የትኛውንም በጎ ሥራ ለማከናወን እድሜ፤ ጾታና ሌሎች ማንነቶች መሠረት አይሆኑም። ይህም ሆኖ አዲስ ጉልበት፣ አዲስ እሳቤና ጠንካራ ስሜት ያላቸው ወጣቶች ሲከውኑት ደግሞ ከቁሳዊ ጥቅሙ ባለፈ ለትውልድ አሻራን የማስቀመጥ፤ የታሪክ አጋጣሚ የፈጠረውን ታሪክ የመሥራት ዕድልን የመጠቀምም ገጠመኝ ይሆናል። የልደታ ክፍለ ከተማ ኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ባለፉት ዓመታት በክፍለ ከተማው ለሚኖሩ ዜጎች ተደራሽ ሲያደርግ የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሳያቋርጥ ወቅቱ ለፈጠረው የትብብር ጥያቄም ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል።
እኛም የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ የሆኑትን አቶ ክብረአለም ደምሴን አነጋግረን ሕዝብን በማስተባበር ወገንን ከችግርና ከሰቆቃ ለመታደግ የተሠሩትን ሥራዎች እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመለት መሠረታዊ ዓላማ አጠቃላይ ኅብረተሰቡ አቅሙ፤ ጉልበቱና እውቀቱ በፈቀደ በበጎ አድራጎት ተግባራት እንዲሳተፍ ማስተባበር ነው። ይህም ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን የሚያካትት ሲሆን በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ነው።
ጽሕፈት ቤቱ በዋናነት ለበጎ ሥራዎች እንቅስቃሴ ምንጭ የሚያደርጋቸው ከተቋማት፤ ከወጣቶችና ሌሎች አደረጃጀቶች ጀምሮ መላውን ሕዝብ ተሳታፊ በሚያደርግ ነው። በዚህም በክፍለ ከተማው ሰላሳ ስምንት የተደራጁ የበጎ ፈቃድ ማኅበራት ያሉ ሲሆን። እነዚህና ውል ከተፈራረማቸው ተቋማትም ጋር በጥምረት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየከወነ ይገኛል። ለድጋፍ የሚውለውን በገንዘብና ቁሳቁስ ማሰባሰብ ረገድ የክፍለ ከተማው ባለሀብቶች በቀዳሚነት ከፍተኛ ትብብር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በክፍለ ከተማው የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ የተለያዩ ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የደሃ ደሃ ተብለው የተለዩና በራሳቸው አቅም መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ሟሟላት ለማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፤ ያረጁ ቤቶችን ማደስ አንደኛው ነው። ይህ ሥራም አረጋውያን እናቶችና አባቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞችና በተለያዩ ሕመሞች የተጠቁትን ወገኖች ያካተተ ነው። ለእድሳት የሚመረጡት አብዛኛዎቹ ቤቶች በእርጅና ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ ሲሆን ነዋሪዎቹን ለተለያዩ ችግሮች ሊዳረጉ የሚችሉም ናቸው።
የእደሳው ሥራ የሚከናወነውም ለእያንዳንዱ የተመረጠ ቤት ፕሮግራም በማውጣት ከባለ ሀብቶች፤ ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶችና ሌሎች ይመለከተናል ከሚሉ አካላት ጋር በመቀናጀት ነው። በዚህ ዓይነትም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በክፍለ ከተማው ሶስት መቶ አስራ ስምንት ቤቶችን በማደስ ለአቅመ ደካሞች እንዲዳረስ ማድረግ ተችሏል። ከእነዚህም መካከል በጤና ሚኒስትር በገንዘብ ድጋፍ ተባባሪነት የተሰሩ አስራ ስድስት ቤቶችን በጥሩ ደረጃ በማደስ ለልደት በዓል ለተገልጋዮች ማስረከብ ተችሏል። የቤት እድሳት ፕሮግራም ቁሳቁሶች ተሟልተው ሲገኙ ግዜ ሳይለይ በበጋም በክረምትም በበጎ ፈቃደኞች የሚከወን ነው።
ሁለተኛው የክፍለ ከተማው የበጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት ተግባር ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው ለአረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞችና በተለያዩ ችግሮች ራሳቸውን ችለው መኖር ለማይችሉ እየተደረገ ያለው ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብር ነው። ይኸው ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብር የሚከናወነው ከወረዳ ጀምሮ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ተለይተው ለሚመጡት የደሃ ደሃ ችግረኛ ቤተሰቦች በአንድ ማዕከል ነው።
በተጨማሪ ተጠሪነታቸውን ለጽሕፈት ቤቱ ያደረጉ ወረዳዎች ላይ ያሉ ተቋማቶች በተመሳሳይ በዚህ ተግባር የሚሳተፉ አሉ። እነዚህ ተቋማትም የራሳቸውን መስመር በመጠቀም የሚያሰባስቡትን ሀብት፤ ቁሳቁስና ሌሎች አገልግሎቶች አቅማቸው ለደከመና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ተደራሽ እያደረጉ ይገኛል።
በሦሥተኛ ደረጃ በጽሕፈት ቤቱ እየተሰጠ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተከታታይነት ያለው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ነው። የዚህ የደም ልገሳ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል አሁን የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ እንዲሁም በአዘቦቱ ግዜ ከፍተኛ የደም አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ስለሚታወቅ ሲከናወን የነበረና በአሁኑ ወቅትም በመከናወን ላይ ያለ ነው። የደም ልገሳ መርሐ ግብሩ የሚከናወነውም ሁሌም የሚኖር ፍላጎት አቅም በፈቀደ ቀላል ማድረግ ነው።
