የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዲያስፖራዎችን ከጀማሪ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር የሚያገናኝ መድረክ በቅርቡ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይ በርካታ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን ይዘው ቀርበዋል። በተለያዩ ዘርፎች የፈጠራ ሥራዎችን የሠሩ ፈጣሪዎችም ሥራዎቻቸውን ይዘው የቀረቡበት ነው ።
ሥራ ፈጣሪዎቹ ከኢንቨስተሮች እና ከተለያዩ አገራት ከመጡ ዲያስፖራዎች ጋርም ተገናኝተዋል። መድረኩ ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ራሳቸውን እና ሥራቸውን የሚያስተዋውቁበት ምቹ እድልም ፈጥሮላቸዋል። በመድረኩ የፈጠራ ሥራ ይዘው ከቀረቡት መካከል “ብሉ ሄልዝ” ኢትዮጵያ የተሰኘ ጀማሪ ድርጅት አንዱ ነው። በድንገተኛ አደጋ ምክንያት በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ጀማሪ ድርጅት ነው ።
ከተመሠረተ አንድ ዓመት ገደማ ሆኖታል። ከብሉ ሄልዝ ኢትዮጵያ መስራቾች አንዱና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቢኒያም አለሙ እንደተናገሩት፤ ብሉ ሄልዝ ጤናን ከቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር እየሠራ ያለ ኩባንያ ነው። ሦስት ዶክተር ጓደኞች፣ ከአንድ የኮምፕዩተር ኢንጂነር ጋር በመሆን ድርጅቱን መስርተው ሥራ እንደጀመሩ ያነሳል። ዶክተር ቢኒያም ለዚህ የፈጠራ ሥራ ያነሳሳቸውን ምክንያት እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ፤ “በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ እያሉ ኢንተርን ሺፕ ወጥተው በድንገተኛ ክፍል አካባቢ ከፍተኛ ችግሮችን ያስተውላሉ።
አንድ ሰው አደጋ አጋጥሞት ሆስፒታል እስኪደርስ ድረስ በጣም ብዙ ጉዳት ይደርስበታል”። ኢንተርንሺፕ ላይ በነበሩበት ወቅት ይህን ችግር መቅረፍ አለብን ብለው እንደተነሱ የተናገሩት ዶክተር ቢኒያም ተመርቀው ከወጡ በኋላ ቤተሰቦቻቸው የመንግሥት ሥራ ተቀጥረው እንዲሠሩ ግፊት ቢያደርጉም እነ ዶክተር ቢኒያም ግን የመንግሥት ሥራ ከመቀጠር ይልቅ ህክምና ከቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን እና ህሙማንን ለመርዳት እንደወሰኑ ያነሳሉ።
የድርጅቱ መስራቾች ከጊዜው ጋር የሚሄድ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህኛው ደግሞ በቀላሉ የስማርት ቀፎ ያላቸው ሰዎች የሞባይል መተግበሪያ በመጠቀም የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እንዲያውቁና ሰዎችን እንዲያግዙ የሚረዳ ነው። ደራሽ የተሰኘ መተግበሪያ በማበልጸግ በአፕልስቶር ማውጣታቸውን ጠቁሟል።
ድንገተኛ አደጋ የደረሰበት ሰው ወደ ሆስፒታል ከመሄዱ በፊት ምን ማድረግ አለበት የሚለውን እንዲረዱ እውቀት የሚያስጨብጥ መተግበሪያ መሆኑን አንስተዋል። ‹‹ጎልደን ሐወር›› ወርቃማ ጊዜ በሕክምና አጠራር አንድ ሰው አደጋ ደርሶበት ከተጎዳበት ቦታ ተነስቶ ሆስፒታል እስከሚደርስበት ያለ ጊዜ (ሰዓት) ነው።
ወርቃማ ጊዜ ሰዓቱ አጠር ማለት የተጎዱ ሰዎች በሕይወት የሚኖሩበት ዕድል ይጨምራል ። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ሁለት ሰዓትና ከዚያ በላይ የተጎዳ ሰው ወደ ሕክምና ቦታ ለማድረስ እንደሚወስድ ገምተዋል። ይህን ችግር በቀላሉ ሊፈታ ይችላል ተብሎ የተሠራ መተግበሪያ ነው።
