሚ የሪፎርም ስራውን ከሃገራዊ የልማት አጀንዳዎችም ጋር አያይዞ ማየት ነው የተሞከረው። በዚያ ደረጃ ተቋምን ማብቃት፤ የተቋሙን ፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን የውስጣዊ አደረጃጀቶችን ጭምር ማስተካከል ትኩረት ተሰጥቶታል።
መንግስት እየሰራ ካላቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚ ሪፎርም ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በተለይም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለብልፅግና ጥሩ መደላደል ይፈጥራል ተብሎ የሚገመተው የማዕድን ልማት ነው። የማዕድን ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው። ማዕድን ተገኘ ሲባል ይዞት የሚመጣው ችግር በመኖሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው።
ከዚያ ይልቅም ፋይዳውን አግዝፎ መመልከት ጠቃሚ ተብሎ ነው የተወሰደው። ማዕድንን ከግብርና ልማት፤ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት፤ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት በእጅጉ የተቆራኘ ስለመሆኑ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል። ለምሳሌ ግብርናን ከማልማት አንፃር ለረጅም ጊዜ ብዙ ነገር ተብሏል።
ግን ደግሞ ግብርናን ለማዘመን ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ውስጥ አንዱ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የማዳበሪያ ምርት ነው። ለማዳበሪያ ደግሞ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እያወጣን ነው ያለነው።
ግን ደግሞ ለማዳበሪያ ምርት የሚሆን ግብዓት ማለትም በወሳኝ መልኩ የተፈጥሮ ጋዝ እና ፖታሽ ማዕድናት በሃገራችን አለ።
መንግስት እነዚህን ስትራቴጂክ የሆኑ ሃብቶችን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ ልማት በማስገባት ግብርና የሚፈልገውን የማዳበሪያ ግብዓት በሃገር ውስጥ ለማምረት ሰፊ እንቅስቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው። ማዳበሪያ ማምረት መቻላችን በራሱ በምግብ እህል ራስችንን እንድንችል ከፍተኛ ሚና አለው። በመሆኑም ማዕድንን በምናነሳበት ጊዜ አብሮ የሚተሳሰረው ከግብርና ልማታችን ቀጥታ የተገናኘ ጉዳይ እንደሆነ ማሰብ አለብን።
አጠቃላይ የልማት ግባችንን ሊያሳካ በሚችል መልኩ የማዕድን ልማታችንን ልናከናውን ይገባል ብለን ነው እየሰራን ያለነው። በተመሳሳይ ኢንዱስትሪን ማልማት ከተፈለገ ብረትን ማልማት ወሳኝ ሚና አለው። የብረት ማዕድንን የማልማት አቅምን መገንባት ማለት ለቀጣይ ኢንዱስትሪ ልማት ጥሩ መደላደል መፍጠር ነው።
በተጨማሪም አጠቃላይ ኢኮኖሚያችን የወጭ ንግዱን የሚያበረታታ እንዲሆን ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚቻለው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን ሲቻል ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ባሉን ፀጋዎች መተካት ትልቅ ፋይዳ አለው። ስለዚህ ስለማዕድን ልማት ስናነሳ አንድ የሆነ የተፈጥሮ ሃብትን ስለማውጣት ብቻ ሳይሆን ግብርናን፤ ኢንዱስትሪውን ስለማልማት እያወራን መሆኑን መገንዘብ ግድ ይለናል።
በሌላ በኩልም ከኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ልማት አንፃር ማዕድን ልማት ወሳኝ ሚና አለው። እንደሚታወቀው ኮንስትራክሽንም ለሀገር ልማት በጣም ትልቅ የኢኮኖሚ ድርሻ ካላቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። ለዚህ ዘርፍ የሚያገለግሉ የሲሚኒቶ፤ የሴራሚክና የብርጭቆ ምርቶችን በሃገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ የተፈጥሮ ሃብት አለን። ይሁንና አሁንም ከፍተኛ ወጪ እያወጣን ነው እያስመጣን ያለነው። ስለዚህ የማዕድን ዘርፉን በወሳኝ መልኩ የማሳደጉ ስራ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት ቁልፍ ድርሻ አለው። ከውጭ የምናስመጣቸውን ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ግብዓቶችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬያችንን እንታደጋለን። አዲስ ዘመን፡- በዚህ ረገድ ታዲያ ሚኒስቴሩ አሁን ያለበት ቁመና እነዚህን ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ለለመለስ የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል? አቶ ሚሊዮን፡- በውይይታችን መግቢያ ላይ እንዳነሳሁልሽ በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በቅድሚያ የተከናወነው ስራ ከሁሉ በፊት ተቋሙ ውስጥ ሰፊ የሪፎርም ስራ ነው። ሚኒስቴሩ ከላይ የዘረዘርኩልሽን ሃላፊነቶች መወጣት ያስችለው ዘንድ መዋቅራዊ አደረጃጀቱንም ጭምር በአዲስ መልክ የማዋቀር ስራ ተሰርቷል።
በተመሳሳይ ሁለት ትልልቅ ኢንስቲትዩቶችን በአዲስ መልክ እንዲደራጁ አድርጓል። ቀድሞ ጂኦሎጂካል ሰርቨይ የሚባለው ተቋም ወደ ኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ኢንስቲትዩትነት በመቀየር አጠቃላይ ያሉንን የማዕድን ሃብቶች ለሚፈለገው አላማ ሊውሉ በሚችሉበት መልኩ ጥናቶችን በማቅረብ ሰፊ ስራን ለመስራት ከፍ ባለ መልኩ እንዲደራጅ ተደርጓል።
በሁለተኛ ደረጃ የማዕድን ልማት ኢንስቲትዩት ተዋቅሯል። ለማዳበሪያ፤ ለብረትና ለኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናትን ከማልማት አንፃር የዘርፉን አቅም ለመገንባት እና ያሉንን ሃብቶች ደግሞ ለሀገር ውስጥም ለውጭም ባላሃብት ለማስተዋወቅም፤ ኢንዱስትሪውን ጭምር ለማጎልበት የሚያስችል እንዲሆን፤ ብሎም ማዕድን ሚኒስቴር ጠንካራ አቅም ኖሮት የታለመውን አላማ እንዲያሳካ የማዕድን ኢንደስትሪ ልማት የተባለ ተቋም ተዋቅሯል።
