የኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጠቃሚ ስፋት፣ የተለያዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ የቴክ-ቁሶችና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አድማሶች እድገት ማሳየታቸው እየተስተዋለ ነው።
ይህንን ተከትሎ ዕውቀትና ክህሎትን ለማሳደግና በዘርፉ የሰፋ ግንዛቤ እንዲኖርም በመንግሥት ተቋማት በኩል በየግዜው ሥራዎች ይከናወናሉ። ከዚያም ባለፈ ሕግ፣ መመሪያና የአሠራር ሥርዓት ይዘረጋል።
በዋናነት የመንግሥት የዘርፉ ተቋማት እያከናወኗቸው ካሉ የማስፋፊያና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የመምራት ተግባራት ባሻገር ማኅበረሰቡ (በተለይ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ቁሶችን ተጠቃሚ የሆኑትን) ስለሚጠቀሙት ጉዳይ ወቅታዊ መረጃዎችና የጥንቃቄ ግንዛቤዎች እንዲያዳብሩ በርከት ያሉ መረጃዎችን በየጊዜው ይሰጣሉ።
ለዛሬ በርዕሰ ጉዳይነት ከመረጥናቸው ውስጥ “ተግባራዊነትና ደህንነት” እንዲሁም ዲያስፖራው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን እውቀት ከማካፈል ጋር ተያይዞ ሊኖረው ስለሚገባ ድርሻ ይገኙበታል።
ተግባራዊነት (Functionality) እና ደህንነት (security)
በሳይበር ምህዳሩ ውስጥ ማንኛውም ሶፍትዌር፣ መተግበሪያ አሊያም ማንኛውም ጥቅም ላይ የሚውል ሲስተም ሲበለፅግ ወይም ጥቅም ላይ እንዲውል ሲሠራ ራሱን የቻለ ሂደት ያለው ሲሆን ከአሠራር ሂደቱ ጋር ተያይዞ ሊታሰብበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ አለ። ይህም የደህንነት ጉዳይ ነው።
አገልግሎት ወይም ሰርቪስ ማግኘትና ደህንነት ማስጠበቅ ምንና ምን ናቸው?
አንድ ሲስተም ዒላማ ተደርጎ የተሠራበትን የአሠራር ሂደት ተከትሎ ከሥርዓቱ /system/ የሚመጡ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት መመሪያዎችን፣ ቅጾችን፣ ግብዓቶችን እንዲሁም መጠይቆችን በመከተል እና ምላሾችን በመስጠት ተጠቃሚው የሚፈልገውን አገልግሎት በሚፈልገው ጊዜና ቦታ እንዲያገኝ ማድረግ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ እንደተጠቃሚ አገልግሎት ሰጪ ለሆነው ሥርዓት ግብዓቶችን በሚቀርብበት ጊዜ፣ ለእያንዳንዱ የአሠራር ሂደት ከሥርዓቱ ጋር በሚኖር መስተጋብር፣ ከሥርዓቱ ካለ ባልታወቀ ክፍተት የተነሳ አገልግሎቱን በማግኘት ፋንታ የሥርዓቱን ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ክስተት ሊነሳ ይችላል።
ስለዚህ አንድ ሲስተም አገልግሎት /Service/ እስከሰጠ ድረስ የደህንነቱ ጉዳይም እንዲሁ መጠበቅ ይኖርበታል።
የትኛው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ?
አንድ ሥርዓት አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ እስከተሠራ ድረስ ለተጠቃሚዎች ቀላል፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ አስተማማኝ መሆኑ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ለመሥራት ይረዳል። በዚያው ልክ ደግሞ ሥራዎችን ወይም አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር ማስቻሉ እንዳለ ሆኖ ለጥቃት የመጋለጥ እድሉም በዚያው ልክ ይሰፋል።
ይህም የተጠቃሚዎችን መረጃ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን የሚገታ እንዲሁም ሰርቪስ የመስጠት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ የሚያስቆምና ብሎም ሥርዓቱን ከጥቅም ውጭ ሊያደርጉ ከሚችሉ እና አጠቃላይ የሥርዓቱን የደህንነት መዋቅር ከሚያፈርሱ ነገሮች ደግሞ መጠበቅ የግድ ነው። ስለዚህ ሁለቱም ነገሮች በማስተባበር ሊተገበሩ ይገባል።
ይህን ማን በኃላፊነት ሊሠራው ይገባል?
