
የአቤቱታው ጭብጥ
የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪው አቶ በቀለ ወዳጆ የፍትህ ችግር አጋጥሞኛል በማለት ወደ ቢሯችን መጥተዋል። ፍርድ ቤቶች በሕግ ማግኘት የሚገባኝን መብት አሳጥተውኛል በማለት አቤቱታ ይዘው ሲቀርቡ፤ ፍረዱኝ ለማለት ያነሳሳቸው ‹‹ፍርድ ቤቶች ያለአግባብ ውሳኔ ሰጥተዋል።
ለሚመለከታቸው አካላት የሕግ ስህተት የተፈጠረ መሆኑን ባሳውቅም ጉዳዬን በተገቢው መልኩ አላዩልኝም›› የሚል እምነት ስላደረባቸው ነው። አቶ በቀለ በዚህ ምክንያት በምሬት ዝግጅት ክፍላችን ድረስ ቀርበው ተፈፀመብኝ ያሉትን በደል ዘርዝረዋል።
ሃሊላ ቀበሌ ገበሬ
የአቶ በቀለ ወዳጆ ጉዳይ የመሬት ክርክር ነው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በ1992 ዓ.ም በምስራቅ ባሌ ዞን፣ በጎሎልቻ ወረዳ የሃሊላ ቀበሌ አስተዳደር የሕዝብን መንገድ ድንበር በማድረግ መሬት እንዲከለልላቸው ፍቃድ ሰጥቶ ነበር። ቀበሌ አስተዳደሩ ለአቶ በቀለ መሬት ይሰጥ ብሎ ያዘዘበት ማስረጃ አለዎት? በሚል ዝግጅት ክፍሉ ለአቶ በቀለ ላቀረብንላቸው ጥያቄ እርሳቸው ሲመልሱ፤ አሠራሩ በወረቀት አይደለም።
የገጠር መሬት ላይ በአብዛኛው የሚሰጠው የአካባቢው ሽማግሌዎች ድንበር አድርጉ እየተባሉ ይታዘዛሉ። እነርሱም ድንበር ካደረጉ መሬቱ የዛ ሰው ነው ማለት ነው በማለት አሠራር ነው ያሉትን አስረዱ፡፡
በመቀጠል አቶ በቀለ በ1999 ዓ.ም ለየት ባለ መልኩ በቀበሌው የሕዝብ መሬት ይዘሃል የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ይገልፃሉ። አቶ በቀለ የያዙት መሬት በ2000 ዓ.ም ይልቀቁ የሚል ውሳኔ በቀበሌው ፍርድ ሸንጎ ተላለፈ።
ከሳሹ እና ፈራጁ ራሱ መሬት ሰጠ የተባለው የሃሊላ ቀበሌ ነበር፡፡ ቀበሌው ይህንን ውሳኔ ቢያስተላልፍም ትክክል አይደለም ለማለት ይከብዳል። የሰነድ ማረጋገጫ ከሌለዎት መሬቱ ለእርሶ ስለመሰጠቱ ማስረጃዎት ምንድን ነው? በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ በቀለ በድጋሚ መልስ የሰጡት መሬቱ ለእኔ ስለመስጠቱ የኔ ቃል ብቻ አይደለም።
በሰው ተመስክሮልኛል የሚል መልስ ሰጡ። ድንበሩን የወሰኑት ሽማግሌዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ‹‹ ቀበሌ አስተዳደር አዞን ድንበር አድርገናል›› በማለት መመስከራቸውን ተናገሩ። አቶ በቀለ እንደሚሉት፤ መሬቱን ከስምንት ዓመት በኋላ እንደ አዲስ በ2000 ዓ.ም ቀበሌው አዲስ ውሳኔ ማስተላለፉ ከጀርባው ሌላ ጉዳይ አለው። ምክንያቱም መሬቱን አስመልክቶ በቀበሌ ሸንጎ የተላለፈው ውሳኔ ‹‹ አቶ በቀለ የያዘው የሕዝብ መሬት መለቀቅ እንዳለበት አዘናል። ›› የሚል ነበር። ነገር ግን መሬቱ የሕዝብ አልሆነም።
እንደውም በቅርብ ለሚያውቋቸው ለሁለት ሰዎች እንደተሰጣቸው ከተናገሩ በኋላ፤ ‹‹የሕዝብ ከሆነ ለምን ከእኔ ተነጥቆ ለሌላ ተሰጠ?›› በማለት ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ በቀለ፤ የቀበሌው አስተዳደር እርሳቸውን ነቅሎ ለሌሎች ሰዎች መሬቱ መሰጠቱን በንዴት እየገለፁ፤ የቀበሌው አስተዳደር በጊዜው እርሳቸውን ከቦታው ነቅሎ ሁለት ሰዎች መሬቱን እንዲይዙት ያደረገው በገንዘብ ስለተገዛ እንጂ ሌላ ይህ እንዲደርግ የሚያስችል ምንም ምክንያት እንደሌለው ይገልፃሉ። ቀበሌው እርሳቸውን እንዳስለቀቀ በዛው በ2000 ዓ.ም ሌሎች ሁለት ግለሰቦች መሬቱን ወስደዋል።