የማዕድን ሃብት ልማት ትልቅ ካፒታልና ትልቅ እውቀት እንዲሁም ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ነው። ይህንን ከማረጋገጥ አንፃር የጂኦሎጂ ኢንስቲትዩቱም ሆነ የማዕድን ልማት ኢንስቲትዩቱ ከዚህ አንፃር ተገቢውን ስራ እንደሚሰሩ ነው የሚታሰበው።
አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከውጭ የምታስመጣቸውን የማዕድን ምርቶች ለማስቀረትስ እየተሰራ ያለው ስራ ምን ያህል ውጤታማ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡- እንደሚታወቀው በመንግስት አሁን ላይ ከተያዙ የትኩረት መስኮች አንዱ የኢነርጂ ማዕድን በስፋት ማምረት ነው። ለአብነት ያህል ብንጠቅስ ለሲሚኒቶም ሆነ ለሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች የሚያገለግለውን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሀገራት በየዓመቱ ከ275 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር እያወጣን ነው የምናስመጣው።
ግን ደግሞ እንዳልኩሽ ሰፊ የድንጋይ ከሰል ሃብት አለን። ስለዚህ የእኛ የድንጋይ ከሰል ያለበትን ጉድለቶች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ሰፊ የኢነርጂ አቅርቦት ሆኖ እንዲያገለግል ለስምንት ኩባንያዎች ፤ ለዘጠኝ ፕሮጀክቶች ፍቃድ ሰጥተናል። በሚቀጥሉት አንድ ዓመት ውስጥ ወደ ስራ በማስገባት ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ለማስቀረት ሰፊ እንቅስቃሴ ነው እየተደረገ ያለው።
ሌላው በተደጋጋሚ ርዕሱ በተነሳ ቁጥር ልብ የሚያሞቀው ከነዳጅና ከተፈጥሮ ጋዝ ጋር ያለው ጉዳይ ነው። ከእይታ አንፃር አስቀድሜ እንዳነሳሁት በመንግስት የሚታሰበው ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ ሀገሪቱ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ያለመችውን የብልፅግና መደላደል መሰረት ለመጣል የምንጠቀማቸው ወሳኝ አቅም አድርገን ነው እነዚህ ሃብቶች የምናስበው።
በዚህ መሰረት በስድስት ቦታዎች ላይ ማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ምርመራና ፍለጋ ለብዙ ጊዜ ሲካሄድ ነው የቆየው። ከዚህ ውስጥ ግን በተለይም በሱማሌ ክልል ኡጋዴን አካባቢ ያለው የሃብት መጠንም ተለይቶ በተለይ የተፈጥሮ ጋዙ ወደ ገበያ ሊቀርብ በሚችል ደረጃ ላይ ነው ያለው።
ይሄ ማለት ሃብት መኖሩ ከታወቀ ፤ አዋጭነቱም ተለይቶ ከታወቀ በኋላ ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ይኖራል። በተለይም ይህ የተፈጥሮ ጋዝ ማዳበሪያ ማምረት ከሚያስፈልጉ ግብዓች ዋነኛው እንደመሆኑ ምርቱን ቶሎ ወደ ገበያ የማቅረቡ ጥቅም አጠያያቂ አይደለም።
ከዚህ አንፃር ኡጋዴን አካባቢ ካለን ሃብት የሚመነጭ ይህ ሃብት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ነው ተስፋ የተጣለው። ሌላኛው ለማዳበሪያ ልማት ወሳኝ ሚና ያለው የፖታሽ ማዕድን ነው። ፖታሽ ደግሞ በሰፊው በአፋር ክልል ያለ ሃብት ነው። እነዚህን ሁለቱን ሃብቶች በማቀላቀል ነው ማዳበሪያ በሃገር ውስጥ ለማምረት በመንግስት ደረጃ ታልሞ እየተሰራ ያለው።
ይህንን ሃብት ለማልማት ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች በተለይ አሁን ላይ ይዞት ያለው ኩባንያ ወደ ምርት መግባት በሚገባው ጊዜ ላይ ነው ያለው። በተለይም ወደ ገበያ ከማቅረብ አንፃር ያጋጣሙ ችግሮች አሉ። እነዚያን ችግሮች እንዴት ነው መቅረፍ ያለብን? በሚሉ ጉዳዮች ላይ እየሰራን ነው ያለነው። በተለይም የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ የተረጋገጠና ለገበያም በሚቀርበበት ደረጃ የደረሰ ቢሆንም ኩባንያው ባጋጠመው ችግር ምክንያት እንደታሰበው ሊሆን አልቻለም። ይህንን ችግር ለመፍታት እየሰራን ነው ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- ፕሮጀክቱን የያዘው ኩባንያ በተጨባጭ ወደ ገበያ ማቅረብ ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ሚሊዮን፡- እዚያ አካባቢ ለብዙ ጊዜ ትልልቅ ኩባንያዎች ይገባሉ። ግን ቶሎ ውጤት ማምጣት ላይ ችግር አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ችግሮች እንደምክንያት ቀርቧል። ለምሳሌ የአለም የፋይናንስ ቀውስ መከሰቱን ተከትሎ እነዚህ ኩባንያዎች መዋእለ ንዋያቸውን በስፋት ለማንቀሳቀስ ተቸግረው ነበር። በሌላ በኩል ኩባንያቹ በውስጣቸው ካለው ችግር ጋር ተያይዞ በተባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት መግባት አልቻሉም።
እነዚህ አለምአቀፍ ኩባንያዎች ወደ ምርመራ ውስጥ ገብተው፤ ጥሬ እቃ መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ የምርት ፍቃድ ተሰጥቷቸው የሚገቡት ውል መሰረት በአለም አቀፍ ህግ ነው የሚዳኙት።
በኋላም ወደ ክስ በሚኬድበት ጊዜ በኋላ ብዙ ጣጣዎችን ይዞ የሚመጣ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር ተሳስሮ ነው ለውጭ ባላሀብቶችም ለልማት እንዲሰማሩ ስናስብ አብረን ማየት የሚገባን። ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ ከኦጋዴኑ ነዳጅ ሃብት ጋር ተያይዞ በተለይ በመንግስት ከተሰጡ ተስፋዎች አንፃር በፍጥነት ወደ ሽያጭ አለመገባቱ በህዝቡ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል። በዚህ ረገድ ፕሮጀክቱን የያዘው ኩባንያ ላይ ለምን እርምጃ መውሰድ አልተቻለም?
