
የትግራይ ሕዝብ በአሸባሪው ሕወሓት ሴራና አምባገነናዊ አገዛዝ የተነሳ ልጆቹን ለጦርነት እየገበረ ይገኛል። ከዚህም አልፎ ክልሉ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም ከፍተኛ ኪሳራን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ለመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ይህንን ማስቆም ሳይችል ቀርቶ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ይነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ለበርካታ ዓመታት የተሰራበት የስነልቦና ጫና ከሕወሓት አፈና እንዳይላቀቅ አድርጎታል የሚሉ አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የትግራይ ጉዳይ ያገባናል ብለው የሚሠሩ የፖለቲካ ኃይሎች ሚና የላቀ ነው፡፡
ከነዚህ ኃይሎች ውስጥ አንዱ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፡፡ እኛም ለዛሬው የተጠየቅ አምዳችን የትግራይን ሕዝብ ከእጅ አዙር የሕወሓት ቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ምን መደረግ አለበት? ትግራይን መልሶ ለመገንባት ምን መደረግ አለበት ? በሚሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌን አነጋገረን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- የሕወሓት የሽብር ቡድን በአማራ ክልልም ሆነ በአፋር ክልል ወረራ በማካሔድ ትልቅ ጥፋት አድርሷል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሙሉብርሃን፡- ቡድኑ ለሕዝብ ታገልኩ ይላል እንጂ፤ ፀረ ሕዝብ ነው፡፡ ፀረ ሕዝብ በመሆኑ ሕዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት ውድመት አድርሷል፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ቢያስብ ኖሮ ለአማራም ሆነ ለአፋር ሕዝብ ያስብ ነበር፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ለሕዝብ የማያስብ በመሆኑ እንዲህ አይነት አረመኔያዊ ድርጊት ፈፅሟል፡፡
ሌላው ቡድኑ ይህንን ድርጊት የፈፀመበት ምክንያት ያሰበውን እኩይ ዓላማ ለማሳካት ሲል ነው የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን ካስተዳደረ በኋላ ተገፍቶ ሲሔድ፤ ኢትዮጵያን የመገንጠል አጀንዳን በሰፊው ይዟል፡፡ ይህን ለማሳካት የትግራይ ሕዝብ ከአጎራባች ክልሎች እና ከሌላውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ማጣላት እና ማጋጨት ነበረበት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ጦርነት ውስጥ የገባው የትግራይ ሕዝብን ለማላተም ጭምር ነው።
የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት ሕዝቡን ለጦርነት ዳርገዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከአማራም ሆነ ከአፋር ሕዝቦች ጋር ለዘመናት ኖሯል፡፡ የሚያጋጨው ምንም ምክንያት የለውም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ከአማራ ሕዝብ እና ከአፋር ሕዝብ የተለየ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ጦርነት ውስጥ የተገባው በትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን በአሸባሪ ቡድኑ ፍላጎት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንደገለፁት የሽብር ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ የማይወደድ ተግባር እየፈፀመ ከሆነ፤ የሕወሓት የሽብር ቡድን ለምን አልተወገዘም? ሕዝቡን እና የሽብር ቡድኑን መነጠል ይቻላል ? በምን ዓይነት መንገድ ይህንን ማድረግ ይቻላል?
