ባለፉት ተከታታይ ሳምንቶች የኢትዮጵያን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም የምርምርና ፈጠራ ሥራዎች የሚያስቃኙ መረጃዎችን ስናደርሳችሁ ሰንብተናል። ዛሬም እንደተለመደው ወቅታዊና አዳዲስ የአገራችንን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ አድርገን ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
መረጃዎቹን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም ሌሎች የመረጃ ምንጮቻችን አድርሰውናል።
የበዓላት ወቅት የደህንነት ጥንቃቄዎች
የታኅሣሥና የጥር ወር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ተወዳጅ በዓላት ከሚከበሩበት መካከል ይመደባል። ከቀናት በፊት በታኅሣሥ መጨረሻ ላይ የተከበረው የገና በዓልና ከማክሰኞ ጀምሮ ረቡዕ እና ሐሙስ ጭምር በድምቀት የሚከናወነው የጥር ወቅት የጥምቀት (ከተራ)፣ ጥምቀትና ሌሎች ክብረ በዓል ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ «በበዓልም ወቅት የሚፈፀም ዲጂታል ወንጀል» አሊያም ጥቃት መኖሩን ነግሮናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊደረግ ስለሚገባ ጥንቃቄ እንዲሁ መረጃዎችን አድርሶናል።
ለመሆኑ በበዓላት ወቅት የሚፈፀመው ይህን መሰል ወንጀል ምን ዓይነት ባህሪ አለው? የበዓላት ወቅቶች ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ የሳይበር ወንጀለኞች በቀላሉ የመረጃ ጥቃቶችን ለማድረስ የተመቹ ወቅቶች ናቸው፡፡ በዓልን ጠብቀው በሚፈጸሙ ሳይበር ጥቃቶች ሳቢያም የገንዘብ ስርቆት፣ የማንነት ስርቆት እና የማጭበርበር ተግባራት በስፋት ይስተዋላሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራችን ብዙዎች የኦንላይን ግብይቶችን በቴሌግራም፣ በፌስቡክ፣ በዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም እና በመሳሰሉት ማህበራዊ የትስስር ገጾች በስፋት እየተዋውቁ እና ግብይቶች እየፈጸሙ ያሉበት ወቅት ነው፡፡
ይህ ሁኔታም በበዓል ወቅት ሸማቾች በመረጃ መንታፊዎች እና አጭበርባሪዎች እጅ ላይ ሊወድቁ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡
በበዓላት ወቅት በመረጃ መንታፊዎች እና አጭበርባሪዎች እጅ ላይ እንዳይወድቁ ሊያደርጓቸዉ የሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች ውስጥ የሚከተሉት ቀርበዋል።
የመጀመሪያው ወደ መልዕክት መቀበያ ሳጥንዎት የሚላክሎትን አጠራጣሪ አገናኞች /links/፣ አባሪዎች / attachments/ እና ሌሎች መልዕክቶችን ከመክፈትዎ በፊት በጥንቃቄ ያጢኑ፡፡ በባዓላት ወቅት የመረጃ ጠላፊዎች አጥፊ ተልዕኮ ያላቸው ሰነዶችን፣ ደረሰኝ፣ ስጦታ፣ የትዕዛዝ መረጋገጫ በማስመሰል ሊልኩልዎት ይችላሉ፡፡
በኢ-ሜይል ለሚላክልዎት ቅጽ ወይም አገናኝ የይለፍ-ቃልዎን ወይም የፋይናንስ መረጃዎን አያስገቡ። ስጦታ ሲቀበሉም ሆነ ሲሰጡ ጥንቃቄ ያድርጉበዚህ በዓል ቴክኖሎጂ ነክ ስጦታ እየተቀበሉ ወይም እየሰጡ ከሆነ የሚጠቀሙበት ቁስ የዘመነና የቅርብ ጊዜ ሶፍትዌር ያለው መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ሶፍትዌሮች ተጋላጭነቶችን የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያዘምኑ።
ያገለገለ ቁስ እየተቀበሉ ወይም እየሰጡ ከሆነ ከመስጠትዎ ወይም መጠቀም ከመጀመርዎ በፊት መሣሪያውን ወደ መጀመሪያ የፋብሪካ ምርት ሥርዓት /factory reset/ መመለስዎን ያረጋግጡ፡፡
የበይነ-መረብ ጋር የተቆራኙ ቁሶችን /IoT/ ደህንነት ለመጠበቅ የሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ እርምጃዎችን ይውሰዱ። ከበይነ-መረብ ጋር የተቆራኙ ቁሶች ደካማ የሚባል የደህንነት ጥበቃ ሪከርድ ያላቸው በመሆኑ የቁሶችን ደህንነት በአግባቡ አለማስጠበቅ ለአጥፊዎች ይበልጥ ሥራቸውን ቀላል እያደረጉላቸው መሆኑን አይዘንጉ፡፡ በመሆኑም፡-
በቁሶቹ ላይ ከሚገኙ የደህንነት ሥርዓቶች በባለብዙ ደረጃ የማንነት ማረጋገጫ ዘዴዎችን ይጠቀሙ፤ በቁሶቹ ላይ የነበረውን ነባሪ /default/ የይለፍ-ቃል ይቀይሩ፤ የዘመነ ሶፍትዌር ይጠቀሙ፡፡ ከሁሉ በላይ የበዓሉ ግርግር እና ወከባ ከበየነ-መረብ አደጋዎች ጥንቃቄ እንዳያዘናጋዎት ጥንቃቄ አይለየዎ እንላለን!! “”
የኢ-ሜይል ሳይበር ጥቃት ምንድነው?