አቶ ሚሊዮን፡- ይህንን በሚመለከት አስቀድሜ እንዳልኩሽ በዋናነት እይታችንን ማስተካከል ወሳኝ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ። የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ተገኘ ተብሎ ከልክ በላይ መደሰት በራሱ ይዞት የሚመጣው አደጋ አለ። እንዳልሽው ኡጋዴን ላይ ብቻ ሳይሆን ጋምቤላና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ተገኝተቷል ተብሎ አንድ ሰሞን በየማህበራዊ ሚዲያው የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል።
ዞሮ ዞሮ ማዕድን የሰው ልጅ ለሚያስፈልገው መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ነው የሚጠቅመው። እርግጥነው፤ የእኛም ተቋም መረጃዎችን ዝም ብሎ መልቀቁ ነው ለእንዲህ አይነቱ ቅሬታ መፈጠር ምክንያት የሚሆነው። በመሆኑም ተራው ዜጋ በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ሰፍ አለ? ብዬ አልወቅስም። ግን ነገሮችን በልኩ ማየት ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን የህዝብን ደስታ ገድበን የጨፈገገ መንፈስ እንፍጠር ማለቴ አይደለም። ምክንያቱም ነገሮችን በአግባቡ ተረድቶ የሚሄድ ትውልድ ነው የሚያስፈልገን።
አዲስ ዘመን ፡- ግን አኮ ህዝቡ በሃገሪቱ እየተከናወነ ስላለው ነገር የመጠየቅ መብት አለው?
አቶ ሚሊዮን፡- ልክ ነሽ፤ ከማወቅም በላይ ግን ስንፍናን ነው የሚፈጥረው ብዬ ነው የማስበው። ማዕድን ስለተገኘ ሁሉም እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ስሜት መፈጠሩ ላይ እኔ አልስማማም።
መረጃው ለማደግ የምናደርገውን ትጋት እንድንጨምር የሚያደርግ ነው መሆን ያለበት። ኡጋዴን ላይ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ባለፉት 40 ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ምርምርና ፍለጋ ውጤት ነው። ብዙ ኩባንያዎች ገብተው ወጥተዋል። አሁን በአካባቢው ላይ ያለው ኩባንያ ምርት ወደ ገበያ ሊቀርብ በሚችል ደረጃ የደረሰ ነው፤ ገና የምንፈልገው አይደለም። ይህ ግልፅ ሊሆን ይገባል። ደግሞም ማዳበሪያ ፋብሪካ እናቋቁማለን ሰንል ዝም ብለን በሌለ ጉዳይ ላይ አይደለም።
ከዚህ ከሚገኝ ግብዓት ጭምር ታሳቢ በማድረግ ነው። የተቀረውን ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ ታልሞ ነው ኩባንያው ወደ ስራ የገባው። ምክንያቱም ይህ ፕሮጀክት ሰፊ የልማት ፍላጎታችንን ሊያሟላ የሚችል ሃብት የምናገኝበት ነው።
ከዚህ አንፃር እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ወደ ገበያ ሊገባ ሲል ነው ታሽጎ ምልልሶች እየተካሂዱ ያሉት ባለፉት ሁለት ዓመት ገደማ። ይሄ ነው በሰው ዘንድ የሚነገር ግን ውጤቱ የማይታይ ሆኖ ቅሬታንም ጭምር እየፈጠረ ያለው። እዚህ ጉዳይ ፈቃድ ወስዶ እያለማ ያለው ኩባንያ በተደጋጋሚ ወደ ስራ እንዲገባ ግፊት ተካሂዷል። በተፈለገው መልኩ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም። ስለዚህ ከውሉ አንፃር ተጠያቂነት ለማምጣት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ሚሊዮን፡- እንዳልኩሽ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል። ከዚህም አልፎ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራን ነው። ይህ ድርጅት እስካሁን ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ነው በቦታው ላይ ያካሄደው። እኛ ግን ፍላጎታቸን የነበረው ፈጥኖ ልማት ውስጥ ገብቶ አልምቶ ጥቅም ከዚህ ሃብት እንድናገኝ ነበር። ያ ባለመሆኑ አስተዳደራዊ ሂደት ተከትለን የሰራናቸው ስራዎች አሉ። ህጋዊ እርምጃ ደግሞ የሚከተል ነው የሚሆነው። ያው ጉዳዩ በህግ መስመር ውስጥ እየገባ ያለ በመሆኑ በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ አለምአቀፍ ድርጅት ስለሆነ በአለምአቀፍ ህግ የሚታይ ነው የሚሆነው። እንዳልኩሽ ግን የመጀመሪያ ምርጫችን እሱ አልነበረም፤ ምክንያቱም እኛ እንደሀገር የምንጠቀመው እንደዚህ አይነት አተካራ ውስጥ ባንገባና ፈጥኖ ወደ ልማት ብንገባ ነበር። ግድ ስለሆነብን ነው ወደዚህ የገባነው።
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየተሻሻለ የመጣበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ሚሊዮን፡- ከውጭ ምንዛሬ ግኝት አንፃር የተሰራው ዋነኛ ስራ መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉ ነው። በሪፎርም ስራዎችንም ጭምር ለገቢው መጨመር ትልቅ እገዛ አድርጓል።