አቶ ሙሉብርሃን፡– ይሔ በጣም ብዙ ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ ለአርባ እና ለሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጀክት ላይ በደንብ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ሕወሓት የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀንደኛ ተዋናይ በመሆን ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጀክት ላይ ለዓመታት ሠርቷል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ መሠረት ሆኖ እያለ ኢትዮጵያዊነቱ እንዲደበዝዝ ከዋናው ኢትዮጵያዊ ማንነቱ ወጥቶ ትግራዋይ የሆነ ማንነት ፈጥሮ ይህንን አስተሳሰብ እንዲሸከም አድርጓል።
ይህ የሽብር ቡድን አፋኝ እና አምባገነን ነው። የተለያዩ ስልቶች አሉት፡፡ ሕዝቡ በአፈና እና በፍርሃት ቀንበር ውስጥ ነው፡፡ የሕወሓት አሰላለፍ እነርሱ ራሳቸው እንደሚሉት አብዮታዊ ነው፡፡ ወዳጅ እና ጠላት የሚል ፅንፍ የወጣ አሰላለፍን ይከተላል፡፡ የእነርሱን አስተሳሰብ የሚቀበል፣ የሚያስፈፅም እና ከእነርሱ ጋር የሚሰለፍ ከሆነ ወዳጅ ነው ይሉታል። በተቃራኒው የሚቆም ደግሞ ይሔ አፍራሽ ነው ለሕዝቦች አንድነት አይጠቅምም ይሉታል፡፡ ጠላት ብለው ካስቀመጡት ደግሞ ጠላት የተባለውን ሁሉ ማሳደድ፣ ማሰር፣ መግደል እና ማሰቃየትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።
በዚህ ምክንያት በፍርሃት የተሸበበ በርካታ የትግራይ ሕዝብ አለ። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን ቢቃወም ራሱን የሚከላከልበት የተለየ አማራጭ እና አደረጃጀት የለውም፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰን ካየን ሕወሓት ትግራይ ውስጥ ከሕወሓት ውጪ ሌላ ፓርቲ መኖር የለበትም ብሎ የደመደመ ፓርቲ ነው። በጣም እጅግ የሚያሳፍር ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን ከአንድ ሃሳብ ውጪ ሌላ ሀሳብ ማስተናገድ አይቻልም የሚል አቋም ነበራቸው፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ ውስጥ ድህነት አለ፡፡ የትግራይ ሕዝብ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖር ነው። ሁልግዜም ስለሚበላው እና ስለሚጠጣው የሚጨነቅ ሕዝብ ነው፡፡ በተጨማሪ በተደጋጋሚ ጦርነት ያጋጥመዋል፡፡ ይህ ኃይል ለራሱ ጥቅም ሲል ሕዝቡን በጦርነት ውስጥ ሲከት ኖሯል። ለ17 ዓመታት ከደርግ ጋር ጦርነት ውስጥ ሆኖ ሲዋጋ ከቆየም በኋላ ስልጣን ላይ ቢወጣም የትግራይ ሕዝብ ከጦርነት ማረፍ አልቻለም። መልሶ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም የሚዘነጋ አይደለም። አሁንም በድጋሚ ሕዝቡን ጦርነት ውስጥ እየከተተ ሶስተኛ ትውልድ እየጨረሰ ነው። ይህ ሁሉ ተደምሮ የትግራይ ሕዝብ በከባድ የሥነልቦና ጫና ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይን ሕዝብ የጎዳውን ሕወሓትን ከሕዝቡ ለመነጠል የተቀናጀ ሥራ መሠራት አለበት፡፡
የሕወሓት አጀንዳ እና አስተሳሰብን ሕዝቡ በቅጡ እንዲረዳ መሠራት አለበት፤ ይሔ አልሆነም፡፡ የትግራይ ሕዝብ የተለየ አስተሳሰብ እንዳይኖረው የተለየ አማራጭ እንዳያይ ሕወሓት በራሱ ቁጥጥር ውስጥ አድርጎ በሩን ዘግቶ ስለቆየ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል። የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ መሠረት እንደሆነ፤ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር እና ለኢትዮጵያም ብዙ ዋጋ እንደከፈለ፤ ኢትዮጵያ አገሩ እንደሆነች የማስረዳት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ሕወሓት ያመጣው ትርክት ውሸት እንደሆነ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ በጣም የሚገርመው የእነርሱ ካድሬዎች እንደመምህር ገብረኪዳን አይነቶቹ ትግራይ ኢትዮጵያ ሆና አታውቅም ብለው ፅፈዋል፡፡ አክሱማውያን ኢትዮጵያውያን አይደሉም የሚል ክህደት ፈፅመዋል። ስብሃት ነጋ የትግራይ ሕዝብ ከ40 እና ከ50 ዓመት በፊት ምንም ዓይነት ታሪክ እንዳልነበረው በአደባባይ ክዷል፡፡ ስለዚህ ይህንን የማስተካከል ሥራ በቅጡ መሠራት አለበት፡፡
ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ነው። የትግራይ ሕዝብ ዋጋ እንዲከፍል እና እንዲጎብጥ ያደረገው ይህ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ እንዲጠፋ ከተፈለገ የትግራይ ሕዝብ መታገል መቻል አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ ታግሎ እንዲያስወግደው የሕወሓት ማንነትን ገልፆ በማስረዳት የትግራይን ሕዝብ ልናነቃው ይገባል፡፡ እነርሱ የትግራይ ሕዝብ ብዙ ጠላት እንዳለው ነግረውታል፡፡ አማራ ብቻ ሳይሆን መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ የእርሱ ጠላት እንደሆነ እንዲታሰብ ሰብኳል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የሚሆንበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓትን አምርሮ ይጠላል። ምክንያቱም ሕወሓት የተጠላው ለአገር ጥቅም ስለማይቆም፣ አፋኝ፣ ከፋፋይ፣ ፅንፈኛ እና ብሔርተኛ ስለሆነ ነው፡፡
የትግራይ ሕዝብ የሚጠላ አይደለም፡፡ ደሃ ሕዝብ ነው፡፡ እያስመታን፣ እንድንጠላ እያስደረገን፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ጥያቄ መልክት ውስጥ እያስገባብን ያለውን ይህንን ኃይል በደንብ አውቀነው መታገል አለብን። ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ እና ይሔንን ኃይል ነጥሎ መታገል አለበት፡፡ ያኔ ሕወሓት ይሸነፋል፤ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን የማይበጀው አስተሳሰቡ ይጠፋል፤ የኢትዮጵያውያን አብሮነታችን ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደጠቀሱት የትግራይ ሕዝብ የሚበላው እና የሚጠጣው ያጣ ሕዝብ ነው፡፡ በዛ ላይ አፈናውም አለ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ልጆቹን አጠቃላይ ትውልድን እያጣ ለምን ሕወሓትን በቃ ማለት አልቻለም? ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ሙሉብርሃን፡– ሕወሓት ሴረኛ ድርጅት ነው። ዋናው ሴራው ራሱን ከሕዝብ ጋር ያቆራኛል፡፡ ሕወሓት እና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው የሚልበት ምክንያት ተራ አይደለም፡፡ ራሱን በሕዝብ ውስጥ የደበቀው ለይቶ ለመምታት የሚያስቸግር መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። ዘላለሙን የትግራይን ሕዝብ አጥር አድርጎ መሐል ላይ ለመቀመጥ ዓላማ አለው፡፡ በርካታ ድራማዎችን ሠርቷል።
በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ተፈፀመ፤ ሊያጠፉን ነው የሚል የውሸት ወሬ በማስወራት ሕዝቡን ብዥታ ውስጥ ጨምሮታል፡፡ እንደገና እርሱም በእያንዳንዱ ነገር ላይ ትግራዋይን ያጠቃል፡፡ በአንድ በራሱ ኃይል ትግራዋይን ካስመታ በኋላ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ልታልቅ ነው፤ በማንነትህ ልትጠቃ ነው›› ብሎ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ይነዛል፡፡ ይህ የተለመደ ስልቱ ነው። ነገር ግን በተቃራኒው ይህንን ሊመክት የሚችል ሥራ በደንብ አልተሠራም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ሕወሓት እንዲጠፋ ካስፈለገ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት በተለየ መልክ የሚስተናገድበት ዓውድ ሊኖር ይገባል፡፡ ለምሳሌ ከእስር ጋር ተያይዞ ሁሉንም ትግራዋይ በማሠር ሕወሓትን ማጥፋት አይቻልም። ሕወሓትን ማጥፋት የሚቻለው የትግራይን ሕዝብ በማንቃት እና የመኖር ዋስትናውን በማረጋገጥ፤ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን በእኩልነት እንደሚኖር በማሳየት ነው፡፡
ትግራዋይ አገር አፍራሽ ከሆነ ቡድን ጋር እንዳ ይገናኝ እና ከዛ ውጪ ከሆነ ግን እንደማይመለከተው በማሳወቅ በኩል መሠራት መቻል አለበት፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ አልሠራም፡፡ ይህ ባለመሠራቱ ሕወሓት ‹‹ይኸው ንግድ ፈቃድህ ይሰረዝብሃል ፤ እስር ቤት ትገባለህ፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ያንተ አይደለችም፡፡›› በሚል ወደ ራሱ የመውሰድ ሥራ ይሠራል፡፡ ስለዚህ መንግሥት መሥራት አለበት፡፡ ወንጀለኞች መጠየቅ እና መያዝ አለባቸው። ከአገር በላይ ስለሌለ ከሁሉም አገር እና ሕዝብ ስለሚበልጥ በተለይ ከአሸባሪው ጋር ግንኙነት ያላቸው ያለምንም ምሕረት እርምጃ መወሰድ አለበት። ንፁሓኑ ግን የተሻለ እንክብካቤ በማድረግ ሕወሓት ያልሰጠውን ይህ መንግሥት የተለየ ነገር ማቅረብ መቻል አለበት፡፡
የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን እያጣ በጉዳት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ሕወሓት እየተከተለ ያለው መንገድ ኪሳራ ነው፡፡ መስዋዕት ከመሆን ውጪ ሌላ የሚሆነው ነገር የለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለህ ምን አገኘህ ቢባል ይሄን አገኘሁ የሚለው ነገር የለም፡፡ ይህ እንዳይሆን ያደረገው እና ነገሮችን ያወሳሰበው ሕወሓት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም መንግሥት በትኩረት ከሠራ የትግራይ ሕዝብ ብዥታው ከጠፋለት ሕወሓትን ይታገለዋል፡፡ በዛን ጊዜ ሕወሓት ይጠፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሕወሓት በኩል በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ቁጥር ቀላል አይደለም። እነኚህ ሁሉ የተሰለፉት ሳያምኑበት በግድ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሙሉብርሃን፡– ሕወሓት በግድ ስለማሰለፉ ምንም ዓይነት ጥርጥር የለም፡፡ ነገር ግን የተደናበረም አለ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሊጠፋ ነው፣ መክትለት፣ ጋሻ ሁንለት እያሉት እውነት መስሎት የተሰለፈ በርካታ ነው፡፡ የተሰለፈው አካል የትግራይ ሕዝብን ለማዳን ሳይሆን አሸባሪው ቡድንን ለማዳን መሆኑን አያውቅም። የትግራይ ሕዝብን ለማዳን እኮ ለበርካታ ዓመታት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መክቷል፡፡ አብሮ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መላው ኢትዮጵያ አብሮ ከትግራዋይ ጋር ተቀብሯል፡፡ የትግራይ ሕዝብን ለማዳን ማንም ይመክታል፤ ሕወሓትን ለማዳን ግን ማንም አይመክትም፡፡ ስለዚህ እውነት መስሎት የተደናበረ አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን በደንብ ማወቅ እና ለትግራዋይ ማሳወቅ ይገባል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ነገም የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ የሕዝብ ጠላት የለም፡፡ ሕወሓት ራሱ የፈጠራቸው ጠላቶች አሉ፡፡ እነዚህን በሚመለከት የትግራይ ሕዝብ አንተን አይመለከትህም በሚል ሰፋፊ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ በስፋት አልተሠራም፡፡
ሕወሓትን እንዴት ማጥፋት ይቻላል የሚለው ላይ በደንብ አልተሠራም፡፡ መንግሥት ከዚህ በኋላ ይሠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወደ ኋላ ሕወሓት የበለጠ ዕድሜ እንዲያገኝ እና ነገሮች የበለጠ እየተወሳሰቡ እንዲሄዱ በርካታ ግብዓቶች ሲያገኝ ነበር፡፡ ይህም ከታረመ ሕወሓት የመላው ኢትዮጵያውያን ጠላት ነው፡፡ በተለይ የትግራይ ደግሞ ጠላት ነው፡፡ ምክንያቱም የትግራይን ሁሉንም ነገር በልቷል፡፡ ሶስት ትውልድ አስጨርሷል፡፡ ሕወሓት እስከ ዛሬ የቆየው የትግራይ ሕዝብ ወደ ውጪ እንዳያይ በመደረጉ ነው፡፡
የኛ ፓርቲ ይህንን በሚመለከት በስፋት እየሠራ ነው። እኛ ጠላት ሕዝብ የለንም፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች፡፡ የምትፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለ፡፡ ይህ እንዲሆን በጋራ እየታገልን ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ ተለይቶ የሚጠላበት ምክንያት እንደሌለ በተለያየ አጋጣሚ እየገለፅን እየታገልን ነው፤ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ይህ ግን የእኛ ሥራ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትክክል ነዎት! የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን ታግሎ እንዲያጠፋው የመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በትግራይ ዙሪያ እናንተን ጨምሮ ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽብር ቡድኑን ለመታገል ሕዝቡም እንዲታገለው በማድረግ ላይ ሚናችሁ ምን ያህል ነው?