የኃላፊነት ደረጃውን ለመወሰን ያክል ከሥርዓቱ ንድፈ ሃሳብ ከመሠራቱ በፊት ጀምሮ ባሉ የሥርዓት መስፈርቶች /requirements/፣ ሥርዓቱ ሥራ ላይ ሲውል፤ ብሎም በሥራ ላይ እያለም በሚኖረው የሥራ ሂደት ጨምሮ ባሉት ደረጃዎች አስፈላጊውን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የደህንነት ፍተሻዎችን እና ግምገማዎችን በመተግበር በሚያልፍበት ሁኔታ የሚኖሩ ተሳታፊዎችን ያካትታል።
ይህም አልሚዎችን፣ የፍተሻ ባለሙያዎችን፣ የሲስተም ባለቤቶችን፣ የሆስቲንግ ድርጅቱን፣ የሲስተሙ አስተዳዳሪዎችን (አድሚኖችን) እንዲሁም ማንኛውም ከሲስተሙ ጋር ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ መስተጋብር ሊኖረው የሚችል አካል ሊመለከተው ይችላል።
ይህም አልሚዎች ከንድፈ ሃሳቡ በሁለቱም መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች በማካተትና በማስታረቅ ሲስተሙን ማልማት ይገባቸዋል፤ የፍተሻ ባለሙያዎች መሠረታዊ እና ቴክኒካዊ የሆኑ የፍተሻ ዘዴዎችን እና ክህሎቶችን በመጠቀም የተመረተው ሲስተም ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ሰጭ ሲስተም መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፤ አድሚኖችና የሆስቲንግ ድርጅቱ በተግባር ላይ ሲውል የመሠረተ ልማቶቹን ደህንነትና ብቃት ጨምሮ አስፈላጊውን እና ጊዜውን የጠበቀ እድሳትን ቁጥጥርን በመከታተልና በመተግበር ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።
የሥርዓቱ ባለቤቶችም ከአልሚዎች ጋር ከንድፈ ሃሳቡ ጀምሮ የሚኖረውን የአሠራር ሂደት እና ፍላጎት (የሲስተሙ ሪኳየርመንት) በማስማማት ማጣጣም ሊኖርባቸው የሚችሉ ሃሳቦችን በማስተባበርና በማስተግበር እናም ከሌሎቹም አካላቶች ጋር በመሆን ደህንነቱ የተጠበቀ ሲስተም እንዲኖር መሥራት አለባቸው።
እንዲሁም ማንኛውም ከሲስተሙ ጋር ቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መስተጋብር ሊኖረው የሚችል አካል የሲስተሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ሊያስተጓጉል እና ሊያውክ የሚችል ድርጊትን በመከላከል እንዲሁም መረጃን ለሌላ ሶስተኛ ወገን አሳልፎ ባለመስጠት ደህንነቱን ማስጠበቅ ይገባል።
ምን ሊደረግ ይገባል?
አንድን ሲስተም ለማበልጸግ ሲታቀድ ከንድፈ ሃሳቡ እነዚህን ሃሳቦች ታሳቢ በማድረግ እና ተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜም በንድፈ ሃሳቡ መሠረት ፖሊሲዎችንና ስታንዳርዶችን ሁሉ በመጨመር የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን የተሟላ ማድረግ ይገባል።
በተጨማሪም የተጠቃሚዎችንም የክህሎት ክፍተት በተቻለ መጠን ተጠቃሚ ተኮር የሆኑ የእርዳታ ወይም ፍንጭ ሰጭ መመሪያዎችን መልዕክቶችን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጡን ሂደትም ሆነ ደህንነቱን ማስጠበቅ ይገባል።
ማልዌር ምንድን ነው?
የዝግጅት ክፍላችን ሌላው ከኢንፎርሜሽን ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘውና አንባቢዎቻችን ቢመለከቱት ሊያተርፉበት አሊያም አንዳች ግንዛቤ ሊይዙበት ይችላሉ ብሎ ያሰናዳው መረጃ “ማልዌር ምንድነው” የሚል ርዕሰ ጉዳይ ነው።
ይህ መረጃ በብዛት በኮምፒውተርና የመረጃ መረብ ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት የሚነሳ ጥያቄ ከመሆኑ አኳያ ማብራሪያውን አቅርበንላችኋል። ማልዌር /Malware/ የሚለው ቃል “malicious software” ከሚሉ ሁለት የእንግሊዘኛ ቃላት በመውሰድ የተሰጠ ስያሜ ነው።
ማልዌር የራስ ወዳልሆነ ኮምፒውተር ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለመግባት እና ጉዳት ለማድረስ ታስቦ የሚዘጋጅ “አጥፊ ሶፍትዌር” ነው። አጥፊ ሶፍትዌሮች ዓይነታቸው የሚለያይ ሲሆን ስፓይዌር /spyware/፣ ራንሰምዌር / ransomware/፣ ቫይረስ /viruses/፣ ዋርም /worms/፣ ትሮጃን ሆርስ /Trojan horses/፣ አድዌር /adware/ ወይም ማንኛውም ዓይነት ኮምፒውተርን ሊጎዳ የሚችል ኮድ የያዘ ሊሆን ይችላል።
በምን መንገድ ልንከላከለው እንችላለን?