አስቀድሜ እንደገለፅኩት ዘርፉን ለማልማት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች ከመለየትና ከማስተካከል ጀምሮ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ነው የተሞከረው። ለምሳሌ አንድ በደንብ መሰመር ያለበት ጉዳይ የማዕድን ሃብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ አይደለም የመንግስት ትኩረት የነበረው። እነዚህ በተፈጥሮ የተሰጡን ፀጋዎች ናቸው።
ከዚህ አንፃር ያደጉት ሃገራት ሃብታቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸው ነው ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ የቻሉት። ይሁንና ባለፉት ዓመታት በእኛ ሃገር በነበረው የተሳሳተ ግምት ማለትም ማዕድን ሲወጣ የሁከትና የብጥብጥ ምንጭ ይሆናል በሚል ማዕድንን መጠቀም የማያስችል ፖሊሲ መከተሏ ትልቅ ስህተት ነበር ባይ ነኝ።
ባለፉት ስርዓቶች ማዕድንን እንደአሉታዊ የልማት አካሄድ ተደርጎ ነው የተወሰደው። ማዕድን ላይ ያልተመሰረተ የልማት መንገድ ነው ሲባል የነበረው። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ዘርፉን በእውቀት ፤ በግልፅ ስትራቴጂና ቴክኖሎጂ ደግፎ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቱ እንዲያለማ በፖሊሲ መምራት ሲገባ ዘርፉን ወደ ዳር የማድረግ አቅጣጫ ነበር የምንከተለው።
አስቀድሜ ያልኩት ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈገው ግብዓት ከማዕድን ሃብት ነው የሚገኘው። ፈጣን የግብርና ልማትን አረጋግጣለሁ፤ ዘርፉን አዘምናለሁ የሚል መንግስት እንዴት ሆኖ ነው ማዳበሪያ በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር ወጪ እያደረገ ከውጭ እያመጣ ሊዘልቅ የሚችለው? ሀገር ውስጥ ይህንን ለማምረት የሚያስችል አቅም እስካለ ድረስ ሃገር ውስጥ ነው መመረት ያለበት። ስለዚህ የመንግስት አቅጣጫ ነው የተቀየረው። ማዕድንን ከሚረግም አስተሳሰብ ወጥተን የብልፅግና እና የልማት ምንጭ ለማድረግ እየሰራን ነው።
ለዚህም የሚያመች የአቅጣጫ ለውጥ አድርገናል። ይህም ደግሞ የወጭ ንግዱን መደገፍ ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ጭምር ለመቆጣጠር መንግስት ለማዕድን ሃብት ልማት እየሰጠ ያለው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል። አጠቃላይ የልማት አቅጣጫችን በማዕድን ላይ ጥገኛ እንዲሆን፤ ይልቁንም ሌሎች ዘርፎችንም ጭምር ይዞ እንዲወጣ የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን በተገቢው ትኩረት መምራት አለብን ብለን የፖሊሲ ማሻሻያ አካሂደናል።
ይህ በደንብ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ነው። ከዚህ ተነስቶ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት እጅግ የተለየ ነው። በማዕድን ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚን ከመገንባት ወጥተን መሰረተ ሰፊ የሆነ ኢኮኖሚ እናልማ የሚል መነሻ ተይዟል።
ለዚህም ነው የወጭ ንግዱ ላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚታየውን እድገት ማስመዝገብ የተቻለው። በተጨማሪም ከዚህ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ለውጥ በማድረጉና ከተከናወነው ሪፎርም ስራ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን መውሰድ ያስፈልጋል።
እንዳውም አሁን ሃገራችን ጦርነት ውስጥ ባትቆይ ኖሮ ከዚህ በላይ ማስገባት በቻልን ነበር ። አሁን የተገኘው በባህላዊ፤ በአነስተኛና በጥቂት ኩባንያዎች ተመርቶ የመጣ ገቢ ነው።
ይሁንና ለኤክስፖርት የሚሆኑ ማዕድናትን ማልማት ይቻላል። በተለይም በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ክምችት ውስጥ እኛ ሃገር ያለው የታንታለም ክምችት አለ። አሁን አሁን እየመጡ ያሉ በጣም ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ታንታለም በስፋት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ መኪና መስፋፋት በአለም ላይ ፍላጎት በጣም እየጨመረ ነው የመጣው። ስለዚህ እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ ፈልጎ አልምቶ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረጉ ጉዳይ ገና በጣም ሰፊ ሃብት ነው ያለን። በአጠቃላይ ችግሮች ውስጥ የነበርን ቢሆንም መንግስት በሰጠው ትኩረት የመጣ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል። ያለንን ሰፊ እድል በአግባቡ ለመጠቀም ብዙ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ልማቱ አሁንም ቢሆን ዘመናዊ አሰራሮችን ከመከተል አኳያ ወደኋላ የቀረ ነው። ከዚህ አኳያ የተደረጉት ጥረቶች ምንድናቸው?