እርሳቸው ደግሞ ወዲያው ለወረዳው ፍርድ ቤት የቀበሌውን ውሳኔ አስመልክቶ ይግባኝ ጠይቀዋል። አቶ በቀለ ያቀረቡት የሰነድ ማረጋገጫ እንደሚያመለክተው በእርግጥም የባሌ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ለምለም ሃሊላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ጽሕፈት ቤት አቶ በቀለ ወዳጆ የያዘውን መሬት ለሕግ እንዲለቅ የሚል ውሳኔ የተላለፈ መሆኑን ያመለክታል።
ቀበሌው እኔን የነቀለኝ በሌለው ስልጣን ነው የሚሉት አቶ በቀለ፤ በኦሮሚያ የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ 130/1999 በወጣው አዋጅ የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ወይም የቀበሌ ፍርድ ሸንጎ ስለመሬት አከራክሮ መወሰን እንደማይችል በአንቀፅ 16 ላይ አግዷል። ታዲያ እንዴት ይህ ተጥሶ የቀበሌው ፍርድ ሸንጎ የመሬት ክርክር አካሂዶ ፍርድ ሰጠ? የሚለው ግራ የሚያጋባ መሆኑን ያመለክታሉ።
ይህንን ያልተገባ ተግባር ሁሉም ማየት እንደነበረበት፤ ነገር ግን ሆን ተብሎ መታለፉን እና አቤቱታ ባቀረቡባቸው አካላትም የሕግ ስህተት አልተፈፀመም መባላቸውን ይገልፃሉ።
የጎሎልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት
አቶ በቀለ ለጎሎልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀበሌው ፍርድ ሸንጎን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ አቀረቡ። ወደ ወረዳ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሲያቀርቡ ከአንድ ዓመት ክርክር በኋላ በወረዳው ፍርድ ቤት የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ውሳኔ ተሻረ። ያቀረቡት የሰነድ ማረጋገጫ እንደሚያመለክተው በቀን 21 ጥር 2001 ዓ.ም ለአቶ በቀለ ተፈረደ። እንደአቶ በቀለ ክርክሩ ቀጥሏል።
ነገር ግን እስከ አሁንም ድረስ ይህ ውሳኔ በፍርድ ቤት አልተሻረም። የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሻር ክርክርን ማስቀጠል በራሱ ትልቅ የሕግ ስህተት ቢሆንም ይህንንም አቤቱታ ባቀረቡባቸው ሰበር ሰሚ ችሎቶችም ሆነ በምክር ቤት በደንብ ባለመታየቱ የሕግ ስህተት የለም ተብሎ አቤቱታቸው ተዘግቶባቸዋል። በውሳኔው ላይ እንደተብራራው፤ የጎሎልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀበሌው ብይን ሰጥቶ ማከራከር ሲኖርበት ምስክሮችን ሰምቶ ቀጥታ ወደ ውሳኔ መግባቱ ትክክል አለመሆኑን በመጥቀስ የቀበሌው የፍርድ ሸንጎ ውሳኔ የተሻረ መሆኑን ያመለክታል።
አቶ በቀለ ይህንን ውሳኔ ተከትለው ለአፈፃፀም ማለትም መሬቱን ለማስመለስ ወደ ቀበሌው ወረዱ። ነገር ግን የወረዳውን ውሳኔ ቀበሌው ለማስፈፀም ፈቃደኛ አልሆነም። አቶ በቀለ ተመልሰው መሬቱን ማግኘት አልቻልኩም። ስለዚህ ፍርዱ አልተፈፀመም ሲሉ ለጎሎልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት ቅሬታ አቀረቡ፡፡ አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ መጀመሪያ ውሳኔውን ያስተላለፈው የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ ተቀይሮ ነበር። የክርክሩ ቦታም በአቶ ታደሰ ኡርጊ እና በአቶ ታምሩ ብሩ ተይዞ ነበር።