ኮምፒውተር በተለያዩ ምክንያቶች ለማልዌር ጥቃት ሊጋለጥ የሚችል ሲሆን ከነዚህም መካከል በኦፕሬቲንግ ሲስተም ዲዛይን ላይ በሚፈጠር ችግር በአንድ ኔትወርክ ውስጥ ሁሉም ኮምፒውተሮች ተመሳሳይ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀሙ ከሆነ ወይም ለተጠቃሚዎች በርካታ ፈቃዶችን የሚሰጥ ከሆነ በቀላሉ ለጥቃት ሊጋለጥ ይችላል።
ማልዌር ጥቃትን ለመከላከል ሊወሰዱ ከሚገቡ ጥንቃቄዎች መካከል በኢ-ሜይል የሚላኩ አባሪዎችን ከመክፈታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ፤ ከአጠራጣሪ ድረ-ገጾች መራቅ፤ ዝመናዎችን በየጊዜው እየተከታተሉ መጫን እና ጥራት ያላቸው ፀረ-ቫይረስ ፕሮግራሞችን መጠቀም ይመከራል።
የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ባለፉት ስድስት ወራት
ከላይ ካነሳነው ርዕሰ ጉዳይ ብዙም ሳንርቅ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን አስመልክቶ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ባለፉት ስድስት ወራት የተከሰቱትን አጠናክሮ ይፋ አድርጓል። በዚህም በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከተሰነዘሩ 3ሺ406 አደገኛ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከ96 ከመቶ በላይ የሚሆኑትን ማክሸፉን አስታውቋል።
ኤጀንሲው በ2014 በጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከ3ሺ400 በላይ “አደገኛ” የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መከሰታቸውን እና ከዚህ ውስጥ ከ96 ከመቶ በላይ ያህሉን ማክሸፉን ገልጿል። ቀሪዎቹ ከ4 ከመቶ በታች የሚሆኑትን የጥቃት ሙከራዎች ደግሞ ምላሽ በመስጠት ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታውቋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በ2014 ዓ.ም የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ 3 ሺህ 406 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል። ካለፈው የ2013 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዚህ በጀት ዓመት የተሞከረው የሳይበር ጥቃት ሶስት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ጥቃቱ ከዓመት ወደ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ዋና ዋና ምክንያቶች ዓለም አቀፍ የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚነት ማድረግ፣ በዘርፉ ወንጀልን ለተለያዩ ዓላማዎች የሚጠቀሙ ተዋንያን መበራከት፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና የጂኦ-ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች መጨመር እንዲሁም አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ናቸው። በስድስት ወራት ከተሞከሩ ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛዎቹን ጥቃቶች የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ማክሸፉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ ፣ በተቋማት እና በአገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን ነበር ብለዋል። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች ትኩረታቸውን በፋይናንስና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ያነጣጠሩ እንደነበር ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት አይነቶች ውስጥም የድረ-ገጽ ጥቃት ፣ የማልዌር ጥቃት እና የመሠረተ-ልማት ቅኝት ጥቃቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።
እነዚህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች በተለያዩ ሕገወጥ አካላት የተሰነዘሩ መሆናቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ጥቃቶቹ በተለይም ከሕልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ካሉ አገር የማፍረስ ተልዕኮ ካላቸው አካላት እና በአገራችን ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን ማስገባት በሚፈልጉ ምዕራባውያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም አገራት በሚገኙ የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች መሆኑን አብራርተዋል።
ኤጀንሲው በየጊዜው ባሕሪውን የሚለዋውጠውን የሳይበር ደህንነት ዘርፍ ታሳቢ ያደረገ አገራዊ ፣ ቀጠናዊ እንዲሁም ዓለምአቀፍ የሳይበር ምህዳሩን ላይ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማጥናት፣ ቀድሞ የመዘጋጀት፣ የማቀድና በጥብቅ ዲሲፕሊን ሥራዎችን በመሥራቱ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሳይበር ጥቃትን የማስጠበቅና የመጠበቅ ቁመናው አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ሹመቴ ገልጸዋል።
“የሳይበር ደህንነት የሁሉም ኃላፊነት ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ተቋማት ሥነ-ምግባር የተላበሱ ሙያተኞችን እንዲኖራቸው በመሥራት፤ የሳይበር ደህንነቱ የተጠበቀ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ ፣ የሚጠቀሙባቸውን ሲስተሞች ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ኦዲት በማስደረግ እና የአሠራር ሥርዓቶችን በአግባቡ በመተግበር የሳይበር ደህንነት ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 24/2014