አቶ ሚሊዮን፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ዘርፉን ለማዘመን ከተኬደባቸው አቅጣጫዎች አንዱ የፖሊሲ ግልፀኝነትና በቂ ትኩረት መስጠት ላይ ነው። ከዚህ አንፃር በፍኖተ ብልፅግና ትኩረት ከተሰጣቸው ሃገራዊ ኢኮኖሚ ልማት ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ ማዕድን ሃብት ላይ የተሰጠ ትኩረት ነው።
ይሄ ማለት ማዕድንን ማልማት አጠቃላይ ኢኮኖሚን ከማልማት እይታ ጋር ነው ተያይዞ የሚታየው። ይህንን ተልዕኮውን እንዲወጣ ማዕድን ሚኒስቴር ከአደረጃጀቱ ጀምሮ የአሰራር ስርዓቱን የማሻሻል፤ በእውቀት ላይና በዘመናዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስራን ለመስራት ሲባል ነው የጂኦሎጂ ኢንስቲትዩት በዚያ ደረጃ ራሱን እንዲያደራጅ የተደረገው።
የማዕድን ልማትም ኢንስቲትዩትም በተመሳሳይ መልኩ እንዲደራጅ ተደርጓል። እነዚህ ሥራዎች በአጠቃላይ በማዕድን ሃብታችን ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለይቶ ዘርፉን ለማዘመን ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ ታሳቢ ተደርገው የተከናወኑ ናቸው። እንደተባለው ለዘመናት በባህላዊ መልኩ ማዕድናት ሲወጡ ነው የቆየው። ማህበረሰቡ በራሱ በአካባቢው ያለውን ሃብት በአግባቡ ተጠቅሞ ሃብት አፍርቶበታል።
ይህም የማህበረሰቡን እውቀት፤ ክህሎት በመጠቀም በህብረት አብሮ የመስራት እና በአደራጀት የመስራት ሥራን ለማምጣት አስችሏል። ይህን አደረጃጀት የበለጠ ለማጠናከርና አሰራሩን ለማዘመን በሚኒስቴሩ በኩል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። ምክንያቱም ደግሞ በተናጠል ከሚያደርገው ጥረት ይልቅ በጋራ የሚደርገው እንቅስቃሴ የበለጠ ጥቅም ያለው በመሆኑ ነው።
በማህበር ተደራጅተው በጋራ ሲንቀሳቀሱ የተሻለ ውጤት ነው የሚያገኙት። በአገኙት ገንዘብ ህይወታቸውን ለማሻሻል፤ ለቤተሰባቸውም ጥሪት ለማፍራት ጭምር የሚጠቅማቸው በመሆኑ ነው። ይህንን ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራን ነው ያለነው።
ከዚህ አኳያ ለአብነት ያህል ብጠቅስልሽ ባህላዊ አምራቾቹ የሚያስፈልጋቸውን የሙያ ፣ የሥራ፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ከማስተዋወቅ አንፃር ከእኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም፤ ሌሎችም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየሰሩ ነው ያሉት። እነዚህ ማዕድንን በጋራ ከሚመረትባቸው ቦታዎች ጋር በተለይም ከወርቅ ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የማድረግ ስራ ከክልሎች ጋር እየሰራን ነው።
ባህላዊ ማህበራቱ ካፒታል እያጠራቀሙ የተሻለ ቴክኖሎጂ ወደሚጠቀሙት ልዩና አነስተኛ ደረጃ ተሸጋግሮ የሚጠቀሙትን ቴክኖሎጂና ካፒታል እየጨመሩ እንዲሄዱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው። በሂደት በኩባንያም ጭምር የሚሰማሩበትን አቅጣጫ መከተል አለብን ብለን እየሰራንም ነው።
ይህም አንደኛ ቀጣይነት ባለው መልኩ በአካባቢያቸው ያለውን ሃብት በአግባቡ ተጠቅመው ህይወታቸውን የሚቀይሩበትን፤ ያገኙትንም ገንዘብ ደግሞ ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥሪት ማፍራት የሚችሉበትን እድል ጭምር ለማረጋገጥ ያስችላል። ከዚያ በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ አልሚዎች የተለያዩ ቴክኖሎኖጂዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ይዘው እንዲገቡና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ የበኩላችን ጥረት እያደረግን ነው ያለነው።
አጠቃላይ የማዕድን ሃብታችንን ነዳጅ፣ ጂኦተርማልንም ጭምር ዘመናዊ በሆነ መልኩ እና የአካባቢ ብክለትን እንዲሁም መራቆትን በሚቀንስ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል በሰፊው ነው እንቅስቃዎች እየተደረጉ ያሉት። እርግጥ ማዕድን በተገኘበት ቦታ ላይ ቁፋሮ መኖሩ የማይቀር ነው።
ቁፋሮ ሲኖር አካባቢ መጎዳቱ የማይቀር ስለሆነ ከቁፋሮ ጋር ተያይዞ የተጎዳ አካባቢን መልሶ በሚያገግም መልኩ መጠቀም የሚያስችል ስርዓት ነው እየተዘረጋ ያለው። እዛ አካባቢ ላይ ማዕድን ሲወጣ ዘላቂ የማህበረሰብና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አብረው የሚሰሩ ስራዎች ናቸው።
በዚያ ደረጃ የቴክኖሎጂውን ሽግግር አስቀድሜ ባነሳሁት መነሻ ዘርፉም ትኩረት ያገኘ ባለመሆኑ የትኛውን ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ በውል አይታወቅም ነበር። ሰፊ ጉልበት እያለ ግን በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሃብት በአግባቡ ወደ ጥቅም ላይ መቀየር በማይችል መልኩ ሲመራ የነበረው። አሁን ላይ ከዚህ ኋላቀር አሰራር ለመውጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