መተግበሪያውን ሲከፍቱ በኢትዮጵያ ያሉትን የአምቡላንስ ቁጥሮችን ያመጣል ። ዶክተር ቢኒያም ቡድኑ ብዙ ጥናቶችን ማድረጉን ይናገራሉ። አብዛኛው ዜጋ የአምቡላንስ ቁጥር እንደማያውቅ ነው ያብራሩት። መተግበሪያው ላይ የተለያዩ የአምቡላንስ ቁጥሮች ተጭነዋል ። በመሆኑም ማንም ሰው የአምቡላንስ ቁጥርን በቀላሉ ማግኘት ይችላል።
የአምቡላንስ ሰርቪስ እስኪመጣ ደም የሚፈሳቸው፣ የአየር ቱቦ የተዘጋባቸውና ሌሎች ቶሎ መታገዝ ያለባቸው ዜጎችን ለማዳን መተግበሪያ ላይ መመሪያዎች ተቀምጠዋል። መተግበሪያው በጽሑፍና በቪዲዮ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጠት እንዲችሉ የሚያግዝ ነው። አምቡላንስ ከመጣ በኋላ እንዴት ወደ ሕክምና መሄድ እንደሚችል የሚያሳይ ነው።
እንደ ዶክተር ቢኒያም ማብራሪያ፤ ከታካሚዎች ጋር ተያይዞ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ ብዙ ሰዎች ወደሚያውቁት ጤና ተቋም መሄድ ይፈልጋሉ። የሚመርጡት ሆስፒታልተጎጂው ካለበት ቦታ ሩቅ ሊሆን ይችላል ።
ወርቃማ ጊዜን ለመጠቀም ደግሞ በአቅራቢያ ወደሚገኘው ጤና ተቋም መሄድ ግድ ይላል። መተግበሪያው ቅርብ የሆነውን የጤና ተቋም የሚያመላክት ነው። ኪሎ ሜትሩን፣ ስልክ ቁጥሩን ከጎግል ማፕ ጋር በማገናኘት ወደ ሆስፒታል የሚያመራ ነው።
ድንገተኛ አደጋ የደረሰበት ሰው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ከሚያጋጥመው ችግር አንዱ ከዚህ በፊት ተጎጂው ያለበት ሕመም፣ የሚወስደው መድኃኒት አለመታወቅ ነው።
ኪሎ ሜትሩን፣ ስልክ ቁጥሩን ከጎግል ማፕ ጋር በማገናኘት ወደ ሆስፒታል የሚያመራ ነው። ድንገተኛ አደጋ የደረሰበት ሰው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ከሚያጋጥመው ችግር አንዱ ከዚህ በፊት ተጎጂው ያለበት ሕመም፣ የሚወስደው መድኃኒት አለመታወቅ ነው።
መተግበሪያው ከደም ዓይነት ጀምሮ ያለበትን የሕመም ዓይነት መሙያ አለው፣ የአደጋ ጊዜ ተጠሪም እንዲያስገባ የሚያዝ መሆኑን ዶክተር ቢኒያም ይጠቅሳሉ። መተግበሪያው በአሁኑ ወቅት በሦስት ቋንቋዎች(በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ) አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ቋንቋዎችን ለመጨመር እቅድ አላቸው ።
እንደ ዶክተር ቢኒያም ማብራሪያ፤ በቀይ መስቀል ማኅበር አማካይነት 33,000 የሚሆኑ ዜጎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሰለጠኑ አሉ ። ይህ ማለት ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለሚኖርባት አገር በጣም ትንሽ ነው ይላል።
ብሉ ሄልዝ ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ሊፈታ ይችላል ያለውን መፍትሔ ይዞ መምጣቱን ጠቁሟል። በዚህ ረገድ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አሰጣጥ ዙሪያ ሾፌሮችንና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን አሰልጥነዋል። በተጨማሪም ለመምህራንና ለተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ዕርዳታ አሠጣጥ ግንዛቤ ሰጥተዋል።
የአምስት ዓመት ዕቅድ ማውጣታቸውን ያብራሩት ዶክተር ቢኒያም፤ ቢያንስ በአምስት ዓመት ውስጥ እስከ 200 ሺህ ሰዎችን የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና አሰጣጥ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እናደርጋለን ብለው እቅድ መያዛቸውን አንስተዋል።
ከአሥር ዓመት በኋላ ደግሞ የራሳቸው የሆነ የድንገተኛ ሕክምና ሴንተር ለማቋቋም አስበዋል። ለድንገተኛ ሕክምና ተብሎ የተሰራ የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ባለመኖሩ ከምሥራቅ አፍሪካም ለኢትዮጵያም የሚሆን ተቋም ለመሥራት እቅድ መያዛቸውን ነው ያነሱት።