በዚህ ምክንያት አዲስ ክርክር ተነሳ። አዲሱ የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛ የቀበሌው አስተዳደር ያልፃፈውን ‹‹የቦታው አዋሳኝ እና ስፋት ባለመገለፁ ቀበሌው በአፈፃፀም አልገደድም›› ብሎ መልስ ስለሰጠ የሚፈፀም ነገር የለም ብሎ ወረዳው መዝገቡን ዘጋ። ይህ ተግባር አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ ፍፁም አግባብነት የጎደለው ነው። ቀበሌው ወረዳው የሰጠውን ምክንያት አልሰጠም ነበር። በእርሳቸው የይግባኝ ማመልከቻ ላይ የመሬቱ አዋሳኝ ተጠቅሷል። በቀበሌው ክስም ላይ አዋሳኙ ተጠቅሷል።
ንብረቱን ወደ ቦታው መልሱ መባል ሲኖርበት ጉዳዩ በተገላቢጦሽ ሆነ። ይሔኔ አቶ በቀለ ስለሕግ ነገር በሚል በአንድ የሚዲያ ፕሮግራም ላይ ጉዳያቸው እንዲቀርብ ለአቤቱታ ሔዱ። የፕሮግራሙ አዘጋጅ ወደ ባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሔዶ ስለጉዳዩ ጠየቀ።
የዞኑ ፍርድ ቤት ባለጉዳዩ መጥቶ ያነጋግረን በማለታቸው አቶ በቀለ ወደ ፍርድ ቤቱ ሔዱ። ‹‹በድጋሚ በአፈፃፀም ሳትገደድ መሬቱን ለቀሃል፤ መሬቱ በእጅህ ያለ ነው። ስለዚህ ወደ ኋላ ተመልሰህ መሬቱን የያዙትን ሰዎችን ክሰስ፡፡›› ተባሉ። አቶ በቀለ በበኩላቸው ‹‹ ያጨማልቁብኛል፤ ችግር ይፈጥሩብኛል። ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድሩብኛል እንጂ ፍትሕ አይሰጡኝም፡፡›› ቢሉም፤ ‹‹የፈለጉትን ውሳኔ ይወስኑ፤ ግፋ ቢል መሬቱ የሕዝብ መሬት ነው ቢሉ ነው። ወደ ዞኑ ፍርድ ቤት በዚያ ጊዜ በይግባኝ ትመጣለህ። ከዛ ጉዳዩን እኛ በደንብ እናየዋለን፡፡›› ተባሉ። በዛ መሰረት ለወረዳው ፍርድ ቤት መሬቱን የያዙባቸውን ሰዎች ማለትም አቶ ታደሰ ኡርጊ እና አቶ ታምሩ ብሩን ከሰሱ።
እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ፍርድ ቤት አንድ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ፍርዱ ሳይፈፀም እንደገና ያው ጉዳይ ለክርክር በቃ። ይህ የሕግ ስህተት ነው። ምክንያቱም አንድ ፍርድ ቤት አንድን ነገር ሁለት ጊዜ አያይም። ይህንን ሕግ በመጣስ የወረዳው ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ አከራክሮ መሬቱ የሕዝብ መሬት ነው ብሎ ውሳኔ ሰጠ። የወረዳው ፍርድ ቤት መሬቱ የሕዝብ በመሆኑ ከሳሹም ሆነ ተከሳሹ በመሬቱ ላይ መብት የላቸውም አለ። አቶ በቀለ አላቆሙም ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመሩ።
በ1992 ዓ.ም ያገኘሁት መሬት በ2000 ዓ.ም በጉልበት ተነጥቄያለሁ። ስለዚህ በሕግ ይመለስልኝ በማለት ለዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቀረቡ።
የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት
አቶ በቀለ እንደሚገልፁት፤ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወረዳውን ውሳኔ ሽሮ መጀመሪያ በአንድ ጉዳይ አንድ ፍርድ ቤት ሁለት ጊዜ ክርክር ማካሔድ አይችልም። የወረዳው ውሳኔ ከክርክሩ ውጪ የተሰጠ ነው።
በክርክሩ ውስጥ ለሌለ አካል ውሳኔ መሰጠቱ አግባብ አይደለም። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ይህንን ዘርዝሮ ገልፆ በመሆኑም ሲል ለአቶ በቀለ ውሳኔ አሳለፈ። የሰነድ ማረጋገጫው እንደሚያሳየው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጎሎልቻ ወረዳ ፍርድ ቤት በኅዳር 05 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በመዝገብ ቁጥር 08427 ላይ የሰጠው ውሳኔ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ አንቀጽ 348/1/ መሠረት ተሽሯል የሚል ውሳኔ የተሰጠ መሆኑን ያመለክታል:: አንድ ቀርጥ የሚሆን የእርሻ መሬት በምስራቅ እና በሰሜን የሕዝብ መንገድ የሆነው በምዕራብ አቶ በቀለ (ይግባኝ ባይ) በደቡብ ወዳጆ አያና ከሚዋሰነው ላይ አቶ በቀለ በአዋጅ ቁጥር 130/99 አንቀጽ 6 /1/ መሠረት መብት ያለው ስለሆነ መሬቱን የያዙት ሰዎች ማለትም አቶ ታደሰ እና አቶ ታምሩ እንዲለቁ ውሳኔ አሳለፈ።