እነዚህ ስራዎች በቀጣይ እያደጉ የሚሄዱ ናቸው። አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር የነበረ እንዲሁም በሙስና እና ሌብነት የታጠረ እንደነበር እሙን ነው። ከዚህ አኳያ በተለይ የማዕድን ፈቃድ አሰጣጡ ተመሳሳይ ብልሹ አሰራር እንዳይፈጠር ምን አይነት ጥንቃቄዎች እየተደረጉ ነው ያሉት? አቶ ሚሊዮን፡- አስቀድሜ ካነሳኋቸው የሪፎርም ስራዎች አንዱ ይሄ ነው። ግልፀኝነትን ማስፈን ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው።
የፈቃድ አሰጣጡ ግልፀኝነት ያለው ለማድረግ አሰራሮች ተዘርግተዋል። የምርመራ ፍቃድ ወስዶ በአንድ አካባቢ ላይ በተለይ በስፋትና በኩባንያ ደረጃ የሚመረቱ ማዕድናት አስቀድመው የምርመራ ስራ ወይም ፍለጋ ስለሚያካሂዱ ፍቃድ አሰጣቱ በግልፅ ነው የሚካሄደው።
ከተቋሙ ህንፃ ግንባታ ጀምሮ ሁሉም ሥራ በገሃድ እንዲከናወን ቢሮዎችን መስታወት ብቻ እንዲገነቡ አድርገናል። ይህም የተደረገው በአዲስ መልኩ ተቋሙን ለመቀየርና ግልፀኝነትን ለማምጣት ያለመ ነው። አንዱ የስራ ሂደት ከሌላው ጋር በፊት ለፊት የሚናበብበት፤ በመግባባትና በመተመማን ላይ የተመሰረተ የስራ አካበቢ እንዲኖር ነው ከሪፎርሙ ጋር እየተሰራ ያለው።
አሁን ተደብቆ የሚሰራ ስራ የለም። ፍቃድ ጠያቂው ምን ምን አሟልቶ ሲገኝ የምርመራ ፍቃድን አግኝቶ እንደሚፈቀድለት ፊት ለፊትና ያለምንም ድብብቆሽ ነው እንዲያውቅ የሚደረገው። ምክንያቱም ደግሞ ኢንቨስትመንቱ ሰፊ ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። ፈቃድ ጠያቂው በመጀመሪያ ምርመራውን በራሱ አካሂዶ በራሱ አካባቢ ላይ የማዕድን ሃብት መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ነው ፍቃድ የሚወስደው።
ስለዚህ የማዕድን ሃብት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው የማምረት ፍቃድ የሚሰጠው። በተለይም ትልቅ የውጭ ኩባንያዎች ፈቃድ እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሄዶ የሚፀድቅ ነው። በሃገር ውስጥም ሆኖ ራሱ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች በተመሳሳይ መልኩ ነው የሚሰጠው።
በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ዓመታት አስቀድሞ የነበረውን አካሄድ ዘርፉንም ጭምር ሰው እንዳያይ የመጋረድ ስራ ነው ሲሰራ የነበረው። በመሆኑም አሁን እየተሰራ ያለው ስራ ዘርፉ ላይ የነበረውን መጋረጃ ጭምር ነው ለማንሳትና ግልፅ በሆነ መልኩ ይህ ሃብት ለሌሎች ዘርፎች ማደግ መሰረት እንዲጥል እየተሰራ ያለው።
በሌላ በኩል የማዕድን ልማት እውቀትን ፤ ክህሎትና ካፒታልን የሚጠይቅ ስራ እንደመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰማራ ማንኛውም አካል ራሱን ተማምኖ ነው ለፈቃድ ጥያቄ የሚመጣው።
ስለዚህ አስቀድሞ የነበሩ አሰራሮችን በዚህ መልኩ ለማስተካከል በሰፊው ነው እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ያሉት። የፖሊሲ ማሻሻያው ሃገር እንዲለውጥ ጭምር እየተሰራ ነው። በተለይም ላለፈው አንድ አመት ጦርነት ውስጥ በመቆየታችን እና አሁንም ድረስ ከጦርነት ድባብ ያለመውጣታችን ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ ቆይቶብናል። ከሁሉ በላይ ማዕድን ስለተገኘ ብቻ ሁሉም እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበት ግንዛቤ ማስጨበጡ ላይ ትኩረት ያደረግነው።
ይህም ማለት የሚበዘበዝ ሃብት እንደተገኘ ተደርጎ የኖረው እሳቤ እንዲለወጥና ከሌላው የልማት ስራ ጋር ተሰናስኖ ዘላቂ ልማት ማምጣት ይገባል ወደሚለው መምጣት ላይ ትኩረት ማድረጋችን በቀጣይ ላቀድነው የልማት ግብ ወሳኝ ሚና አለው። አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም ከፈቃድ አሰጣጡ ጋር ተያይዞ በተለይ የሃገር ውስጥ ባላሃብቶችን ለማሳተፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለሙስና የሚያጋልጡ አሰራሮች ይፈጠራሉ የሚል ስጋት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ።
ከዚህ አንፃር የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው? አቶ ሚሊዮን፡- እኔ ከፍቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የተነሳው ስጋት ለእኔ ውሃ የሚያነሳ አይደለም። ገና መቼ ጀመርንና ነው ስጋት የሚናሳው?። ባይሆን አሁን የተጀመረው መጠነ ሰፊ ጉዳይን የምንረዳበት መንገድ ገብቶናል ወይ የሚለው ነገር የበለጠ ያሳስበኛል።
ምክንያቱም ለእኔ ይህ ስጋት ራሱ የመነጨው ቀድሞ ዘርፉን የሃብት መበዝበዣ ምንጭ ነው የሚል እሳቤ በስፋት በመሰራጨቱ ነው። ሌላው ይቅርና በዚህ ስራ የቆዩ የእኛ ባለሙያዎች ጭምር ማዕድንን የሚረዱበት አግባብ ገና ብዙ መሻሻል የሚገባው ነው። ጉዳዩ ለአንድ ኩባንያ ምርት እንዲያመርት ፈቃድ እንዲሰጥ ማድረግ ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ልማትን ልናረጋግጥ ከሆነ እየተባለ ያለውን ከፍ ብሎ ማየት ይፈልጋል።