ከዲያስፖራው ጋር እንዲገናኙ የተፈጠረው መድረክ ስራቸውን ለማህበረሰቡ እንዲያሳዩ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። የሰሩት ሥራ ለማህበረሰቡ የሚታይበት እድል መፈጠሩ ትልቅ እድል ነው ይላሉ ።
በዘርፉ እውቀት ያላቸውን የአገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ዲያስፖራዎች እንዲገናኙ ሰፊ እድል ፈጥሮላቸዋል። የእውቀት እና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት መድረክ እንደሚሆንላቸውም ተስፋ አድርገዋል። ሌላው የፈጠራ ሥራ ይዞ የቀረበው ፍሪላንስሲራ የተሰኘ ድርጅት ነው። ፍሪላንስሲራ በትርፍ ጊዜያቸው እውቀታቸውን እና ሙያቸውን ተጠቅመው ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው ስራ መስራት የሚፈልጉትን ሰዎች ከአሰሪዎች ጋር የሚያገናኝ የኦንላይን ፕላትፎርም ነው።
የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቤዛዊት አድማሱ እንደተናገረችው፤ ወጣቶች በተለይም ግራፊክ ዲዛይኒንግ፣ ጽሁፍ፣ ዳታ እና የማሰልጠን ሥራ የሚሰሩ ወጣት ሰራተኞችን አሰሪዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸው ለማስቻል የተፈጠረ ነው።
በፍሪላንስ ስራዎች እና ሰራተኞች መካከል ያለውን የመረጃ እና የአገልግሎት ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ መፍትሄ ነው ። ቀጣሪዎች እና ፍሪላንስ ሰራተኞች አብረው የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታን መፍጠር፣ ለፍሪላንሰሮች ቀላል የሥራ እድልን ማመቻቸት፣ ትክክለኛ ተሰጥኦ ያላቸው የትርፍ ጊዜ ሰራተኞች በትክክለኛው ቦታ እንዲቀጠሩ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር አሰሪዎች ለሚከፍሉት ገንዘብ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም ተቋማት እና አማካሪ ድርጅቶች በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸውን የሰው ኃይል ፍልሰት ለመቀነስ እንደሚረዳ ትናገራለች።
ስራውን ከጀመሩ አንድ ዓመት ሊሞላ ነው ። በአሁኑ ወቅት በትርፍ ጊዜያቸው እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በመጠቀም መስራት የሚፈልጉትን ፍሪላንሰሮች መረጃ እያሰባሰቡ ነው ። ሰሞኑን የተካሄደው ዲያስፖራዎችን ከጀማሪ ሥራ ፈጣዎች ጋር የሚያገናኝ መድረክ የአይቲ ቴክኖሎጂ ሰዎች ጋር እንዲገናኙ እድል ፈጥሮላቸዋል።
በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰማሩ ዲያስፖራዎች ጋር እንዲነጋገሩ እና በቀጣይ በጋራ ለመስራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ዘርፍ ከተሰማሩ ሰዎች ጋር የዘርፉ ተግዳሮቶች እና እድሎች ዙሪያ እንዲጋሩ ይረዳል።
የፍሪላንሲንግ እና አውትሶርሲንግ ስራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ነው። በመንግሥት በኩል ሊደረጉ የሚገቡ ድጋፎች ዙሪያም ከመንግሥት አካላት ጋር ለመነጋገር እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል። ትክክለኛ መንገድ ተከትለው ስራቸውን በጥራት እንዲሰሩ ፣ በፍጥነት በሚፈልጉት ጥራት እንዲያድጉ ብዙ የግንኙነት መረቦችን እንዲዘረጉ አግዟቸዋል። እንደ ሥራአስኪያጇ ማብራሪያ፤ በመድረኩ ላይ ፍሪላንሰሮችን ለማሰልጠን ፈቃደኛ የሆኑ ዲያስፖራዎች ተገናኝተዋል።