አቶ ሙሉብርሃን፡- ትክክል ነው መጀመሪያ ከጠየቅሽኝ ጥያቄ ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ ሕወሓት ከራሱ ውጪ ሌላ ሃሳብ እና ፓርቲ እንዳይገባ ዘግቶ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ የረባ ፓርቲ አልነበረም። ራሱ የፈጠራቸው ፓርቲዎች ነበሩ፤ እነርሱም ራሳቸው ከስመዋል፡፡ አንድ የነበረው አረናም በብዙ መልኩ ተዳክሟል፡፡ አሁን ያለው በተሻለ መልኩ የሚንቀሳቀሰው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ነው፡፡ ትዴፓ የተቻለውን አድርጓል፤ አሁንም የተቻለውን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ትዴፓ ሕዝባዊ ነው፡፡ ትዴፓ በዋናነት መሠራት አለበት ብሎ የሚያምነውም ሕዝብን ማደራጀት እና ማንቃት ላይ ነው፡፡ በተቻለው አቅም በተገኘ ዕድል የትግራይ ሕዝብ የሕወሓትን አስተሳሰብ በቅጡ እንዲረዳ፣ በቡድኑ አስተሳሰብ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ጥቅምም ሆነ ሠላም እንደማይረጋገጥ እየተናገረ እየታገለ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ከውስጥም ከውጪም ትዴፓ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም የትግራይ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት የሆነው የሽብር ቡድን እስኪወገድ እና እርሱ የፈጠራቸው ትርክቶች እና ችግሮች እስኪፈቱ እና የትግራይ ሕዝብ ወደ መደበኛው ኢትዮጵያዊነት ተመልሶ የኢትዮጵያ እንብርት እስኪሆን ድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት አሸባሪውን ሕወሓት ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደምስሶ ለማጥፋት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ከዛ ደግሞ አንሰራርቶ ድጋሚ ይሔን የሚያክል ጥፋት ለማድረስ ዕድል የሰጠው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው በሚል አስተያየት ይሠጣል፡፡ አሁን ለደረሰው ጥፋት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ተያይዞ ያለውን ግንኙነት በሚመለከት ይገለፃል፡፡ እርሶ ምን ይላሉ? በተለይ ያልተሠሩ ሥራዎችን በሚመለከት ሃሳብዎ ምንድን ነው ?
አቶ ሙሉብርሃን፡– ይህንን በሚመለከት በፊትም ብለነው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ሕወሓት ጦርነቱን ከለኮሰው በኋላ የአገር መከላከያ ሠራዊቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መጨረስ ችሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕወሓት ከተሸነፈ በኋላ ከላይ የገለፅኳቸው ሥራዎች መሠራት ነበረባቸው። ነገር ግን አልተሠሩም ነበር፡፡ ለምሳሌ ሕወሓት መቀሌን ለቆ ማሊያውን ቀይሮ የትግራይ ገጠር ውስጥ ሲደበቅ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር መሥራት ከነበረበት ሥራዎች መካከል ሕወሓትን ከሕዝቡ ጉያ አውጥቶ ማንነቱን የማስረዳት ሥራ መሠራት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ይህ ሥራ አልተሠራም። በሕወሓት በ17 ዓመት የትግል ጊዜም ከገጠር ወደ ከተማ ገብቶ ሲጠቀምበት የነበረውን አደረጃጀት ያላፈረሰው በመሆኑ አደረጃጀቱን እንዳለ ተጠቅሞበት እንደገና ወደ መሐል መመለስ ችሏል የሚል ግምገማ ፓርቲያችን አለው፡፡