በመሰረቱ ረጅም እድሜ ካላቸው ተቋማት አንዱ የእኛ መስሪያ ቤት ነው። ስለዚህ የሆነች ቦታ ላይ ፍቃድ ከመስጠት ያለፈ ማሰብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ማዳበሪያ ፍላጎታችንን ማሟላት ማለት በየቤታችን ያለውን የዳቦ ጥያቄ መመለስ ማለት ነው።
በየከተማው ያቋቋምነውን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥጥ ማቅረብ ማለት ነው። ስለዚያ ነው እያወራን ያለነው። እንዳልኩሽ ገና ምንም ባልተጀመረበት ሁኔታ ‹‹ስጋት አለኝ›› የሚል ነገር ጉዳዩን ለዘመናት በነበራቸው አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። በዚህ መልኩ የሚታሰብ ከሆነ እኔ ጉዳዩን ለመረዳት ይቸገራሉ ብዬ ነው የማምነው።
አጠቃላይ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በሚያሳድግ ዘርፍ ላይ ነው እየተነጋገርን ያለነው። ስለዚህ ከሚኒስቴሩ የሚጠበቀው ነገር ማዕድን የሚባል ቁንፅል ነገር ማውጣት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሀገሪቱን የልማት ዘርፎች የማበልፀግ ስራ ነው።
ለምሳሌ የኢንዱስትሪ እናት የሚባለውን የብረት ማዕድንን ማውጣት ማለት ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ብቻ አይደለም፤ ኮንስራክሽን፤ ትራንስፖርትም ሆነ ሌላውንም የልማት መስኮች ማበልፀግ ማለቴ ነው። ብረትን የሚያመርቱ ሃገራት የቆረጡ መሪዎች ያሏቸው ናቸው።
በነገራችን ላይ እኔ እየተናገርኩ ያለሁት ነገር ቅዠት አይደለም። መንግስት ከቆረጠ ብልፅግናን ማምጣት እንችላለን። በተመሳሳይ ይህች ሃገር ሰፊ የታንታለም ማዕድን ሃብት አላት። ታንታለም እንደሚታወቀው የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች በሙሉ የሚመረቱበት የማዕድን አይነት ነው።
ይህንን ማዕድን በስፋት አወጣን ማለት መገጣጠም ብቻ ሳይሆን በራሳችን ስልኮችን እያመረትን የውጭ ምንዛሬ እንታደጋለን፤ እናስገባለንም ጭምር ማለት ነው። እንዳልኩሽ አሁን እኮ ገና ከጦርነት ድባብ ገና አልወጣንም፤ ለልማት የሚመች ከባቢያዊ አየር ባልተፈጠረበት ሁኔታ ስጋት ነው ብሎ ለዘርፉ ማነቆ ማበጀት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።
በመሰረቱ ተሰጡ የተባሉት ጥቂት ፍቃዶች ናቸው፤ እነዚህም በዚህ ደረጃ ችግር አለባቸው ብዬ አላስብም። አጠቃላይ አሰራሩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚፀድቅ በመሆኑ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ገና ግን ብዙ ፍቃድ እንሰጣለን። ምክንያቱም አንዳንዱ ሥራ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ማሰር የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።
በተመሳሳይ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ተያይዞ የተነሳውም ስጋት እኛም አስቀድመን ስለለየነው ነው በሚኒስቴሩ ስር ያሉትን ተቋማት በአዲስ መልክ ማደራጀት ያስፈለገው። ስለዚህ ይህ ስራ በዋናነት የእነዚህ ተቋማት ትኩረት አድርገው ነው የሚሰሩት። ከዚህ በተጨማሪ ማዕድናቱ በሚገኙባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን ውስጥ ስርዓተ-ትምህርት ተቀርፆ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በስፋት የማምረት ስራ ተጀምሯል። ለምሳሌ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ላይ የጂኦሎጂና የማዕድን ሃብትን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው።
አካበቢው ላይ ያሉ ኩባንያዎች የምርምርና የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ነው እየተደረገ ያለው። በተጨማሪም የስነምህዳርና የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ጭምር አያይዞ እንዲሄድ እየተደረገ ነው ያለው።
ስለዚህ ከምርምር ተቋማት ጭምር የኢንዱስትሪ ትስስር እንዲመጣ አቅጣጫ ተሰጥቶ ነው እየተሰራ ያለው።
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል በተለይም ማዕድናት በሚወጡበት አካባቢዎች የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያለመሆን ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ሚሊዮን፡- እንደአጠቃላይ የማዕድን ሃብት የሁሉም የሃገራችንን ዜጎች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መልማት ነው ያለበት። ግን ደግሞ በወሳኝነት በተለይ ማዕድን በሚገኝባቸው አካባቢዎች ማዕድኑ ልማት ላይ እንዲውል ማህበረሰቡ መጠቀም መቻል አለበት።