በክርክሩ አቶ በቀለ ላይ የደረሰው ኪሳራ ብር 800 አቶ ታደሰ ዑርጊ እንዲከፍሉ እና የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተላለፈ። በዚህ መሠረት የወረዳው ውሳኔ በዞኑ ተሻረ። ነገር ግን ይህም ፍርድ ተፈፃሚነት አላገኘም።
ቦታውን ይዘው እየተጠቀሙበት ያሉት አቶ ታደሰ ዑርጊ እና አቶ ታምሩ ብሩ የባሌ ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔን በመቃወም ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ምድብ ችሎት ይግባኝ አቀረቡ።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ምድብ ችሎት
አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ ከክርክሩ ንብረት ላይ ምንም አይነት መብት የሌላቸው መሆኑ በምስክሮች ተረጋግጦ፤ ከሕግ ውጪ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የእነርሱን ይግባኝ መቀበሉ ትልቅ የሕግ ስህተት ነው። ምክንያቱም በክርክሩ ንብረት ላይ አቶ ታደሰ ዑርጊ እና አቶ ታምሩ ብሩ መብት እንደሌላቸው ታውቋል።
በሥነሥርዓት 33 መሠረት መከራከር የማይችሉ ቢሆኑም ይህንን ሕግ ጥሶ የኦሮሚያ ደቡብ ምድብ ችሎት ጠቅላይ ፍርድ ቤት አከራከረ። አቶ በቀለ ያቀረቡት የሰነድ ማስረጃ እንደሚያ መለክተው፤ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኝ ክርክር ሰምቶ አከራካሪው መሬት የሕዝብ መሬት ነው በማለት የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮ የወረዳው ፍርድ ቤት 2ኛ ውሳኔን አፅንቷል።
በዚህ ምክንያት አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህግ ጥሶ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጣቸውን ውሳኔ ሽሮባቸዋል፡፡ በእርግጥ የወረዳው ፍርድ ቤት ከሳሽም ተከሳሽም በአከራካሪው መሬት ላይ መብት የላቸውም ብሎ እርሳቸው ላይም ውሳኔ ያሳለፈ ቢሆንም፤ በእርሳቸው በኩል መብት እንዳላቸው ማስረጃዎችን እና የሰው ምስክሮችን እንዲሁም ቀድሞ የተሰጡ ውሳኔዎችን አያይዘው በማቅረባቸው ባለመብት መሆናቸውን ይገልፃሉ። ‹‹እኔ ከቀበሌው ጋር ተከራክሬ ሲወሰን ይግባኝአልጠየቁም።
ስከራከር እነርሱ አልተከራከሩም። የቀበሌው አስተዳዳሪ ራሱ ሲጠየቅ መሬቱ የሕዝብ መሬት ነው ሁለቱም አያገባቸውም ብሏል። እነርሱ ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ የእነርሱ መሬት ያልሆነውን ተከራክረዋል።
ሰዎቹ በመሬቱ ላይ የወረዳ ፍርድ ቤትም ሆነ የከፍተኛ ፍርድ ቤት መብት የላቸውም ብለዋል። ስለዚህ ባለመብት ባለመሆናቸው እንዲከራከሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር›› ሲሉ አቶ በቀለ ያስረዳሉ፡፡ ጨምረውም አቶ በቀለ እንደሚናገሩት፤ ፍርድ ቤት እየተከራከሩ ያሉት እርሳቸው እና ሌሎቹ ቦታው ላይ ያሉት ሰዎች ቢሆኑም ውሳኔው በክርክሩ ውስጥ ለሌለ አካል መተላለፉ የሕግ ስህተት መሆኑንም ይገልፃሉ።