በአሁኑ ወቅት ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ «በኢ-ሜይል አማካኝነት የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ መከላከል እንችላለን?» የሚለው ሲሆን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ይህንንም ጉዳይ በተገቢው መንገድ በዚህ መልኩ አስቀምጦታል።
የኢ-ሜይል-ፊሺንግ (email fhishing) አንዱ የሳይበር ጥቃት መፈጸሚያ ዘዴ ሲሆን የመረጃ በርባሪዎች ኢላማ ያደረጉትን ሰው መረጃ ለመመንተፍ የተለያዩ ይዘት ኖሯቸው ለመክፈት የሚያጓጉ አገናኞች/links/፣ አባሪዎች (attachments) የያዙ መልዕክቶች ወደ ተጠቂው በመላክ እና እንዲከፍት በማድረግ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ናቸው።
ለምሳሌ ትልቅ ሽልማት እንዳሸነፉ የሚገልፁ መልዕክቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህም የሚከሰተው አንድ አጥቂ የታመነ አካል በመምሰል የተጠቂውን ኢ-ሜይል ፈጣን መልዕክት ወይም የጽሑፍ መልዕክት እንዲከፍት በማድረግ የሚፈጸሙ ናቸው። ቀጥሎም በከፈተው ኢ-ሜይል ላይ አጥፊ ተልዕኮ ባዘሉ አገናኞች /links/ አማካኝነት ወደሚፈልጉት አደገኛ ገጽ እንዲገቡ በማድረግ ጠቃሚ ወይም ምስጢራዊ መረጃ ለአደጋ ይጋለጣል።
መደረግ ያለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች
ኢንተርኔት ከፍተን ያለፍቃዳችን ብቅ እያሉ እንድንጭናቸው የሚጠይቁ ማስታወቂያዎች ውስጥ በመግባት ምስጢራዊ መረጃዎችን ከማስገባት መቆጠብ፤ የግል እና ምስጢራዊ መረጃዎን እንዲሁም የገንዘብ ነክ መረጃን በበይነመረብ ላይ በጭራሽ አለማጋራት፤ የመረጃዎቻችንን መጠባበቂያ (backup) መያዝ መረጃው ቢጠፋ ወይም ቢወድም መረጃዎቹን መተካት የሚያስችል ምትክ መጠባበቂያ መያዝ፤ የሚጠቀሙትን የድረ-ገጽ ደህንነት ማረጋገጥ በመረጃ ማፈላለጊያው (browsers) የአድራሻ ባር ላይ (HTTPS) መኖሩን በማየት ማረጋገጥ፤ አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ፋየርዎልን (firewall) መጫን ኮምፒዩተር ላይ አጥፊ ተልዕኮ ያላቸው ሶፍትዌሮች እንዳይገቡ መከላከላል፤ የባለ ብዙ ደረጃ የደህንነት ማረጋገጫ መጠቀም፣ ለምሳሌ የአንድ ጊዜ የይለፍ-ቃል በኤስ ኤም ኤስ መልዕክት በኩል የሚገባ፣ physical token፣ የባዮሜትሪክ አይዲ/ID ተግባራዊ ማድረግ።
የኦንላይን ላይ መለያዎችዎን በመደበኛነት ይመልከቱ ወይም ያረጋግጡ። ለምሳሌ፤ የይለፍ-ቃሎችን በመደበኛነት መቀየር፣ የእርስዎን የባንክ ሂሳብ መግለጫዎች / statements/ በመደበኛነት ያረጋግጡ። የመረጃ ማፈላለጊያዎን (web browser) ወቅቱን ጠብቀው ያዘምኑ፤ አላስፈላጊ የሆኑ የኢሜይል መልዕክትን ማጣራት /Filter Spam/ የማይታወቁ ወይም አስፈላጊ ያልሆኑ የኢ-ሜይል መልዕክቶች ወደ ግልዎ ወይም የድርጅትዎ የመልዕክት ሳጥን እንዳይገቡ ማገድ፤ ሰዋሰዋዊ ስህተቶች እና የፊደል ግድፈቶች ያሉባቸው ድረ-ገፆችን ሁልጊዜ በትኩረት ማየት እና አለመጠቀም እንዲሁም ያለዎትን ማንኛውንም ምስጢራዊነት ያለው የግል መረጃ መስጥሮ መያዝ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት
ከሰሞኑ ከተሰሙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ «ከቴክኖሎጂ አንፃር ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ሕግ ሊኖር ይገባል» ሲሉ መናገራቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሚኒስቴሮች የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸምን አስመልክቶ በተካሄደው ግምገማ ላይ ነው።
ቴክኖሎጂ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ እንዳይውልና ተጠይቂነትን ለማስፈን የቴክኖሎጂ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ሕጎች ሊኖሩ እንደሚገባ አንስተዋል። የተቋማት አሠራሮች የኦቶሜሽን ሥራ ሲሠራ ሁሉም ተናባቢ፣ ደረጃ የወጣላቸው እና ሥራን የሚያቀላጥፉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።
ዲጂታላይዜሽን ለሁሉም ዘርፍ የሚጠቅም መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ ትምህርት፣ ጤና፣ ገቢ እና ሌሎችም ተቋማት ሥራቸውን በዲጂታል መልክ ለመስራት ቴክኖሎጂ ሰፊ መሠረት ልማት ይጠይቃል ሲሉም ተናግረዋል።
ለከተሞችና ተቋማት የተሠሩ ፖርታሎችን ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂን ለሀብት ማግኛነት መጠቀምና አገር በቀል እውቀት ያላቸውን ሰዎች መደገፍ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ ማድረግ ላይ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ- ዳያስፖራው
