በአገሪቱ የተከሰተው ችግር የብዙዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ ከግለሰብ እስከ መንግሥት ለዓመታት የተለፋባቸውን ንብረቶች ለውድመት ዳርጓል።
በሌላ በኩል ዛሬም ድረስ አሸባሪው ሕወሓት የጦርነት ጉሰማውን ባለማቆሙ በመንግሥትም ሆነ በግለሰቦች በኩል በሙሉ ልብ ወደልማት ለመግባት ሁኔታውን አስቻጋሪ አድርጎታል። ይህም ሆኖ ፋታ የማይሰጡ ነገን፣ የማይጠብቁ እንደ የጤና ተቋማትና ሌሎች የሕዝብ መገልገያዎች በፍጥነት ወደነበሩበት መመለስ እንዳለባቸው ይታመናል።
በዚህ ረገድ የመንግሥት ቁርጠኝነት ለጥያቄ የማይቀርብ ቢሆንም የደረሰውን ውድመት በሙሉ በመንግሥት ብቻ ይሸፈን ማለት ከአቅም በላይ ከመሆኑ ባሻገር ረጅም ጊዜን የሚፈልግ ይሆናል። በመሆኑም ከግለሰብ እስከ የግል ተቋማት የበጎ አድርጎት ማህበራትን ጨምሮ እንደየደረጃውና እንደየአቅማቸው በመሳተፍ ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄን መፈለግ ወቅቱ የሚያቀርበው ጥያቄ ነው። በዚህ ረገድ ይህንን በመረዳት «የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ» ይህንን አገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት በማቀድ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
እኛም ለዛሬ የአገርኛ አምዳችን የጥምረቱን ከፍተኛ ኃላፊዎች በማነጋገር የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል። የድርጅቱ ፕሬዚዳንትና የቲያትር ጥበባት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው «የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ» በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚከተለው አብራርተዋል።
«የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ» ሦስት መቶ ስልሳ አራት አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጋራ ያቋቋሙት ጥምረት ነው። ጥምረቱ የተቋቋመበትም ዋነኛ አላማ በአገሪቱ በርካታ ችግሮች ያሉ በመሆናቸው እነሱን በተናጠል ለመፍታት ከመሞከር በህብረት መንቀሳቀሱ ፋይዳው የጎላ ነው ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው። እንደ መሪ ቃልም «ስለኢትዮጵያ ፍቅር፣ አንድነት፣ ሰላምና ወንድማማችነትን ማጎልበት» የሚል ነው። ይህም ሆኖ ጥምረቱ መሠረቱን በውጭ አገር ያደረገ በጎ አድራጎት ተቋም ስር የማይካተት ሲሆን ሁሉም አባላት አገር በቀል ናቸው።
ጥምረቱ ሙሉ ለሙሉ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት እንዲሁም ሃይማኖት ገለልተኛና ነፃ ሆኖ የሚንቀሳቀስም ነው። ይህም ሆኖ በሁሉም አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይመለከተኛል በሚል ስሜት ለግለሰቦች ድጋፍ ከማድረግ እስከ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በመንቀሳቀስ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ እየሠራ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ከተሠሩት ሥራዎች መካከልም በዋነኝነት በእገሪቱ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ከፍተኛ የደም እጥረት ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል። ይህንን የደም እጥረት ችግር ለመቅረፍም ጥምረቱ ከብሔራዊ ደም ባንክ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴሌ ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች አካላትንም በማስተባበር የስምምነት ሰነድ በመፈራረምና የሚዞር ዋንጫ በማዘጋጀት ደም የማሰባሰብ ሥራ ሠርቷል።
በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእቅድ ደረጃ አምስት ሺ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ አቅዶ ከእጥፍ በላይ ደም አሰባስቦ ጉዳት ወደ ደረሰባቸውና ከፍተኛ የደም እጥረት ወደ አጋጠማቸው አካባቢዎች ማድረስ ተችሏል። ይህ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በአሁኑ ወቅትም በመካሄድ ላይ ሲሆን በቀጣይም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እስኪቀረፍ
ድረስ በሁሉም ክልሎች የሚከናወን ይሆናል። በተጨማሪ ጥምረቱ ከኢትዮ ቴሌኮም፤ ዩኒቲ ፎር ኢትዮጵያና ሌሎች ጋር በትብብር በሸራተን አዲስ ተከታታይነት የሚኖረው ልዩ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።