ምክንያቱም ደግሞ ልማቱ የእኔ ነው ብሎ ሊይዝና ሊንከባከብ የሚችለው ተጠቃሚ መሆን ሲችል ነው። ይህንን ደግሞ በተጨባጭ አይተናል። አንዳንድ የሲሚኒቶ ኢንዱስትሪዎች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ በማድረጋቸው ከህብረተሰቡ ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ነው ያየነው።
ስለዚህ ከግንዛቤ አንፃር አልሚዎች ማህበረሰቡን ጠቅሞ መጠቀም ለኢንዱስትሪ ልማትና ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተረድተው ሊሰሩ ይገባል። በመሰረቱ ዘላቂ ልማት የሚባለው እኮ አሁን ያለውን ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለው ትውልድ ጨምሮ ማሰብና ተጠቃሚ ማድረግንም ያካትታል። እኛም ያንን ነው ተግባራዊ እያደረግን ያለነው።
ስለዚህ ማዕድናቱ ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ ለምሳሌ ማዕድናቱ በሚለሙበት አካባቢ ራሱ ማህበረሰቡም ጭምር በጉልበቱም ጭምር ተደራጅቶ እንዲሰራ ነው ድጋፍ እየተደረገለት ያለው። አስቀድሜ ባህላዊ አምራቾች ያልኩሽ የዚሁ አካል ነው። ለምሳሌ ወርቁን ካመረቱ በኋላ ለሽያጭ ሩቅ ሳይሄዱ ባሉበት ስፍራ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበትንም ጭምር ነው እየሰራን ያለነው። ስለዚህ በየወሩ የኤክስፖርት ስራ ጭምር ይገመገማል።
ለምሳሌ ሚድሮክ በ2008 ዓ.ም በነበሩት ሀገራዊ ሁከቶች ተዘግቶ ነው የቆየው። ከዚህ በኋላ ግን ከማህበረሰቡ እና ከመንግስት ጋር በተደረገ ውይይት ወደ ተግባር እንዲገባ ተደርጓል። በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሕክምና ተቋማት ፤ መንገድ፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በመሳተፍ በጣም ሰፊ የልማት ስራዎች ነው እየሰራ ያለው። አስቀድሞ የአካባቢው ልጆችም ጭምር እንዲቀጠሩ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ያለው።
በተመሳሳይ ሌሎች ኩባንያዎች ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ዋነኛው የትኩረት አቅጣጫ አድርገን ነው የተከተልነው።
አዲስ ዘመን፡- የድንጋይ ከሰል የማምረት ሂደት ለአካባቢ ብክለት የሚዳርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት የአለም ሀገራት ወደታዳሽ የሃይል ምንጭ እያዞሩ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም ከምትከተለው ከብክለት የፀዳ ስትራጂ ጋር በተያያዘ እንዴት ነው አጣጥሞ ለመሄድ የታሰበው?
አቶ ሚሊዮን፡- በነገራችን ላይ በአለም ላይ የሚነገረውና እየሆነ ያለው ነገር አንድ አይነት አይደለም። ለምሳሌ አሜሪካም ሆነ ቻይና በዚህ አመት የተጠቀሙት የድንጋይ ከሰል እስካአሁን ተጠቀመው ከሚያውቁት በእጅጉ የላቀ ነው። እኛ እንዳውም በአንዳንድ ጉዳይ የቀደምን ነን ባይ ነኝ። ለምሳሌ የኢንዱስትሪ እድገታችን በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑና የምንከተለውም አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመሆኑ አካባቢን ከመበከል አኳያ ሚናችን በጣም አነስተኛ ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን የልማት አቅጣጫችን ከመነሻውም በታዳሽ ሃይል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በዚህ በኩል የሚነሳው ስጋት ያንን ያህል ውሃ የሚያነሳ አይደለም። የሃይል ማመንጨት ስራችንን በሙሉ በዚሁ የልማት ስትራቴጂ የተቃኙ ናቸው። እርግጥ ነው፤ የሃይል አጠቃቀማችን በጨመረ ቁጥር የእንፋሎትንም ሆነ የድንጋይ ከሰል ሃብታችንን መጠቀማችን የማይቀር ነው። በሌላ በኩል አሁንም ቢሆን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የድንጋይ ከሰልን ከውጭ ነው የምናስመጣው።
ይህ ማለት አሁን ላይ አድገዋል የምንላቸው ሃገራት ናቸው ለእኛ እየሸጡልን ያሉት ማለት ነው። በአጠቃላይ እኛ በከፍተኛ ሃላፊነት ነው ልማቱ እያከናወንን ያለነው የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ምክንያቱም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በወሳኝ መልኩ የሚቀይር ስራ እየሰራን ባለመሆኑ ነው። ከዚህም በኋላ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ይህንኑ አቅጣጫ የሚከተሉ ነው የሚሆኑት። ደግሞ ከድንጋይ ከሰል ስናመርት የሚያመነጨው በካይ ጋዝ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለግምትም የሚገባ አይደለም።
በተጨማሪም ከአቅማችን በላይ የሆነ ታዳሽ ሃይል ተንጠራርተን እያለማን ነው ያለነው። ፈጥነን እንልማ እያልን ከሆነ በእጃችን ያሉ ሃብቶችን ነው መጠቀም የሚገባን። ስለዚህ በሚዛኑ ነው ነገሮችን ማየት ያለብን ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሚሊዮን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 25/2014