ይህንን ምክንያት መሠረት በማድረግ አቶ በቀለ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት አመለከቱ።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት
ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደቡብ ምድብ ችሎት ውሳኔን ባለመቀበል ፍርድ ቤቱ መቀበል የሌለበትን ይግባኝ ተቀብሎ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን ሻረ። በተጨማሪ በክርክሩ ለሌለ አካል ውሳኔ ሰጥቶ ትዕዛዝ ያስተላለፈ መሆኑን ሠበር ሰሚ ችሎቱ ይይልኝ ብለው ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ማመልከቻ ቢያቀርቡም፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቶች ከሰጡት ውሳኔ ጋር በማነፃፀር መርምሮ ጉዳዩ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም ብሎ መዝጋቱን በአቶ በቀለ የቀረበው ሰነድ ያመለክታል። አቶ በቀለ በዚህ አላበቁም ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት በመቅረብ እንደገና የሕግ ስህተት መፈጠሩን አመለከቱ።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ያስተላለፈው ፍርድ ላይ እንደተብራራው ጉዳዩ በዝርዝር ታይቷል። አቶ በቀለ ለወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ የይዞታ መብትን ለማስከበር የቀረበ ነው። አንድ ሰው የይዞታ መብቱ በፍርድ ኃይል እንዲለቀቅለትና እንዲከበርለት ለመጠየቅ በመጀመሪያ ክስ የቀረበበት መሬት ሕጋዊ ይዞታው መሆኑን የማሰረዳት ግዴታ አለበት።
ይህ መሆን እንዳለበት በፍተሐብሔር ሕግ ቁጥር 1144 ድንጋጌዎች ይዘትና ዓላማ ላይ ተቀምጧል። አቶ በቀለ ይዞታቸው በአቶ ታደሰ ኡርጊ ከሕግ ውጭ የተያዘባቸው መሆኑን ገልፀው፤ ክስ ያቀረቡ ቢሆንም፧ አቶ በቀለ እና አቶ ታደሰ የሚከራከሩበት መሬት ፤ የአቶ በቀለ ሕጋዊ ይዞታ አለመሆኑ የሕዝብ መሬት መሆኑን በበታች ፍርድ ቤት የተሰራውን የፍሬ ጉዳይ ፤ የማስረጃ ምዘና የሕግ ስህተት የማረም ሥልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዳረጋገጠው የፍርድ ሠነዱ ላይ ያትታል። አቶ በቀለ፤ ክስ የቀረበበት መሬት ሕጋዊ ባለይዞታ መሆኑን የማስረዳት ግዴታውን አልተወጣም ።
ይህ ከሆነ አቶ በቀለ አቶ ታደሰ ከያዘው መሬት ይልቀቅልኝ ብሎ ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው መብት ጥቅም የሌለው መሆኑን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 33 ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻል ተቀምጧል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎት ፍሬ ጉዳይ በማጣራትና ማስረጃ በመመዘን ሒደት ተፈጸሙ የሚባሉ ስህተቶችን የማረም ሥልጣን እንደሌለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 80 ንዑስ አንቀጽ 3/ሀ/ እና በአዋጁ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 ተደንግጓል።