በውጪው ዓለም እንዲህ አይነት ቢዝነስ በጣም የተለመደ በመሆኑ መድረኩ ዲያስፖራው ያለውን እውቀትና ልምድ የሚያካፍልበት ይሆናል። በቀጣይም መሰል ስራዎችን ለመቀጠል እድል ይፈጥራል። በመድረኩ የፈጠራ ሥራ ይዞ የቀረበው ሌላኛው የፈጠራ ውጤት ባለቤት ሀብታሙ አሰፋ ይባላል።
ሀብታሙ ከሌላ ጓደኛው ጋር በመሆን በየደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታዊ መረጃዎችን በተንቀሳቃሽ ስልክ ለማድረስ የሚያግዝ «ተማሪ ቤት» የተሰኘ መተግበሪያ ሰርተዋል። የተማሪ ቤት መስራችና ሥራ አስኪያጅም ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ጥራት እንዲያሽቆለቁል ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የብቁ መምህራን የመፃህፍትና የቤተ-መፃህፍት እጥረት እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎች ጥበት መሆናቸውን የሚያነሳው ወጣት ሀብታሙ ይህ ችግር ለረጅም ጊዜ የቆየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ችግር ሆኖ ቀጥሏል።
ከጓደኛው ጋር በመሆን ይህንን የተማሪዎች ተግዳሮት በመጠኑ ለመቅረፍ የሚያግዝ መተግበሪያ እንደሰሩ ይናገራል ። መተግበሪያው የትምህርት መረጃዎችን በየደረጃው ላሉ ተማሪዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያደርስ ነው። ይህንን መተግበሪያ ለመስራት ምክንያት የሆነው በትምህርት ቤቶች በተጨባጭ የተመለከተው ችግር መሆኑንም ሀብታሙ ያብራራል።
በተለያዩ ወቅቶች ይመለከቱት የነበረው የትምህርት አሰጣጥ፣ የመጽሃፍት ይዘት እና ትምህርትን ለዕውቀት ሳይሆን ለፈተና ብቻ አድርጎ የማየት ችግር መተግበሪያውን ለመስራት እንዳነሳሳቸው ይናገራል። እንደ ሀብታሙ ገለጻ፤ መተግበሪያው የተማሪዎች የመማር ፍላጎት እንዲጨምር አድርጓል።
በበይነ-መረብ ግንኙነት እንዲሰራ ተደርጎ የተሰራው ይህ መተግበሪያ፤ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ በአማርኛ ፣በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች ትምህርታዊ መረጃዎችን በፅሁፍ በድምፅና በምስል ለተማሪዎች የሚያደርስ ሲሆን ለወደፊቱም ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ አላቸው።
መተግበሪያው በኢትዮጵያ የመጽሐፍት እና የቤተመጻህፍት እጥረትን ለማቃለል ጥሩ አማራጭ በመሆን ያገለግላል። ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን በአነስተኛ ክፍያ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ አብራርተዋል። በቅርቡ የተካሄደው መድረኩ የዲያስፖራዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የመንግሥት አካላትን ትኩረት እንዲያገኙ እንዳስቻለ ይጠቅሳል። በቀጣይ አብሮ ለመስራት ፍላጎት ያሳዩ ዲያስፖራዎች መኖራቸውንም ተናግሯል።
ከተለያዩ አገራት የመጡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተመለከቱት የቴክኖሎጂ ስራዎች መደሰታቸውን በመግለጽ ከአንዳንድ ሥራ ፈጣሪዎች ጋር አብረው ለመስራት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት እና ስራቸው እንዲቀጥል ማድረግ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጀማሪ ድርጅቶችና ሥራ ፈጣሪዎች በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችና ዲያስፖራዎች እውቀትና ክህሎት ሲታከልበት እንደ አገር በዘርፉ ትልቅ እምርታ ለማስመዝገብ ያግዛል ሲሉ አበረታተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥር 17/2014