መርሃ ግብሩ የተጀመረው በሸራተን አዲስ በተካሄደውና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት የእራት ግብዣና የገቢ ማሰባሰቢያ በማካሄድ ነው።
በተከታታይነትም የትኬት ሽያጭ፤ ከባንኮች ጋር በተደረገ ስምምነት የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍና ቴሌቶን የሚካሄድ ሲሆን ከአርባ እስከ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከፕሮግራሙ የሚሰበሰበው ገቢም በጦርነቱ ለተጎዱት በአፋርና አማራ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ለቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ለማድረግ፤ እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ የጤና ተቋማትንና ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያገለግል ይሆናል።
እንደ እቅድም በእነዚህ አካባቢዎች ለተፈናቀሉና ለችግር ለተዳረጉ ዜጎች ለቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ ለማድረግ፤ እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ ሃያ የጤና ተቋማትና ሃያ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት መታሰቡን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም በአሸባሪው ሕወሓት በሰሜን እዝ ላይ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የመከላከያ ሠራዊቱን ሞራል ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ግንባር ድረስ በመዝመት ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይም የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን አመላክተዋል። ከኢትዮ ቴሌ ኮም ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴሌ ብር አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
ፕሬዚዳንቱ ጨምረው እንደተናገሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚያደርገው የበጎ ተግባር አገልግሎት በተጨማሪ በርካታ የአገርን ገጽታ የሚገነቡና የውጭ ግንኙነትን የሚያስተካክሉ፤ እንዲህም በአገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ግንባታና የሕዝብ ተሳትፎን የሚያጠናክሩ ተግባራትንም ሲያከናውን ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ክፍተት የመሸፈን ሥራ አንዱ ነው።
በዚህም ሕዝቡ ምን ይጠይቃል? ምንስ ይፈልጋል? ምን ምን ቀዳሚ ችግሮችስ አሉበት? የሚለውን በሃያ መስኮች ማለትም በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትህ፣ በልማት ወዘተ በመለየት የሕዝብ ጥያቄን በመሰብሰብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲደርስ ማድረግ ችሏል።
በቀረበውም የሕዝብ ጥያቄና አስተያየት ላይ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የመንግሥት፤ የሲቪክ ማህበራትና የሕዝቡ ሚና ምን መሆን አለበት፤ ችግሮችንስ በጋራ እንዴት መፍታት እንችላለን በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት በማካሄድ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀርቡ ማድረግ ተችሏል።
በቅርብ ጊዜም በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የአሜሪካውያንና የአንዳንድ አውሮፓ አገራት የፈጠሩትን ተጽእኖ ለማስነሳት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
አንዳንድ ሚዲያዎች ባራገቡት ሀሰተኛ መረጃ በኢትዮጵያ በመከላከያ ሠራዊቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ እንደሆነ በማስመሰል ኢትዮጵያን ለመክሰስና በጫና ለማቆየት ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይህንን ዘመቻ ለመቀልበስም ታኅሣሥ 16 ቀን ከአራት ኪሎ ወደ አሜሪካ ኤምባሲና በተመሳሳይ ከአራት ኪሎ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ጥምረቱ አስተባብሯል። እንደገለልተኛ ኢትዮጵያዊ አካልም ሰላማዊ ሰልፉ ከመከናወኑ በፊት ለኤምባሲዎች በስድስት ቋንቋዎች ሰፊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን ደብዳቤ በመጻፍም እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ጥምረቱ የነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተመንግሥት ዘመቻም አንድ አካል ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኤምባሲዎች በአገሪቱ ስላለው ሁኔታ የአሸባሪው ቡድን ከሚያሰራጨው የሀሰት ዜና ተላቀው ትክክለኛውንና የወቅቱን ሁኔታ እንዲረዱ ተደርጓል።