ስለሆነም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎትና የሰበር ችሎት የአቶ በቀለን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የሰጡት ውሣኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠበር ሰሚ ችሎትም መወሰኑን የሰነድ ማስረጃው ያረጋግጣል። አቶ በቀለ በዚህ አላበቁም በድጋሚ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል በማለት ለሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የሕግ ስህተት የተፈጠረ መሆኑን ዘርዝረው አቤቱታ አቀረቡ።
የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም ብሎ አጣሪ ጉባኤውም ምላሽ ሰጠ። አቶ በቀለ አላቆሙም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀኑ። ሕገ ተጥሷል። የፍርድ ቤቶች አሠራር የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት የሕገ መንግስት ትርጉም ይሰጥበት ሲሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቀረቡ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን 2ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ አቶ በቀለ ወዳጆ ያቀረቡትን የሕገ መንግስት ትርጉም የይግባኝ ጥያቄ ተቀብሎ መርምሮ ውሳኔ ሰጠ። በውሳኔው ላይ እንደተብራራው፤ አቶ በቀለ የሕገ መንግስት ጉዳዮች
አጣሪ ጉባኤ በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለምክር ቤቱ የይግባኝ ማመልከቻ አቅርበዋል። በማመልከቻቸውም ‹‹በኦሮሚያ ክልል፣ በባሌ ዞን፣ በጎሎልቻ ወረዳ፣ በአሊላ ቀበሌ የሚገኘውን በ1992 ዓ.ም በሕጋዊ መንገድ ተሰጥቶኝ በስሜ ግብር እየገበርኩበት ያለውን መሬት በስር ተከሳሾች የሆኑት ጉልበታቸውን በመተማመን የያዙብኝ ሲሆን፤ እንዲለቁልኝ በጎሎልቻ ፍርድ ቤት ክስ መስርቼ የግራ ቀኛችንን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ክርክር የተነሳበት መሬት የሕዝብ መሬት ነው፤ ከሳሽ ያቀረበው ክስ የሕግ መሠረት የለውም ብሎ የወሰነውን ውሳኔ በይግባኝ ባስገለብጥም አንደኛው የስር ፍርድ ቤት ተከሳሽ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር የወረዳው ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅናት የወሰነ ሲሆን፤ የኦሮሚያና የፌዴራል ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤቶችም የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም በማለት የወሰኑ ሲሆን፤ በዚህ ውሳኔ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9፣ 25፣ 37፣ 40፣ እና 79/3/ የተከበሩልኝ መብቶቼ የተጣሱብኝ በመሆኑ ተገቢው የሕገ መንግስት ትርጉም ተሰጥቶኝ የተያዘብኝ መብት እንዲለቀቅ እንዲደረግልኝ›› በማለት አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ የፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ እና የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአጣሪ ጉባኤውን ውሳኔና የባለሙያዎችን አስተያየት በማጣመር ጉዳዩን ተመልክቶ፤ አከራካሪው መሬት የሕዝብ መሬት ነው። ብለው ውሳኔ በማሳለፋቸው የተጣሰ የሕገመንግስት ድንጋጌ የለም።