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን “GreatEthiopianHomeComing” ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የመጡና በመምጣት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች ሁሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ኤጀንሲው «ዳያስፖራው ወደ እናት አገሩ ሲመጣ በተለያዩ አግባቦች እናት አገሩን ለማገዝና የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ እንደሆነ ይታወቃል» በማለት አገራቸውን አቅማቸው በፈቀደ መጠን በተለያየ መስክ ለማገዝ በመምጣታቸው ኤጀንሲው የተሰማውን አድናቆት ገልፆ፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወይም በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የሚሠራ ተቋም እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ በእውቀታቸው፣ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ቴክኒካል ጉዳዮች ለማገዝ እና የራሳቸውን አበርክቶ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ተቋሙ በደስታ የሚቀበል እና የሚያስተናግድ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ጉዳይ ከኤጀንሲው ጋር በጋራ ለመሥራት የሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላት በ «አዲስ ዳያስፖራ ማዕከል» በኩል ወይም በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /INSA/ በቀጥታ ግንኙነት መፍጠር እንደሚችሉም አረጋግጧል። ከዚህ መረጃ ጋር በተያያዘ ወደ አገር ቤት የመመለስ ጥሪን ተቀብለው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጋር መምከራቸው ታውቋል።
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ነጋሽ፣ በአትላንታ የኢንፎርሜሽን ሲስተም አርክቴክቸር ባለሙያ የሆኑ አህመድ ጀማል እና በ ቨርጂኒያ የመረጃ እና የመሠረተ ልማት ደህንነት አማካሪ የሆኑት ፍስሃ ደስታ አገራቸውን በዘርፉ ለማገልገል እንደሚፈጉ ተናግረዋል።
የዲጂታል አገልግሎቶች ጥራት እና ደረጃን በማስጠበቅ፣ በዲጂታል ሴኩሪቲ፣ በዲጂታል ኦዲትና በዲጂታል ኢኖቬሽን ላይ ያላቸውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በዘርፉ የተሰማሩና በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን በማስተባበር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ዳያስፖራዎቹ አገራቸውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በመምጣታቸው አመስግነው ስል ኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሠራች ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በዘርፉ የባለሙያዎችን አቅም ለመጠቀምና በትብብር ለመሥራት ተቋሙ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል። ባለሙያዎቹ የዲጂታል ፎረም ላይ እንደሚሳትፉ እና ተሞክሯቸውን እንደሚያጋሩ አስታውቀው ነበር።
የከተሞችና ተቋማት ፖርታሎች
የከተሞችና ተቋማት ፖርታሎች የዜጎች ታማኝና የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ሊሆኑ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናግረዋል። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለ5 ከተሞችና ለ6 የፌዴራል ተቋማት ፖርታሎችን በማልማት አስረክቧል።
ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ጋምቤላ፣ ጅማ እና ሆሳዕና የከተማ ፖርታል የለማላቸው ከተሞች ናቸው። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ፖርታል የለማላቸው የፌዴራል ተቋማት ናቸው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የመንግሥት አገልግሎቶችን በሂደት ወደ ዲጂታል የአሠራር ዘዴ የሚቀየሩበትን ስልት በመንደፍ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።
የከተሞችና ተቋማት ፖርታሎች የዜጎች ታማኝና የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለሙያዎች ፖርታሎቻቸው የዳበረና አዳዲስ መረጃ እንዲይዙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ፖርታሎቹ የከተሞቹንና የተቋማቱን ልዩ አወቃቀራቸውን፣ አገልግሎቶቻቸውን እና የቱሪስት መስህቦችንና አጠቃላይ መረጃዎችን የያዙ ናቸው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፖርታል የመረጃ አስተዳደርና አጠቃቀም ስልጠና ለሕዝብ ግንኙነትንና የአይሲቲ ባለሙያዎች፣ የፖርታል ልማት ቴክኒካል ስልጠና ደግሞ ለአይሲቲ ባለሙያዎች ሰጥቷል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥር 10/2014