በተጨማሪም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለጸጥታው ምክር ቤት፣ አፍሪካ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚንቀሳቀሱ አስር ተቋማት በተመሳሰይ በደብዳቤ ስለኢትዮጵያ እውነታውን እንዲረዱ ተደርጓል።
ከዚህም ውስጥ ለተባበሩት መንግሥታት የተላከው ዝርዝር ሁኔታዎችን ያካተተ ደብዳቤ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ጥሩ ግንዛቤ ለመፍጠር አስችሏል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። የማህበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ብዙወርቅ ፋንታዬ በበኩላቸው ጥምረቱ በህብረት የሚሠራቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሦስት መቶ ስልሳ አራቱም አባል ድርጅቶች በተመሳሳይ ለወገን በመድረስና በአገር መልካም ገጽታ ግንባታ ላይ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ዋና ጸሐፊው በዚህ ረገድ የተሠሩና በመሠራት ላይ ያሉ ሥራዎችንም ሲያብራሩ፤ እንደ ጥምረቱም ሆነ እንደእያንዳንዱ ድርጅት የሚሠሩት ሥራዎች በመላው አገሪቱ በተፈጠረው ችግር የጠፉትን ነገሮች ቢቻል በተሻለ ካልሆነም ወደ ነበሩበት ለመመለስ ነው።
በዚህም በጥምረቱ ስብስብ ብቻ ሰላሳ የሚደርሱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እቅድ ተይዟል። «የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ» በመላው አገሪቱ የሚገኝ ነው።
ይህም በቀላሉ ባለው መዋቅር ሀብት የማሰባሰቡንና ሕዝብ የማስተባበሩን ሥራ ለመከወን የሚያስችለው ሲሆን በተመሳሳይ የተሰበሰበውንም ሀብት ወደሚፈለገው ቦታ ለማዳረስ የሚረዳ ይሆናል።
በተጨማሪ እነዚህ ድርጅቶች እንደ ግል በጤና፤ በትምህርት በኪነ ጥበብና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው። በመሆኑም ጥምረቱ ምንም ዓይነት የሞያም ሆነ የምሁር እጥረት የሚገጥመው አይሆንም።
በአሁኑ ወቅትም ጥምረቱ ከሂሳብ ሥራ ባለሙያ ጀምሮ የሚያስፈልገውን ሁሉ እያሠራ ያለው ከራሱ፣ ከማህበራቱ በሚወጡ ባለሙያዎች ነው። ለምሳሌ እኔ የምመራው «ጌልጌላ ኢንተግሬትድ ኮሚዩኒቲ ዲቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን» እስካሁን ሁለት መቶ አርባ ስምንት ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ አካባቢዎች ያስገነባ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ላይ ይገኛል። እንዲሁም ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች እየተገበረው ያለው «ስፒድ ስኩል መርሃ ግብር» አሁን በአገሪቱ በትምህርት መስክ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ አንዱ ተስፋ የሚጣልበት ነው።
ይህ መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም በሶማሊያና ኦሮሚያ ተፈጥሮ በነበረው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች ላይ ተተግብሮ 18ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። «ስፒድ ስኩል መርሃ ግብር» ተፈናቅለው በመጠለያ ያሉና በወደሙ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ ሕፃናትን በአንድ አመት አራተኛ ክፍል እንዲደርሱ የሚያበቃ ይሆናል።
በዚህ አካሄድ ሕፃናቱ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች አራተኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ ከተደረገ በኋላ ለተከታታይ ሦሰት አመታት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው በመደበኛ ትምህርት ከመጡት ተማሪዎች እኩል እንዲሆኑ ይደረጋል።
በመሆኑም ይህ ልምድ አሁን በደረሰው ጉዳት ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎችንና የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ ተቋሙ ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ በብቃት ለመከወን የሚያስችለው ይሆናል።
ጥምረቱ በቀጣይም በተነሳለት አላማ መሠረት በመላው አገሪቱ ሰላም ፍቅርና ወንድማማችነት እስኪሰፍን የጀመረውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥር 13/2014