የይግባኝ ቅሬታው የሕገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልገው አይደለም በማለት ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ወሰነ፡፡
በመጨረሻ
አቶ በቀለ እንደሚገልፁት፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የተፈጠሩ ስህተቶችን ዘርዝረው እንዲሁም ለሕገመንግስት አጣሪ ኮሚቴ አቅርበው ሕግን ተከትለው እስከመጨረሻው እንደተከራከሩ እየታወቀ፤ በተጨማሪ ክርክር ውስጥ ለሌለ አካል እንደማይወሰን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እያለ የሕዝብ መሬት ነው ብሎ የተከራከረ አካል ሳይኖር የሕዝብ መሬት ነው ተብሎ የተሰጠውን ውሳኔ የሕግ ስህተት የለም ብሎ ውሳኔ መስጠቱ በጣም የሚያሳዝን ነው።
መሬቱ የሕዝብ ነው ሊባል የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በኦሮሚያ የመሬት አጠቃቀም አዋጅ 130/ 1999 አንቀፅ ሁለት ሥር የሕዝብ መሬት የሚባለውን አስመልክቶ በግልፅ ተደንግጓል። አንድ ጥማድ መሬት በአዋጁ እንደተቀመጠው የሕዝብ መሬት የሚባል አይደለም ብለዋል። በተጨማሪ ቀደም ሲል የቀበሌው ውሳኔ የተሻረበት የወረዳ ፍርድ ቤት መዝገብ ቁጥር ሳይሻር እስከ አሁን መከራከራቸው እና ሌላ ውሳኔ መተላለፉም ሕገወጥ አሠራር መሆኑን አመልክተው፤ ሕግ እና ሕገመንግስት በመጣሱ የተንገላቱ መሆኑን እና መብታቸው እንደተጣሰባቸው ተናግረዋል።
አቶ በቀለ እንደሚገልፁት፤ እርሳቸውን ለመጉዳት ብለው ሲከራከሩ የነበሩት ተከሳሾች ማለትም መሬቱን ይዘው ይጠቀሙበት የነበሩ ሰዎች በመጨረሻ እርስ በርስ እስከመገዳደል ደርሰዋል።
አንዱ ሌላውን ገድሎ አንደኛው እስር ቤት ነው። ሌላኛው ሕይወቱ አልፏል። አሁን አከራካሪው መሬት በሟች እና በገዳይ ቤተሰብ እጅ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። ቀበሌው የአንድን ሰው ይዞታ ለሌላ ሰጥቶ ማገዳደል፤ ፍርድ ቤቶችም ሕጉን በአግባቡ አለማየት፤ ሕግን እና ሕገመንግስትን በመጣስ ሰዎችን ማገዳደል፤ አገር ሰላም እንዳይኖራት የማድረግ ተግባር እየተፈፀመ ነው።
ይህንን ለማስረዳት ያልገቡበት እንደሌለ አቶ በቀለ ይናገራሉ። የኦሮሚያም ሆነ የፌዴራል ሰበር ሰሚ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማስረጃ ምዘና ሥልጣን የሌላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ማየት ያለባቸው የሕግ ስህተትን ብቻ እንደነበር አመላክተዋል። የሕዝብ መሬት ነው የተባለውን ውሳኔ የወረዳ ፍርድ ቤት ሽሮታል። መሻሩን የሚሳይ የወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ተያይዞ ቀርቧል።
ነገር ግን ይህን ሳያዩ ማስረጃው የሕዝብ መሬት ነው ተብሎ ስለተመሰከረ፤ የሕግ ስህተት አልተሠራም። ስለዚህ የህግ ስህተት አልተፈፀመም ብለው ዘጉ። በጊዜው አፈጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም ነበሩ። ጉዳዩን ለአፈ ጉባኤዋ አቅርበው እንደነበርም ይናገራሉ። በሕገመንግስት አንቀፅ 25 ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው ይላል።
ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል ከሆነ እኔ ተከስሼ የሕዝብ መሬት ከተባለው ቦታ ላይ ከተፈናቀልኩ ለምን እነዛ ሰዎችስ አልተከሰሱም አልተነሱም የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውንም ይገልፃሉ። በሌላ በኩል በአንድ ፍርድ ቤት አንድ ጉዳይ ሁለት ጊዜ ታይቶ ያንንም ሳይመረምሩ የሕግ ስህተት የለም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ግራ የሚጋባ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ጨምረውም ፍርድ ቤቶች በደረጃ ይበላለጡ እንጂ የሚሰጡት ውሳኔ ሕጋዊ እና የሚፀና መሆኑን አስታውሰው፤ የወረዳው ውሳኔ በይግባኝ እስካልተሻረ ድረስ በውሳኔ ላይ ሌላ ውሳኔ መስጠት ሕገመንግስትን የሚፃረር ያልተገባ ተግባር እንዲሁም የሕግ ጥሰት መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዳላየው ያመለክታሉ። ሕገመንግስትን የሚፃረር ውሳኔ ተፈፃሚነት እንደሌለው በአንቀጽ 9 በግልፅ ተቀምጧል።
የሚሉት አቶ በቀለ፤ ‹‹ በደል ተፈፅሞብኛል፤ በወጪም ሞቻለሁ። ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ‹ኡኡኡ› እያልኩ ሰሚ አጥቻለሁ። ›› ይላሉ። ‹‹የእኔ መብት ብቻ ሳይሆን ፍትሕ ከሌለ እንዴት ይሆናል?›› በማለት የሚጠይቁት አቶ በቀለ፤ አንዱ አካል ስሕተት ቢሠራ የተቀሩት ማረም ለምን አልቻሉም? የፍርድ ቤትን ስህተት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምን አላየም? በማለት ይጠይቃሉ።
ፍርድ ቤቶች ከባድ ችግር አለባቸው። ሕግን እያዩ እየሠሩ አይደለም። ዘመድ ያለው ሰው ‹‹ከፍርድ ቤት ይህን መዝገብ እንዲህ አስደርጉልኝ›› ይላል። እርሱ ባለው መሠረት ይፈፀማል። ዘመድ የሌለው ገንዘብ የሌለው እንደማይፈረድለት በግልፅ የሚታይ ነው። ሃብታም ሆነም ድሃ በሕግ ፊት እኩል ለምን አይታዩም? አንድ ድሃ በማይረባ ጉዳይ መንገላታት ይበዛበታል? ይህ ለምን ይሆናል? በማለት ተከታታይ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። ሕግ ከፍርድ ቤቶች በላይ ሳይሆን ፍርድ ቤቶች ከሕግ በላይ እየሆኑ ነው።
ይህ ዴሞክራሲያዊነት ሳይሆን የአምባገነን አካሄድ ነው። ሕገመንግስት በአንቀጽ 37 ላይ ያለው ተግባር ላይ የለም። በወረዳ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ በክርክሩ ላይ መብት የለውም ተብዬ ቢሆን እኔ ድሃው ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ባቀርብ በሥነሥርዓት ሕግ 33 ላይ የተቀመጠው ከክርክሩ ንብረት ላይ መብት የሌለው ሰው መከራከር እንደማይችል በግልፅ አስቀምጧል ልንቀበልህ አንችልም ይሉ ነበር። ነገር ግን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሳሾቼን ያለመብታቸው ተቀብሎ እንዲከራከሩ አደረገ ይህም የሕግ ስህተት ነው ይላሉ።
‹‹ ሙስናን እናጠፋለን ማለት በወሬ ብቻ መሆን የለበትም። የኔ መንገላታት እና ለወጪ መዳረግ ለአገር ይጠቅማል። ምክንያቱም መንግሥት ይህንን በማየት ፍርድ ቤቶች እንዴት ሕግን እየተረጎሙ ነው? የሚለውን እንዲያይ ያደርጋል፡፡›› ካሉ በኋላ፤ ሚዲያው በፍትሕ ላይ መሥራት አለበት። መንግሥትም ይህንን በደንብ ሊያየው ይገባል ብለዋል። አቶ በቀለ ጉዳያቸው የታየው ወይዘሮ ኬሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ በነበሩበት ዘመን ነበር።
በድጋሚ እንዲታይላቸው ለሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኙም። ደውለው ሲጠይቁ እንዳልታየ እና ነባሮቹ ኮሚቴዎች ፋይሉን ይዘውት ሔደዋል መባላቸውን እና ማመልከቻቸው ለመዝገብ ቤት እንዳልተመለሰም የተነገራቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥር 4/2014