በዚህ ዓመትም እስካሁን ከሶስት ሺ ስድስት መቶ በላይ ዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏል። በደም ልገሳ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ባለፈ ከኦሮሚያ፤ አማራ፤ ደቡብና የአዲስ አበባ ወጣት ማኅበራትና የሴት አደረጃጀቶች እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ ግለሰቦችን አሳታፊ የሚያደርግ ነው። የደም ልገሳ መርሐ ግብሩ «ሕይወቱን ለሰጠኝ ደሜን እሰጣለሁ» በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ሲሆን የተሰበሰበውም ደም ለመከላከያ ሠራዊት፤ ለአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሚሊሻና ፋኖ እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል።
ሌላው የጽሕፈት ቤቱ የበጎ አድራጎት ተግባር በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት ለማስተካከል ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው። በዚህም ወጣቶችና ጎልማሶች የተለያዩ ስልጠናዎችንና ትምህርቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህ መርሐ ግብርም መማር መሰልጠን እየፈለጉ ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ በተለይ በኢኮኖሚ ችግር የትምህርት ተቋማትን ለመቀላቀል ዕድሉን ያላገኙትን በቀዳሚነት ተመራጭ የሚያደርግ ነው። በዚህ ረገድ እስካሁንም ከተለያዩ ኮሌጆች ዩኒቨርሲቲዎችና ባለሀብቶች ጋር በመነጋገር በሚገኙት የትምህርትና ስልጠና እድሎች በርካታ የመማር ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በተጨማሪም እናትና አባታቸውን አልያም ከሁለቱ አንዱን ያጡ ወይንም ወላጆቻቸው በመሠረታዊነት የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ሊያሟሉላቸው ላልቻሉ ሕጻናት የሚደረጉ ድጋፎችም አሉ። በዚህም በተመሳሳይ ከባለሀብቶች የትምህርት ተቋማትና ሌሎችም በጎ አድራጊዎች ጋር በመነጋገር ሕጻናቱ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው ትምህርታቸውን በመከታታል ብቁ አገርና ሕዝብ ወዳድ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ጽህፈት ቤቱ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ብዙ ግዜ ተደራሽና ተጠቃሚ ለማድረግ አስቸጋሪ በሆነው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ጽሕፈት ቤቱ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ እየሠራ ነው። በዚህ ረገድም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ በክፍለ ከተማው ወረዳ አስር ውስጥ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች ሃምሳ ዊልቸሮችን ሀቢታት ፎር ዲቨሎፕመንት ከሚባል የበጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር እንዲደርሳቸው ማድረግ ተችሏል።
ከአስር ቀን በፊትም የገናን በዓል በማስመልከት ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የዘማች ቤተሰቦች አንድ አንድ በግና አንድ አንድ ዶሮ እንዲሁም ሀምሳ ኪሎ ዱቄትና ስኳር ድጋፍ ተደርጓል። ከዘማች ቤተሰቦች ጋር በተያያዘም ቤት ላልነበራቸው ሃያ ሰባት የዘማች ቤተሰቦች ቤት እንዲሰጣቸው ማድረግ በመቻሉ በግንባር ነፍስና ሥጋቸውን እየሰጡ ያሉ ቤተሰቦችን ለመንከባከብ ተችሏል።
በአጠቃላይ ጽሕፈት ቤቱ በክፍለ ከተማው እስካሁን ከሃምሳ ሺህ በላይ ዜጎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። እነዚህ ሰዎች በአማካይ ሦሥት ሰዎች በሥራቸው የያዙ ሲሆን ይህም የተደጋፊውን ቁጥር ከአንድ መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ያደርሰዋል።
በሌላ በኩል በአካባቢ ጥበቃና በአካባቢ ልማት ሥራዎችም ጽሕፈት ቤቱ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። እነዚህ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራዎች የሚሠሩትም ሁለት መሠረታዊ ጥቅሞችን እንዲያስገኙ ታሳቢ በማድረግ ነው።
የመጀመሪያው በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ የሚደረጉ ዜጎች የሥራ ዕድል ያላገኙ በመሆናቸው በተፈጠረላቸው የሥራ እድል በመጠቀም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ነው። በሁለተኛ ደረጃም እንደ ማኅበረሰብ ያለውን ሠርቶ የማግኘት፤ ሠርቶ የመብላት ባህል እንዲዳብር የሚያስችል ይሆናል። እስካሁንም በአካባቢ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ለማስፋፋት ልማት በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በርካታ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል።