ስለዚህ መንግሥት አንደኛ ሕወሓትን ማፍረስ ነበረበት አላፈረሰም፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም የገጠሩን አደረጃጀት ማፍረስ ነበረበት፣ ነገር ግን ያም አልፈረሰም። የሕወሓት ካድሬ በፕሮፖጋንዳው እርሱ እንዳለ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የሕወሓት መሠረቶችን ሕወሓት ቀጥሎባቸዋል፡፡ በዛ ውስጥ ሰርጎ ገባ፡፡ ለውጡን ሲደግፉ እና ሕወሓትን ሲታገሉ የነበሩ ሰዎች እንዲመቱ አደረገ፡፡ በተጨማሪ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓት የተለየ ነገር እንዳያደርግ ሠራ፡፡ የትግራይ ሕዝብ ችግር እንዲወሳሰብ አደረገ። የትግራይ ሕዝብ ትክክለኛ እርሱ ሲለው የነበረውን እንዲሆን አደረገ፡፡ ይህንን ያደረገው ሕወሓት ራሱ ነው። ሕወሓት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ሰርጎ ገባ። ይህ የሆነው በመንግሥት ዳተኝነት ነው፡፡
የፌዴራል መንግሥት ሁኔታውን በቅጡ አለመ ገምገም፤ ሥራዎችን ተከታትሎ ያለማስፈፀም ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እኔ ራሴ ትግራይ ገብቼ ሶስት ወር ብቆይም የሕወሓት ኔትወርክ አስወጥቶኛል፡፡ በጊዜው ሁኔታው ከቀጠለ በትግራይ በኩል ለውጡ ሊቀለበስ እንደሚችል ተናግረን ነበር፡፡ ያ በትክክል ሆኗል፡፡ አሁን የሕወሓትን መዋቅር ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ አዲስ መፍጠር ያስፈ ልጋል፡፡ ለውጡ በደንብ እንዲመራ የለውጥ ሰዎችን ወደ ፊት ማምጣት ይገባል፡፡ መንግሥት አስቀምጦት የነበረው የሕወሓት ካድሬ ለውጡን በቅጡ የማያውቅ ለራሱም ተሃድሶ የሚያስፈልገው ነው። ስለዚህ ለውጡ በቅጡ እንዲመራ ተደርጎ መታገል ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሕወሓትን ለማጥፋት የሕዝቡ ሚና እስከ ምን ድረስ ነው? ከዚህ ጋር ተያይዞ እርስዎ የሚሰማዎት ምንድን ነው ?
አቶ ሙሉብርሃን፡- የትግራይ ሕዝብ ስቃይ በጣም ረዥም ነው፡፡ አሁንም ሕዝቡ በጣም በስቃይ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ስቃይ እንዲያበቃ፤ ይህ ኃይል መወገድ መቻል አለበት፡፡ ይህ ኃይል እንዲወገድ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ መታገል መቻል አለበት፡፡ ሕዝቡ ነቅቶ በመደራጀት መታገል አለበት፡፡ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ሌላ አደረጃጀት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ከዚህ በላይ ዋጋ መክፈል የለበትም፡፡ ስለዚህ መታገል መቻል አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፊት የትግራይ እጣ ፈንታ እና አጠቃላይ ሁኔታ ምን መሆን አለበት?
አቶ ሙሉብርሃን፡– የትግራይ ክልል ከሌሎች ክልሎች በጣም የተለየ ነው፡፡ የትግራይ ክልልን የተለየ የሚያደርገው ሕወሓት በትግራይ ክልል መፈጠሩ ነው። ሕወሓት ትግል በሚል ከሕዝቡ ጋር የተቆራኘ ነው። ይህ የተለየ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ ሕዝቡ ከጭንቀቱ እንዲገላገል ይህ አሸባሪ ኃይል መወገድ መቻል አለበት፡፡ ከተወገደ በኋላ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በወታደራዊ ኃይል ቢቆይ መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የተለያዩ የትግራይ ፓርቲዎች እና ልሂቃን ሥራዎችን ከሠሩ በኋላ የተዛቡ ሕወሓት የፈጠራቸውን ትርክቶች የማጥፋት፣ ተንኮል እና ሴራዎችን የማጥፋት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ ከዛ ወደ ተለመደ ሕይወቱ እንዲመለስ፤ መሠረተ ልማት እንዲጀመርለት ቢያንስ መብራት በመቀጠል ደግሞ የቴሌ አገልግሎት፣ ትራንስፖርት እንዲያገኝ እና ከረሃብ እንዲወጣ ሕዝቡ እንዲያገግም መሠራት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ የገባበት ችግር ከባድ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ ሙሉብርሃን፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 11/2014