ችግኝ መትከል ብቻውን በቂ ባለመሆኑም ዛሬም ድረስ ከጽዳትና ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ጋር በመቀናጀት በየሃያ ቀኑ በዘመቻ እንቅስቃሴው የተተከሉት ችግኞች እንዳይደርቁ የመንከባከብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም ጽሕፈት ቤቱ በአገሪቱ የተከሰተውን ጦርነትና እሱን ተከትሎ የተፈናቀሉትን ዜጎች መታደግ የመጀመሪያ መዳረሻው በማድረግ በመሥራት ላይ ይገኛል። በጽሕፈት ቤቱ ተነሳሽነትም በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያሉበት ድረስ በመሄድ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል። በዚህ በኩልም እስካሁን ጽሕፈት ቤቱ በሸዋ ሮቢት ከተማ ባለሀብቶችና የበጎ አድራጎት ማኅበራትን በማስተባበር ሰባት ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል። ከተደረገውም የቁሳቁስ ድጋፍ ውስጥ ብርድ ልብስ፤ የሴቶችና ሕጻናት የንጽሕና መጠበቂያ እንዲሁም ሌሎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ለጉዳት ለተዳረጉ ዜጎች ቤተሰቦች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በተመሳሳይ የጽሕፈት ቤቱ ልዑካን በጣርማ በር በመገኘት ያዘጋጁትን አርባ ሺህ የሚደርስ የታሸገ ምግብና ውሃ በማቅረብና የመከላከያ ሠራዊትን የአማራ ክልል ሚሊሻና ፋኖን መመገብ ተችሏል። ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅትም የወገን አለኝታነትን ለማረጋገጥ በጋሸና ግንባር በመገኘት ሃምሳ በሬና ሁለት መቶ በግና ፍየል ለሠራዊቱ እንዲደደርስ ተደርጓል።
በቅርቡም በወሎ ግንባር ለሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ሰማኒያ በጎች የተላኩ ሲሆን፤ ተፈናቃዮችን ለመደገፍም በወልድያ ከተማ ለሚገኙት የመድኃኒት ድጋፍና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት አከናውኗል። ሰሞኑንም በኦሮሚያ ክልል በቦረና አካባቢ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ለእንሰሳት መኖ የሚውል ሳርና ውሃ የተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ እንዲደርሳቸው የሚደረግ ይሆናል።
ከእነዚህ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ውጪም ጽሕፈት ቤቱ በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በቋሚነት ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ለማድረግ የሚሠሯቸው ሥራዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል የመሥራት አቅሙና ፍላጎቱ ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ ነው።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በልደታ ክፍለ ከተማ አካባቢ ላሉ አራት መቶ የሚደርሱ ሥራ አጦች በኮብል ስቶን ግንባታና የመንገድ ሰብ ቤዝ ግንባታ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በዚህ አይነት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አራት መቶ ነዋሪዎች እድሉን በማግኘታቸው በዘላቂነት ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚያግዛቸው ይሆናል።
አቶ ክብረአለም ጽሕፈት ቤቱ በቀጣይ ለሠራቸው በእቅድ ያስቀመጣቸውን ሥራዎች ሲያብራሩም፤ በቅድሚያ ጽሕፈት ቤቱ በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚንቀሳቀስ ይሆናል። በዚህም ከቀጥታ የእለት ፍጆታ ፍላጎት አቅርቦት ባለፈ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት፤ ጤና ተቋማትን መልሶ የመገንባትና የማቋቋም፤ እንዲሁም በአሸባሪው ቡድን አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው የወደሙትን ዩኒቨርሲቲዎች ከባለሀብቶችና ወጣቶች ጋር በመሆን መልሶ የመገንባትና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ለመፈጸምም በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች በሙያቸው የወደሙትን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ተሳታፊ ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ፈርኒቸር አምራቾች፤ በግንባታ ሙያ ውስጥ ያሉ ወገኖች ተደራጅተው የተዘጋጁ ሲሆን ወደ ሥራ ለመግባት የሚመለከተውን አካል ጥሪ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
በቀጣይ ሁኔታዎች ተመቻችተው ከከተማ መስተዳደሩ ጥሪ ሲደረግላቸውም ወደ ቦታው በመሄድ ሥራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል።
በተጨማሪም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወንበር፣ ጠረጴዛና ሌሎች ለቢሮና ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በጦርነቱ ወደተጎዱት አካባቢዎች ለማድረስም እቅድ ተነድፏል። እንደ ክፍለ ከተማም እስካሁን የደሃ ደሃ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በዚህም በእቅድ የተያዙ መታደስ ያለባቸውን ቤቶች ያድሳል፤ ለተለዩ የሥራ እድል ፈላጊዎች ሥራ ይፈጥራል እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን ለማቋቋም የተጀመረውንም ሥራ በቋሚነት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥር 6/2014